ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ደጋፊ አገራት የሩሲያን ነዳጅ ከዓለም አቀፍ ገበያ 'ለማስወጣት' ቃል ገቡ
ከ20 በላይ አገራት ዩክሬንን በመደገፍ "የሩሲያን ነዳጅ እና ጋዝ ከዓለም አቀፍ ገበያ ለማስወጣት" ቃል ገቡ።
አገራቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጫና በማሳደር ከዩክሬን ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እንዳሉት አገራቱ የተሰባሰቡት "በበጎ ፈቃደኛነት" ነው።
ስታርመር ለአገራቱ የጋራ ጉባዔ አዘጋጅተዋል።
አሜሪካ በሁለቱ የሩሲያ ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ዩኬም ከአሜሪካ ቀድማ ተቋማቱ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ሁለቱ የሩሲያ ነዳጅ አምራቾች በየቀኑ 3.1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጭ አገራት ይልካሉ።
ሮስኔፍት ከሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ግማሹን ይሸፍናል። ከዓለም አቀፍ ገበያው ደግሞ 6% ድርሻ አለው።
በለንደን በተካሄደው ጉባዔ ላይ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ "ሩሲያ ላይ ጫና ማሳደር ብቸኛው መንገድ ነው" ብለዋል።
በጉባዔው ላይ እንደተጠበቀው ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ለመስጠት ውሳኔ አልተላለፈም።
ዘለንስኪ ሩሲያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የአሜሪካ ቶማሀውክ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ቢያደርጉም ትራምፕ ሚሳዔሉን ለመስጠት አልፈቀዱም።
ዩክሬን የሩሲያን ነዳጅ ማቀነባበሪያዎች ዒላማ ማድረግ ትፈልጋለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለዩክሬን ቶማሀውክ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ከተሰጠ ምላሻቸው "የከፋ" እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ስታርመር በለንደኑ ጉባዔ "ፑቲን ሰላም አይፈልጉም" ብለዋል።
የዩክሬን አጋር አገራት እስከ ቀጣዩ ዓመት ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለዩክሬን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ያለፈው ሐሙስ መግለጻቸው አይዘነጋም።
የኅብረቱ አባል አገራት 122 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሩሲያ ንብረት ላይ ማዕቀብ ይጥላሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ከስምምነት አልደረሱም።
የዩክሬን አጋሮች የአገሪቱን "የአየር ኃይል ለማጠናከር" ቃል ገብተዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ኃይል አቅራቢ ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረስ ቀጥላለች።
ዘለንስኪ "በክረምት ወቅት በቅዝቃዜ ሊቀጡን አስበዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
የዩክሬን አጋሮች በምን መንገድ ከሩሲያ ጥቃት እንደሚከላከሏት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ፑቲንን እንዴት ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንደሚያመጡም ግልጽ አይደለም።
በሌላ በኩል ትራምፕ ከፑቲን ጋር በቡዳፔስት ሊያደርጉ አቅደው የነበረውን ውይይት አራዝመዋል።
ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ጋር በዩክሬን ጦርነት ላይ ተገናኝተው ለመነጋገር የያዙት ቀጠሮ እንዲዘገይ ከተደረገ በኋላ "ያለ ፍሬ የሚጠናቀቅ ስብሰባ" እንዲሆን እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ዩክሬን በዩናይትድ ኪንግደም በተሠሩ ስቶርም ሻዶ ሚሳዔሎች የሩስያን የኬሚካል ፋብሪካ መምታቷን ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች።
ክሬምሊን በበኩሉ ዩክሬን በረዥም ርቀት ጥቃቶችን መፈጸም የምትችልባቸውን የጦር መሣሪያዎች እንዳይሰጡ ምዕራባውያን ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።