ፈረንሳይን እያናወጠ ያለው ተቃውሞ እና አመጽ እንደቀጠለ ነው

ባለፈው ማክሰኞ አንድ የ17 ዓመት ታዳጊ መንገድ ላይ በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ከተገደለ በኋላ ፈረንሳይ በአመጽ እና በውድመት እየተናጠች ትገኛለች።

ዋና ከተማዋ ፓሪስን ጨምሮ በተለያዩ የፈረንሳይ ክፍሎች ውስጥ በፖሊስ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም አመጽ የተቀጣጠለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተቃውሞው ወደ ንብረት ማውደም እና ዝርፊያ መሸጋገሩን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ለእናቱ አንድ ልጅ የሆነው የ17 ዓመቱ ሟች ናሄል ፈጣን ምግቦችን በማድረስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ ማክሰኞ ጠዋት የትራፊክ ሕግ ጥሰሃል በሚል በፖሊሶች እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ነበር በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈው።

አመጹ በተባባሰበት ጊዜ አርብ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ተቃዋሚዎች የታዳጊው ሞት የቀሰቀሰውን ተቃውሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ እየወሰዱት ነው ሲሉ ከሰዋል።

በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ ፕሬዝዳንቱ የተቀጣጠለውን አመጽ ለመቆጣጠር ተጨማሪ ፖሊሶች እንደሚሰማሩ ገልጸው፣ በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመደንገግ ግን ተቆጥበዋል።

ፕሬዝዳንቱ ወላጆች በአመጽ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ልጆቻቸውን በቤታቸው ውስጥ እንዲሰበስቡ እና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችም አንዳንድ ይዘቶችን ከገጾቻቸው ላይ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

የአልጄሪያ ዝርያ ያለው ናሄል እናቱ ብቻዋን ያሳደገችው ሲሆን፣ በሚያውቁት ሰዎች ዘንድ የተወደደ ልጅ እንደነበር ይነገራል።

ግድያውን ተከትሎ ፈረንሳይን እያናወጣት ባለው አመጽ ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት በተቃዋሚዎች የወደመ ሲሆን፣ ፖሊስም አስከ አርብ ድረስ አንድ ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ይዞ አስሯል።

ማርሴይ በተባለችው የፈረንሳይ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ውስጥ የጦር መሳሪያ መሻጫ መደብር በአመጸኞች ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ተንገሯል። የከተማዋ ከንቲባም ማዕከላዊው መንግሥት ሥርዓት ለማስከበር ወታደሮችን እንዲያሰማራ ጠይቀዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት በተለያዩ ስፍራዎች የተቀሰቀሰውን ከባድ አመጽ ለመቆጣጠር በቀላል ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች የታገዙ 45,000 የፖሊስ መኮንኖችን ቢያሰማራም አሁንም ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው።

የፈረንሳይ መንግሥት እና የተለያዩ ወገኖች በመላው አገሪቱ የተቀጣጠለው እና ከባድ ውድመትን እያስከተለ ያለው ለቀናት የዘለቀው ተቃውሞ እንዲያበቃ ጥሪ እያረቡ ነው።

የፈረንሳይ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተመሳሳይ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ መልዕክቱ በቡድኑ አምበል ኪሊያን ምባፔ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ተሰራጭቷል።

የብሔራዊ ቡድኑ አባላት መልዕክትም በግድያው የተፈጠረውን ቁጣ እንደሚረዱ እና አመጽ እና ንብረት ማውደም መፍትሄ ስለማይሆን ተቃዋሚዎች ከብጥብጥ እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

በፈረንሳይ ውስጥ በፖሊስ አባላት የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ግድያዎች በተደጋጋሚ ተቃውሞን ሲቀሰቅሱ የቆዩ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ኅዳር ወር ባወጣው ሪፖርት ላይ በፖሊሶች የሚፈጸሙ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።

በተለይ አፍሪካውያን እና አረቦች በተደጋጋሚ በፖሊሶች በደል የተፈጸመባቸው ሲሆን፣ አሁንም የተገደለው ታዳጊ በተመሳሳይ የሰሜን አፍሪካ ዝርያ ያለው ታዳጊ ነው።

በፖሊስ የተገደለው ናሄል እናትም የልጇ ገዳይ ፖሊስ ኢላማ ያደረገው “የአረብ ገጽታ ያለው ትንሽ ልጅ በመሆኑ ነው” ስትል ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋለች።

ግድያውን ተከትሎ ለናሄል ፍትሕ የሚጠይቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የተሳተፉበት ተቃወሞ የተካሄደ ሲሆን፣ ይህም ቀስ በቀስ በወደ ኃይል እና አመጽ ተሸጋግሯል። ፖሊስም ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተኩሷል። ከዚያም በኋላ ቁጣው እና አመጹ ተባብሶ ንብረት ማውደም፣ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠል በስፋት አጋጥሟል።

ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ፈረንሳይ የሚያቀኑ ዜጎቿ የመደበኛ እንቅስቃሴ መቋረጥ ሊያጋጥም እንደሚችል በመግለጽ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና የባለሥልጣናትን ምክር እንዲከተሉ አሳስባለች።