ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ አመጽ ተጠናክሮ ሲቀጥል ለአመጹ ምክንያት የሆነው ፖሊስ ተከሰሰ
ባለፈው ማክሰኞ ፓሪስ አቅራቢያ አንድ ታዳጊ የገደለው የፖሊስ መኮንን ክስ ቢመሰረትም አመጹ በአገሪቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የ17 ዓመቱ ናሄል ኤም ከቅርብ ርቀት በጥይት ተመትቶ ነው የተገደለው።
ይህን ተከትሎ የተነሳው አመፅ በመላው ፈረንሳይ እየተቀጣጠለ ይገኛል። የሟች እናት ሐሙስ ዕለት የጠሩት ሰልፍ በርካታ ግጭቶችን አስከትሏል።
በሊል እና ማርሴ ከተሞች በርካታ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ለእሥር በቅተዋል።
ናንቴር በተሰኘችው ታዳጊው በሚኖርባት ከተማ አንድ ባንክ ያለበት ሕንፃ በእሳት ተቃጥሏል።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የሚለጠፉ ምስሎች እንደሚያሳዩት በርካታ ሥፍራዎች በእሣት እየጋዩ ነው።
በፓሪስና በሌሎች ከተማዎች የአውቶቡስና ባቡር ትራንስፖርት በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽት 3 ሰዓት ጀምሮ ተቋርጧል።
አንዳንድ ከተሞች ሰዎች በምሽት እንዳንይንቀሳቀሱ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት አመፁን ለመግታት 40 ሺህ የፖሊስ ሠራዊት በሃገሪቱ አሰማርቷል።
ማክሰኞ እና ረቡዕ ምሽት በነበሩ ተቃውሞዎች በርካታ ተሽከርካሪዎችና ሕንፃዎች የእሣት ሲሳይ ሆነዋል።
የሃገር ውስጥ ሚኒስትሩ ዤራልድ ዳርማኒን ረቡዕ ማታ 170 የፖሊስ መኮንኖች ጉዳት እንደደረሰባቸውና 180 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጠዋል።
ሐሙስ ከሰዓት በናንቴሬ የነበረው ተቃውሞ ሰላማዊ ቢሆንም የፖሊስ መኮንኖች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰምቷል።
የፈረንሳይ ጠ/ሚ ኤሊሳቤት ቦርን በ17 ዓመቱ ታዳጊ ሞት የተነሳ የተፈጠረውን ስሜታዊነት ቢረዱም አመፁን ግን ገስፀዋል።
“ምንም ነገር ለአመፅ ምክንያት ሊሆን አይችልም።” ብለዋል።
የታዳጊው መገደል በፖሊስና በተለይ ደግሞ ደከም ባሉ የፈረንሳይ ከተሞች በሚኖሩ ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ማሳያ ነው የሚሉ አስተያየቶች መደመጥ ጀምረዋል።
“ሃገራችን የምትከተለው ሕግ የፖሊስ መኮንኖች የሚጠብቅ ነው። ይህ ደግሞ ያለመከሰስ ባሕልን ያዳብራል” ሲሉ የናሄል ጠበቃ ያሲን ቦዝሩ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ነገር ግን የናሄል እናት በጠቅላላው የፖሊስ መኮንኖች አሊያም ሥርዓቱን ሳይሆን ልጇን የገደለውን መኮንን ነው የምትወቅሰው።
ታዳጊውን ከቅርብ ርቀት ተኩሶ የገደለው ፖሊስ ሽጉጡን የመዘዘው ሕይወቱ አደጋ ላይ እንዳለ ስለተሰማው እንደሆነ ይናገራል።
የፖሊሱ ጠበቃዎች ደንበኛቸው ድርጊቱን የፈፀመው “ሕጉን በተከተለ መንገድ ነው” ይላሉ።