ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ፖሊስ አንድ ታዳጊን በመግደሉ ምክንያት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ቢያንስ 150 ሰዎች ታሠሩ
አንድ የ17 ዓመት ታዳጊ በፈረንሳይ ፖሊስ መገደሉን የተቃወሙ ፈረንሳያውያን ያነሱት ተቃውሞ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
በዚህ ተቃውሞ የተሳተፉ ቢያንስ 150 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ናሄል ኤም የተሰኘው ታዳጊ በቅርብ ርቀት በፖሊስ ተተኩሶበት የተገደለው የትራፊክ መብራት ጥሷል በሚል ነው።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሠራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንሚያሳዩት መኪኖች በተቃውሞ ምክንያት እየተቃጠሉ ነው።
አልፎም በዋና መዲናዋ ፓሪስ ያሉ ሱቆች ለዘረፋ ተጋልጠዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ተቃዋሚዎች ወንድ ማረሚያ ቤት ተቀጣጣይ እሣት ሲወረውሩ ነበር።
የዜና ወኪሉ አክሎ እንደዘገበው 20 ገደማ ወጣቶች የማረሚያ ቤቱ መግቢያ በር ላይ ተቀጣጣይ እሣት እና ሌሎች ቁሳቁሶች ሲወረውሩ ታይተዋል።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንዳሳዩት የማረሚያ ቤቱ ድምፅ ማጉያ የአደጋ ጊዜ ጥሪ ሲያሰማ ነበር።
ሌ ሞንድ የተሰኘው ጋዜጣ እንዳስነበበው የተገደለው ታዳጊ መኖሪያ በሆነችው የፓሪስ አካባቢ የሚገኙ ባለሥልጣናት ሥፍራውን ለቀው ወጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ፓብሎ ፒካሶ በተባለው አካባቢ ነው አመፅ በርክቶ የሚገኘው። የአካካቢው ታዳጊዎች ገና ፀሐይ ብቅ ከማለቷ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
ምንም እንኳ በዚህ አካባቢ አመፅ ቢበረክትም በሌሎችም የፓሪስ ክፍሎች ተቃሚዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች ተቀጣጣይ እሣት ሲወረውሩ ታይተዋል።
በሰሜናዊ ሊል እና በምዕራባዊቷ የረኔ ከተሞች እንዲሁ በርካታ ተቃዋሚዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን ወጥተው ናሄል ላይ የተፈጸመው ግድያ “ይቅርታ የማይደረግለት ነው” ብለዋል።
ነገር ግን በዚህ ንግግራቸው በርካታ የፖሊስ መኮንኖች ቅያሜ ማሳደራቸው ተነግሯል።
አሊያንስ ፖሊስ የተሰኘው ማኅበር የፖሊስ መኮንኖች ሳይፈረድባቸው ወንጀለኛ ሊሆኑ አይገባም ሲል፣ ዩናይትድ ኤስጂፒ የተሰኘው ቡድንም እንዲሁ ፖለቲከኞች “የፖሊስ ጥላቻን እያስፋፋ ነው” ሲል ወቅሷል።
የሟቹ ታዳጊ እናት ሞኒያ አንድ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በተሠራጨ ቪድዮ ልጄን ወስደውብኛል ስትል ታይታለች።
ሞኒያ፤ ለልጇ ማስታወሻ ሲሉ ሰዎች ዘመቻውን ይቀላቀሉ ዘንድ ጥሪ ስታቀርብም ነበር።
ታዳጊውን የገደለው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ሽጉጡን አውጥቶ የተኮሰው ታዳጊው አደጋ ስለደቀነበት እንደሆነ ነው የሚናገረው።
ከፈረንሳዊ አልጄሪያ ቤተሰብ የመጣው ናሄል በፈረንሳይ የትራፊክ መብራት አጠገብ በፖሊስ እጅ የተገደለ ሁለተኛው ሰው ነው።
ባለፈው ዓመት 13 ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ በፖሊስ መገደላቸው ይታወሳል።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች በአውሮፓውያኑ 2017 የወጣውን እና ፖሊሶች ሽጉጣቸውን እንዲጠቀሙ የሚያበረታታውን ሕግ ይወቅሳሉ።