ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቤላሩስ መሪ የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ቤላሩስ መግባቱን ገለጹ
በሩሲያ ለ24 ሰዓታት የቆየ አመጽ የመራው የቫግነሩ መስራች እና አለቃ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ቤላሩስ መግባቱ ተገለጸ።
“አዎ፤ በትክክል ዛሬ ቤላሩስ ነው ያለው” ብለዋል የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቡድኑ መሪ ከአገር እንዲወጣ ማመቻቸታቸውን በመግለጽ።
የቭጌኒ ፕሪጎዢን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የቀሰቀሰው አመጽ በስምምነት እንዲቋጭ ተደርጎ ቡድኑ ተቆጣጥሮ ከያዛት የሩሲያ ከተማ ሲወጣ ከታየ በኋላ የየቭጌኒ አድራሻ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል።
ትናንት ማክሰኞ የየቭጌኒ የግል ጀት ወደ ቤላሩስ ሚኒስክ ስትበር ታይታ ነበር።
ሉካሼንኮ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አባላት መሪያቸውን በቤላሩስ መቀላቀል የሚፈልጉ ከሆነ ክፍቱን የተቀመጠ ወታደራዊ ካምፕ አለ በማለት ወደ ቤላሩስ እንዲመጡ ግብዣ አቅርበውላቸዋል። “አጥር አለው፤ ሁሉም ነገር የተሟላ ነው። ድንኳናችሁን መትከል ነው” ብለዋል።
አመጹን ለማቆም በተደረሰው ስምምነት የቭጌኒ የደኅንነት ማረጋጋጫ የተሰጠው ሲሆን አባላቱ ደግሞ ምንም አይነት ክስ እንደማይመሰረትባቸው ከስምምነት ተደርሷል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አገሪቱን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር የከባድ መሳሪያ ትጥቅ እንደሚፈታ አስታውቋል።
የቡድኑ አባላትም መደበኛ የሩሲያ ጦር ሠራዊት መቀላቀል፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ አልያም ወደ ቤላሩስ ማቅናት ይችላሉ ተብሏል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆኑት ፖላንድ፣ ላትቪያ እና ሊቱኒያ የቫግነር አባላት ወደ ጎረቤት አገር ቤላሩስ መምጣታቸው ለደኅንነታችን አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የሉቲኒያ ፕሬዝዳንት አማካሪ የቅጥረኛ ቡድኑ አባላት በወታደራዊ ሰርጎ ገብ ተግባራት ላይ ስለሚሰማሩ አደገኞች ናቸው ብለዋል። የሉቲኒያ ፕሬዝዳንት ጊታናስ ናኡሴዳ ደግሞ ቫግነር “ገዳይ” አባላቱን በቤላሩስ የሚያሰማራ ከሆነ ጎረቤት አገራት “የበለጠ ያለመረጋጋት አደጋ ይጋረጥባቸው” ብለዋል።
የኔቶ ዋና አዛዥ ጄንስ ሰቶለተንበርግ በበኩላቸው ‘ከሞስኮም ሆነ ከሚንስክ” በአባል አገራት ላይ ሊቃጡ ከሚችሉ አደጋዎች ድርጅቱ አባላቱን ለመከላከል ዝግጁ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት ሩሲያ ታክቲካል የኒውክለር መሳሪያዎችን በቤላሩስ ተክላለች። ፕሬዝዳንት ፑቲን የኒውክለር መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት የሩስያ ድንበር አደጋ ላይ ከወደቀ ብቻ ነው ብለው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቫግነር ሙሉ በሙሉ በሩሲያ መንግሥት ፋይናንስ እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል።
ፑቲን ባለፉት 12 ወራት ለቫግነር ቡድን አባላት ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ለመሸፈን 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል ያሉ ሲሆን የቡድኑ አባላትን ለሚመግበው ኮንኮርድ ለተባለ የየቭጌኒ ምግብ አቅራቢ ድርጅት ተጨማሪ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪም በአመጽ ወቅት አብራሪዎች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል። የቫግነር ቡድን አባላት ወደ ሞስኮ እየገሰገሱ በነበረበት ወቅት ከሰባት ያላነሱ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች እና አውሮፕላኖችን መትተው ጥለዋል።