መካከለኛው ምሥራቅን ወደለየለት ጦርነት ለማስገባት የገፋው ያለፈው ሳምንት

ባለፈው ዓመት ከፍተኛ አደጋ የጋረጡ በርካታ ክስተቶች አሉ። ይኼኛው ግን የከፋው ነው።

ባለፉት ሰባት ቀናት የሔዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስረላህ ተገድሏል፤ እስራኤል እግረኛ ጦር ወደ ሊባኖስ ገብቷል፤ እንዲሁም ኢራን እስራኤል ላይ ያነጣጠሩ ከ200 በላይ ባሌስቲክ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።

በአሜሪካ የሚመሩት ምዕራባውያን እና የቀጠናው ኃያል አገራት ውጥረቶች እንዲረግቡ ጥረት እያደረጉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ግጭቱ “አሁኑኑ እንዲያበቃ”፤ አሜሪካ፣ ዩኬ እንዲሁም ጀርመን የሚገኙበት የቡድን 7 አባል አገራት ደግሞ “ውጥረት አንዲያረግቡ” ጥሪ አቅርበዋል።

ነገር ግን እስካሁን ባለው የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ለየለት ግጭት ለመግባት ጫፍ ደርሷል።

ባለፈው ሳምንት የተከሰቱት ዐበይት ግጭቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

አርብ ምሽት፡ ናስረላህ ተገደሉ

መስከረም 17 በቤይሩት ሰማይ ፀሐይ ስትጠልቅ የአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በከፍተኛ ፍንዳታ ተናወጠ።

በዚህ ፍንዳታ በርካታ ሕንጻዎች ሲመቱ፣ መሬት ላይም ትልቅ ክፍተት ተፈጠረ።

ከሊባኖስ ዋና ከተማ በርቀት ማየት እስኪቻል ድረስ ሰማዩን አቧራ፣ ምድሩን ደግሞ የፍርስራሽ ክምር ሸፈነው።

ይህ የአየር ጥቃት ዒላማ አድርጎ የነበረው ምድር ለምድር የተሰራን መሸሸግያን ነበር፤ የሔዝቦላው መሪ ሐሳን ናስረላህም ተገደሉ።

ናስረላህ ለረዥም ዓመታት ይህንኑ የእስራኤል ጥቃት ፈርተው ከእይታ ተሰውረው ነበር የሚኖሩት።

የመሪው ሞት እስራኤል ሔዝቦላህ ላይ አነጣጥራ ስትፈጽመው የነበረው እና 500 ሰዎችን የገደለው ጥቃት መቋጫ መሰለ።

በርግጥ እስራኤል ከዚያ በፊት የሔዝቦላህ የግንኙነት ሬዲዮ እና ፔጀሮችን አፈንድታ 32 ሰዎችን ሰትገድል 3000 ደግሞ አቁስላ ነበር።

የናስረላህ ሞት ከሰዓታት በፊት ውጥረቶች ይረግባሉ፣ አፈሙዞች ዝም ይላሉ የሚለውን ቀቢጸ ተስፋ እስከናካቴው ይዞት ጠፋ።

በኒውዮርክ እየተካሄደ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አሜሪካ ለ21 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ አቅርባ ውይይት እየተካሄደ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ዳኒ ዳኖን ራሳቸው አገራቸው ለሚመጡ ሀሳቦች “ክፍት መሆኗን” በመድረኩ ላይ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔተንያሁ ከተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ወጥተው ወደ አገራቸው በመጀመርያው በረራ አምርተዋል።

በዛውም ጭል ጭል እያለ የነበረው የዲፕሎማሲ ተስፋ ላይ ውሃ ተቸለሶበታል።

ሰኞ ምሽት፡ እስራኤል ሊባኖስን ወረረች

ከሦስት ቀናት በኋላ የእስራኤል ምድር ጦር የሊባኖስን ድንበር ጥሶ ገባ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል የምድር ጦሩ በአገሪቱ የሚኖረው ተልዕኮ “ውስንን እና የተለየ” እንደሆነ ገለፀ።

በእስራኤል እና በሔዝቦላህ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እንደ ሊባኖስ የአደጋ ጊዜ መስርያ ቤት መረጃ እስካሁን ድረስ 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ቤት ንበረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል።

ቢያንስ 8 የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

እስራኤል አሁን የከፈተችው ዘመቻ ዓላመው ሔዝቦላህ ሮኬቶችን እንዳይተኩስ እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ ጥቃት እንዳይከፍት ማድረግ ነው።

ሔዝቦላህ ባለፈው ዓመት ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ከከፈተበት ጊዜ አንስቶ አጋርነቱን በመግለጽ በየቀኑ ለማለት በሚያስችል መልኩ ሚሳዔሎችን ያስወነጭፋል።

አሁን የእስራኤል መከላከያ እግረኛ ጦር ኃይል በጋዛ እንዲሁም በሊባኖስ ውግያ እያካሄደ ይገኛል።

ይህ ባለፉት አስር ዓመታት አልተካሄደም።

በሔዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ለመጨረሻ ጊዜ ውግያ የተካሄደው በአውሮፓውያኑ 2006 ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብነት እንዲያበቃ ተደርጓል።

በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ሔዝቦላህ ተዋጊዎቹን ከደቡባዊ ሊባኖስ እንዲያስወጣ ቢልም በኢራን የሚደገፈው አማፂ ግን ጡንቻው እየፈረጠመ፣ የመገዳደር አቅሙም እየገዘፈ መጣ እንጂ ቦታዎቹን ለቅቆ አልወጣም ነበር።

እስራኤል ሔዝቦላን ከሊባኖስ የፖለቲካ መድረክ ፈጽሞ ማስወገድ እፈልጋለሁ ብላ እስካሁን አልተናገረችም።

ነገር ግን “የተመጠነ እና የተለየ” ባለችው በዚህ ጥቃት የሔዝቦላህ ተዋጊዎችን ብዛት እና የመዋጋት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማሽመድመድ ትፈልጋለች።

ማክሰኞ ምሽት፡ ኢራን እስራኤልን አጠቃች

በሚቀጥለው ቀን ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ሲል በመላ አገሪቱ የሚገኙ 10 ሚሊዮን እስራኤላውያን ከኢራን የተተኮሱትን 200 ያህል ባሌስቲክ ሚሳዔሎች ሽሽት በአቅራብያቸው ወደ ሚገኙ ምሽጎች ሮጡ።

እስራኤል እና አጋሮቿ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የኢራንን ሚሳዔሎች በማክሸፍ ላይ ተጠምደው አመሹ።

ይህም በቀጠናው ያለው ግጭት እየሰፋ መምጣቱን አመላካች ሆነ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል አብዛኞቹ ሚሳዔሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት መክሸፋቸውን ገልጿል።

ነገር ግን በመካከለኛው እና በደቡባዊ እስራኤል የወደቁ ሚሳዔሎች ነበሩ።

በዚሁ ጥቃትም በዌስት ባንክ አንድ ፍልስጤማዊ መሞቱም ተዘግቧል።

ቴህራን ባለፈው ዓመት እስራኤል ላይ ጥቃት ስትፈጽም ቀድማ ማስጠንቀቅያ ልካ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን የምትደግፋቸው አማፂያን ውዥንብር ውስጥ በነበሩበት ሰዓት በርካታ ባሌስቲክ ሚሳዔሎችን በድንገት በመተኮስ ኃይላቸው አለመዳከሙን፣ አሁንም የእስራኤልን ጥቃት መመከት እንደሚችሉ ለማሳየት የፈለገች ይመስላል።

ምንም አንኳ ኢራን የሚሳዔል አረሮችን እስራኤል ላይ ብታዘንብም ወደ የለየለት ጦርነት ለመግባት ግን ፍላጎት ያላት አትመስልም።

በቀጠናው የለየለት ጦርነት ቢቀሰቀስ ኢራን ምን ክፉኛ እንደምታጣ በሚገባ የተረዳች ትመስላለች።

ምናልባትም የእስላማዊ ሪፐብሊክ ፍጻሜን ያበስር ይሆናል።

እስራኤል ፈርጣማ ክንዶች ያሏቸው ምዕራባውያን አጋሮቿ፣ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ ጎረቤቶቿ የኢራንን ሚሳዔሎች ለማክሸፍ ፈቃደኛ ብቻ ሳይሆን ዝግጁም ናቸው።

ኢራን ምጣኔ ሀብቷ የተዳከመ፣ ሙሉ በሙሉ የሕዝቡ ድጋፍ የሌለው መንግሥት የሚመራት አገር በመሆኗ በቀጠናው ያለውን ሕብረት መቋቋም ትችላለች ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን ክፉ ቀን ቢመጣ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ አብሯት የሚቆም ጠንካራ አጋርም የላትም።

አርብ ዕለት በቴህራን በነበረው የጸሎት ስነስርዓት ላይ የኢራን ሀይማኖታዊ መሪ አያቶላህ ካሜኔይ የአገራቸው አይበገሬነት ድምጽ መሆናቸውን ቢያሳዩም፣ ኢራን ግን ጦርነቱ ቢባባስ መቋቋም እንደማትችል ታውቃለች።

በቀጣይ ምን ይሆናል?

ሔዝቦላህ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ቢሆንም በሊባኖስ ውግያውን ለመቀጠል ቃል ገብቷል።

ታሪክ እንደሚያሳየው ደግሞ እስራኤል ወደ ሊባኖስ እግሯን ለማስገባት ቀላል ቢሆንላትም ለመውጣት ግን ፈተናው ብዙ ነው።

ኢራን እስራኤል ላይ ላደረሰችው ጥቃት ምላሿ ምን ይሆናል የሚለው የቀጠናው አገራትን ከማክሰኞ ጀምሮ በጥፍራቸው ቆመው እንዲጠብቁ አድርጓል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን ደግሞ እስራኤል የኢራንን ኒውክለሮች ወይንም የነዳጅ ዘይት ተቋማት አጸፋ ለመመለስ በሚል እንዳታጠቃ መናገራቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤል ብርቱ ምላሽ ሳይታለም የተፈታ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔተንያሁ የቅርብ ጊዜ ንግግሮችም የሚጠቁሙትም በኢራን የስርዓት ለውጥ እንዲኖር እያሰቡ መሆኑን ነው።

ነገር ግን የእስራኤል የአሁን ግብ ከፊቷ ያለውን ጥቃት መከላከል ላይ ይመስላል።

በጋዛ “የተሟላ ድል” በአገሪቱ በሰሜናዊ ድንበር አካባቢ በሔዝቦላህ የተቃጣውን ጥቃት ደግሞ ማስቆም።

የእስራኤል መሪዎች በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ላይ መሆናቸውን ይረዳሉ። ቤንጃሚን ኔተንያሁ አገራቸው በጋዛ፣ ሊባኖስ፣ ዌስት ባንክ፣ የመን፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶርያ ሰባት አቅጣጫዎች ጦርነት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት ምንም እንኳ በኢራን ከሚደገፉ እና መቀመጫቸውን ኢራቅ እና ሶርያ ካደረጉት ኃይሎች የመጣው ጥቂት ቢሆንም ከሰባቱም አቅጣጫዎች እስራኤል ላይ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።

እስካሁን ቀጠናው ወደ ለየለት ጦርነት አልገባም። ነገር ግን በርካታ ባለድርሻ አካላት እጃቸውን ማስገባታቸውን ለሚያስተውል በጋዛ የተቀሰቀሰው ጦርነት በፍጥነት ወደ ሌሎች ጎረቤት አገራትም እንደተለመደው ተዛምቷል።