ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሊባኖስ የሚወጡበት መንገድ እንዲፈለግላቸው እየተማጸኑ ያሉት ኢትዮጵያውያን
በጦርነት እየታመሰች ባለችው ሊባኖስ ከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ለመውጣት ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለማስወጣት ሥራ መጀመሯን አስታወቀ።
እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃት ከጀመረች ሁለት ሳምንት ሲሆናት ከቀናት በፊት ደግሞ የእግረኛ ሠራዊቷን አሰማርታ ሊባኖስ ውስጥ ዘመቻ እያካሄድች መሆኑ ተዘግቧል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ደግሞ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አመልክተዋል።
ጦርነቱ በፈጠረው አደጋ እና ችግር ምክንያትም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ በመውጣት ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ቢቢሲ ያናገራቸው ሦስት ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በሊባኖስ የሚገኙትን ዜጎቹን ለማስወጣት የሚሠራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካ አያኖ የሚመራ ኮሚቴ ማቋቋሙን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኮሚቴው በችግር ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ለማስወጣት የሚያግዙ ባለሙያዎችን ወደ ሊባኖስ እንደሚልክ የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቤይሩት በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት አማካይነት እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋነኛው ጥቃት እየተፈጸመ የቆየው የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ የሚገኝበት በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የአገሪቱ ዜጎች እና በተለያዩ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው ወደ ቤይሩት እና ሌሎች ከተሞች ሸሽተዋል።
የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ከሆነው አካባቢ ሸሽተው ከወጡት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ዓለም ባለፈው ቅዳሜ ነበር ከልጇን እና ከባለቤቷ ጋር ወደ ዋና ከተማዋ ቤይሩት የገባችው።
ይኖሩበት በነበረው አካባቢ የተጸመ ጥቃት እንዳስደነገጣቸው እና ቤታቸውን ለቀው ለመሸሽ እንደተገደዱ የምትናገረው ዓለም “በድንጋጤ ምንም ነገር ሳንይዝ ነው ነፍሳችንን ለማትረፍ የወጣነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የሊባኖስ ክፍሎች ወደ ዋና ከተማዋ ቤይሩት እየገቡ ሲሆን፣ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በመሄድ ድጋፍ እና ወደ አገራቸው የሚመለሱበት መንግድ እንዲፈለግላቸው ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ምንም ምላሽ እንደሌለ ይናገራሉ።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሥራ በመቆሙ እና አሠሪዎቻቸው ትተዋቸው በመሸሻቸው ለችግር መገላጣቸውን እየተናገሩ ሲሆን፣ ያለው ሁኔታ ለሕይወታቸው ጭምር አስጊ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከዋና ከተማዋ በራቁ አካባቢዎች ያሉ እና ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለመንቀሳቀስ እና ድጋፍ ለማግኘት ፈተና ገጥሟቸዋል።
ሳይዳ በተባለው የሊባኖስ ገጠራማ ክፍል የምትኖረው ኢትዮጵያዊቷ ሔለን “ሕጋዊ ወረቀት የሌለን ኢትዮጵያውያን ብዙ ነን። በዚህ ምክንያት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አንችልም። ወደ አገራችን እንድንገባ አግዙን” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
እስራኤል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የነበራት የድንበር ግጭት ወደለየለት ጦርነት እያመራ ሲሆን፣ ቴል አቪቭ ከአየር ድብደባዋን በተጨማሪ የእግረኛ ሠራዊት አሰማርታ ወረራ እያካሄደች መሆኑ እየተዘገበ ነው።
መጠጊያ ያጡ ኢትዮጵያውያን ጎዳናዎች ላይ መውደቃቸውን የሚናገሩ ሲሆን፣ የእስራኤል ጥቃት ቤይሩትን ጨምሮ በሚያካሂደው የአየር ድብደባ የመኖሪያ ሕንጻዎች ዒላማ በመሆናቸው የአገሪቱ ዜጎች ጭምር ወደ ጎዳናዎች እየወጡ ነው።
“የት እንደሚመታ አይታወቅም። ማለት የሚቻለው እግዚአብሔር ይጠብቀን ብቻ ነው” የምትለው በደቡባዊ ሊባኖስ የምትገኘው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት እታገኝ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በእጅጉ አስፈሪ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በምትገኘው ሊባኖስ ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች የሆኑ እና በቤት ውስጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ 150 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ከአራት ዓመት በፊት የሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመልክታል።
ዛሬ አርብ ንጋት አካባቢ የእስራኤል አየር ኃይል በቤይሩት ከፍተኛ የአየር ድብደባ አድርሷል። ፍንዳታው የተከሰተው ከቤይሩት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብዙም ሳይርቅ ነው።
ጥቃት ከተሰነዘረበት ስፍራ አቅራቢያ የሚገኘው አየር ማረፊያው ዳሂህ የሚባለውን የሄዝቦላህን ይዞታ የሚጎራበት ነው።
በቤይሩት ንጋት ላይ የፍንዳታው ጭስ ከርቀት ይታይ እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስራኤል እያካሄደችው ባለው ጥቃት በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና እንደተገደሉ የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ሲሆን እስካሁንም ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል።
“ሊባኖስ ውስጥ የምንገኝ ስደተኞች በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” የምትለው ሔለን በጥቃቱ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ያልተረጋገጠ ወሬ እንደደረሳት ትናገራለች።
አክላም እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሥራ እና እንቅስቃሴን በማስተጓጎሉ ገንዘብ አግኝቶ የዕለት ፍላጎትን ማሟላት አስቸጋሪ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በርካታ በቤት ውስጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ያለምግብ እና መጠለያ በአስከፊ ችግር ላይ ይገኛሉ።
የአየር ጥቃቱ ዒላማ የሚያደርገው የሄዝቦላህ ይዞታዎችን ነው የምትለው እስራኤል በቤይሩት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽማለች። ሊባኖሳውያንም ዒላማ ይሆናሉ ከሚሏቸው ስፍራዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እየሸሹ በመቶሺዎች ተፈናቃይ ሆነዋል።
ቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አካባቢ “የወደቀ ቦምብ አለ ስለተባለ ወደ ቆንስላው ለመሄድ ፍርሃት ይዞናል” የምትለው ሔለን ኤምባሲው በሚችለው አቅም እገዛ እያደረገላቸው እንደሆነ ትገልፃለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በጦርነቱ ምክንያት ሊባኖስን ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ሰኞ መስከረም 20/2017 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ ጥሪ አቅርቧል።
ቆንስላው እንዳለው ከአገሪቱ የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያኑን ከሊባኖስ “የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት” ዝርዝር መረጃቸውን በመስጠት በተዘጋጁ የስልክ ቁጥሮች በኩል እንዲመዘገቡ ወይም በዋትስአፕ በኩል እንዲልኩ ጠይቋል።
በሊባኖስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ማቲው ሆሊግዎርዝ በቤይሩት ያለውን ሁኔታ “አስጨናቂ” ሲሉ ገልጸውታል።
አርብ ማለዳ የደረሰው የቤይሩት ፍንዳታ እስራኤል በዋና ከተማዋ አንድን ሕንጻ በቦምብ ካወደመች ከ24 ሰዓት በኋላ የተከሰተ ነው።
ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት በአደጋው ነፍስ ለማዳን በአካባቢው ከደረሱ ሠራተኞቹ ዘጠኙ ተገድለውብኛል ብሏል።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ደግሞ 40 የእሳት አደጋ እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሦስት ቀናቱ የእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታ የእስራኤል ጥቃት 1300 ሰዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የእስራኤል ጦር በመዲናዋ ቤይሩት እና በሌሎች የሊባኖስ ክፍሎች የሚያካሂደውን የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል።