ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘ጋዛ ትልቅ የመቃብር ስፍራ ሆናለች’
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ወይም መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ማለዳ ሐማስ በእስራኤል ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጸመ። በዚህም በደቡባዊ እስራኤል ከ1200 የሚሆኑ ንጹሐንን ገድሎ 251 ሰዎችን አግቶ ወሰደ።
ይቺ ቀን በፍልስጤማውያን ላይ ይህን ሁሉ ጦስ ታስከትላለች ያለ አልነበረም።
ቢቢሲ ከዚህ አንድ ዓመት ሊማላው በተቃረበው ዘግናኝ ጦርነት በኋላ በነዋሪዎች ሕይወት ላይ ምን የተለየ ነገር ተፈጠረ? የሚለውን እንዲህ ሰንዶታል።
“የሆነው ነገር ቅዠት ነው የሚመስለኝ” ፋጢማ
ፋጠማ ኢዳማ እና ቤተሰቦቿ ሕይወታቸውን ሙሉ በሰሜናዊ ጋዛ ነው የኖሩት። ላለፉት ወራት ረሃብ፣ ግድያ እና ሞት በቤተሰቧ ላይ ደርሷል።
አሁን እሷ እና ባለቤቷ ያሉበትን ሁኔታ “ከቆሙት በታች - ከሞቱት በላይ” ስትል ትገልጸዋለች።
ለአንድ ዓመት ያህል ኮማ ውስጥ እንደነበረች ይሰማታል። ይሄ የምታየው ጥፋት እና ውድመት ሁሉ ቅዠት ይመስላታል። ከቅዠቷ ስትመለስ የምታውቃትን ጋዛን እንደምታገኝ ታምናለች። ጋዛ ለእርሷ “ውብ እና በሰዎች እንቅስቃሴ የተሞላች ንቁ ከተማ” ናት ወይም ነበረች።
ወደ ቀልቧ ስትመለስ እውነታው ይገለጥላታል። የምትወዳት ከተማ የፍርስራሽ ክምር ሆናለች።
“አንድ ቀን ገንብተናት ወደ ውበቷ እንመልሳታለን” ትላለች።
“እስራኤል ሚስቴን ልጆቼን እና ህልሜን በሚሳዔል ቀበረቻቸው” አሽራፍ
አሽራፍ አታር ይህ ጦርነት ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ይላል።
በኻን ዩኒስ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በነርስነት ያገለግላል።
ሚስቱ እና 6 ልጆቹ በእስራኤል ጥቃት ተገድለውበታል።
የአሽራፍ ሚስት በተባበሩት መንግሥታት ተራድኦ ሥራዎች ኤጀንሲ (UNRWA) ነበር የምትሠራው።
ትልቁ ልጃቸው ኢህሳን ይባላል። 15 ዓመቱ ነበር። ትንሹ ልጃቸው ወጢን ገና 20 ወሩ ነበር ከተወለደ።
አሽራፍ እና ሚስቱ ሐላ አራት-መንታ (quadruplets) ልጆች ነበሯቸው። ሁለቱ ወንዶች፣ ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። 10 ዓመታቸው ደርሰው ነበር። የፈጣሪ ስጦታዎቼ እያለች ነበር የምትጠራቸው እናት ሐላ። አሁን ሁሉም አፈር ለብሰዋል።
“ሁልጊዜ ወደፊት ስለሚኖረን ሕይወት ከባለቤቴ ጋር እናወራ ነበር። ወደፊት ስለምንገነባው ቤታችን እናወራ ነበር። ልጆቻችን ወደፊት ምን ማጥናት እንዳለባቸው እናወራ ነበር። የእስራኤል ቦምብ ልጆቼን፣ ባለቤቴን እና ህልሜን ቀበራቸው።”
በዌስት ባንክ በጽንፈኛ እስራኤላውያን የተገደሉ
በአውሮፓውያኑ መስከረም 23/2024 የተባበሩት መንግሥታት እንደገለጸው 693 ፍልስጤማውያን እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ ውስጥ ተገድለዋል። 676 የሚሆኑት በእስራኤል ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ 12 የሚሆኑት ደግሞ በእስራኤል ሰፋሪዎች ነው የተገደሉት።
ፍልስጤማውያን እንደሚሰጉት ከሆነ አክራሪ የእስራኤል ሰፋሪዎች ይህን ሕገ ወጥ ሰፈራቸውን በቋሚነት በዚህ በዌስት ባንክ ሊቀጥሉ ይችላሉ።
በእስራኤል ያለው ሁኔታ
ባለፈው ዓመት መስከረም ማብቂያ ላይ በሐማስ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤል 1200 ሰዎች ተገድለውባታል።
ቢቢሲ በሰበሰበው መረጃ መሠረት አምስት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ለዚህ ጥቃት ዝግጅት ከሐማስ ጋር ከ2020 ጀምሮ ልምምድ ሲያደርጉ ነበር።
በዚያው ዕለት 251 ሰዎችን ሐማስ አፍኖ ወስዷቸዋል። በአንድ ዓመት ወስጥ የተወሰኑ ታጋቾች ተለቀዋል። አንዳንዶቹ የተለቀቁት በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በወታደራዊ ኦፕሬሽን ነው ነጻ የወጡት።
“ወንድሜ እና ልጆቹ በሕይወት ያሉ ይመስለኛል” ያርደን
የ34 ዓመቱ ያርደን ከባለቤቱ ሺሪ እና ከሁለት ልጆቹ ጋር ነበር በሐማስ ታግቶ የተወሰደው።
በኅዳር 29/2023 ሐማስ የያርደን ባለቤት እና ሁለቱ ልጆቹ መሞታቸውን ይፋ አደረገ። የተገደሉት ደግሞ በእስራኤል የአየር ጥቃት ነው። የእስራኤል መንግሥት በእኔ ስለመገደላቸው እያጣራሁ ነው ብሏል።
ኦርፊ ቢባስ የያርደን እህት ናት። የወንድሟ እና የቤተሰቡ ዕጣ ፈንታ አሁንም ድረስ ያስጨንቃታል። አሁንም ሞተዋል የተባሉት ልጆቹ በሕይወት ይኖራል ብላ ተስፋ ተደርጋለች።
“በሰላም ጉዳይ እምነቴ ተሟጧል” አዳ ሳጊ
አዳ ሳጊ የ75 ዓመት አሮጊት ናቸው። የሰላም አቀንቃኗ አዳ ከቤታቸው ነበር በሐማስ ታግተው የተወሰዱት። ለ53 ቀናት ከታገቱ በኋላ ተለቀዋል።
አዳ የተቀለቁት በሰላም ስምምነት 240 ፍልስጤማውያን እስረኞች በ105 ታጋቾች ለውጥ በተደረገበት ጊዜ ነበር።
“ከዚህ ወዲያ በሰላም ላይ እምነቴ ተሟጧል” ይላሉ።
90% ሕዝብ ተፈናቅሏል
የተባበሩት መንግሥታት የጋዛ ነዋሪ ብዛት 2.1 ሚሊዮን ነው ብሎ ያምናል። 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ታዲያ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።
ባለፈው አንድ ዓመት እስራኤል ነዋሪዎችን መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ሰላማዊ ሰፈር እንዲሄዱ ትመክር ነበር። ሰላማዊ የሚባል መሸሸጊያ ግን በመላው ጋዛ የለም።
ዩኒሴፍ እንደሚለው 1 ሚሊዮን ሕዝብ በ48 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ቦታ እንዲዘዋወር ነው የተነገረው። ይህ ማለት 35 ሺህ ሰዎች በአንድ ስኬዌር ኪሎ ሜትር ይኖራሉ ማለት ነው።
“11 ጊዜ ተፈናቅያለሁ” ንጁድ
የ31 ዓመቷ ንጁድ በጋዛ ከተፈናቀሉ 1.9 ሚሊዮን ነዋሪዎች አንዷ ናት።
ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ እሷ እና አራት ልጆቿ የእስራኤልን ትዕዛዝ በመከተል 11 ጊዜ ከቦታ ቦታ ቀያይረዋል።
በሽታን ፍርሃት፣ የሚሳዔል ጥቃትንሽሽት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጠባብ ቦታ ለመኖር በመቸገር ቦታ ለዋውጠዋል።
አሁን በአልማዋሲ በረሃ ድንኳን ውስጥ ልጆቿን ይዛ ትኖራለች። ይህ ቦታ መጀመሪያ በእስራኤል ‘ሰላማዊ ሰፈር’ ተብሎ ነበር። ያም ሆኖ የሚሳዔል ጥቃት አልቀረለትም።
እንደ ብዙዎቹ ተፈናቃዮች እሷ እና ልጆቿ ከጦርነቱ በኋላ የሚመለሱበት ቤትም፣ ቦታም መጠለያም ምንም የላቸውም።
“70% ቤቶች ፈርሰዋል - መልሶ ለመገንባት 15 ዓመት ያስፈልጋል”
የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ በጋዛ 70 በመቶ የሚሆነው ቤት በጦርነቱ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሯል።
በመጀመርያዎቹ ስድስት ቀናት ብቻ የእስራኤል አየር ኃይል 6 ሺህ ቦምቦችን በጋዛ ላይ ጥሏል።
የእስራኤል ጥቃት ከሰሜን ጋዛ ጀምሮ ቀስ እያለ ወደ ራፋህ የግብፅ ድንበር የቀጠለ ነው። በሁሉም አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ነው ያደረሰው።
በሐምሌ 2024 የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ 40 ሚሊዮን ቶን ስብርባሪ እና ፍርስራሽ በጋዛ ተከምሯል።
ይህ ማለት እያንዳንዱ ስኬዌር ኪሎ ሜትር 115 ኪሎ ግራም በሚመዝን ፍርስራሽ ተሞልቷል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ፍርስራሹን ለማንሳት ብቻ 15 ዓመታት እና ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
ይህም በፍርስራሹ በርካታ ለጤና አደገኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በመኖራቸው ነው። ያልመከኑ ፈንጂዎችን መጥረግም ሌላ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።
የተባበሩተ መንግሥታት እንደሚለው ቤቶቹን እንኳን መልሶ ለመግንባት አቅም ቢገኝ የፈረሱትን ለመመለስ ቢያንስ እስከ 2040 ድረስ ጊዜ ይወስዳል።
“እናቴም አባቴም ታመውብኛል” አሲል
አሲል ወንድሟን በዚህ ጦርነት አጣች። እናቷ ካንሰር ታመዋል። ቤተሰቡ ወደ ውጭ ወስዶ ሊያሳክማቸው ቢፈልግም አልተቻለም።
አባቷ ኩላሊት ክፉኛ ታመዋል።
“አንዳንድ ቀን ተስፋ ስቆርጥ ለምን እንደምኖር ራሱ ግራ ነው የሚገባኝ” ትላለች።
ትንሽ ሻል በሚላት ቀናት ደግሞ ተስፋ ታደርጋለች። ታማሚዎቹ ወላጆቿ ከጋዛ ወጥተው ሕክምና እንዲያገኙ ትመኛለች።
እሷም ከጋዛ ወጥታ በቆጵሮስ ከሚኖረው እጮኛዋ ጋር አዲስ ሕይወት ለመጀመር ታልማለች።
አሲል ይህን ተስፋ በምታደርግበት ወቅት በጋዛ የተለኮሰው ጦርነት መካከለኛው ምሥራቅን በሙሉ እንዳይፈጅ እየተፈራ ነው።