ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሞቱ ወንድ ልጆቻቸው የዘር ፍሬ የልጅ ልጆችን ለማየት የሚጓጉት እስራኤላውያን ጥረት
የወንድ ልጆቻቸውን (አብዛኛዎቹ ወታደሮች ናቸው) ሞት የተረዱ በርካታ እስራኤላውያን ወላጆች የልጆቻቸው የዘር ፍሬ ወጥቶ ማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲቀመጥ እየጠየቁ ነው። ቁጥራቸው ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው።
በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ጥቃት ምክንያት በሂደቱ ላይ አንዳንድ ሕጎች እንዲላሉ ተደርገዋል። ወላጆች ግን በሚያጋጥሟቸው ረጅም የሕግ ሂደቶች ተበሳጭተው ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
በሚያዝያ ወር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በተካሄደ ጦርነት የ20 ዓመት ልጁ ሪፍ መገደሉን ያወቀው አቪ ሀሩሽ መርዶውን የሰማበትን አጋጣሚ ሲናገር አሁንም ድምጹ ይንቀጠቀጣል።
መርዶውን ይዘው የመጡት የጦር መኮንኖችም ሃሳብ አቀረቡለት። የሪፍን የዘር ፍሬ ለማውጣት ጊዜ ነበር። ቤተሰቡስ ፍላጎት ነበረውን?
የአቪ ምላሽ ፈጣን ነበር። ሪፍ “ሕይወቱ ሙሉ ነበር” ሲል ተናግሯል። “አስፈሪው የሕይወት ማለፍ ቢኖርም መኖርን እንመርጣለን።”
“ሪፍ ልጆችን ይወድ ነበር። የራሱም ልጆች እንዲኖሩት ይፈልግ ነበር። ይህ ምንም ጥያቄ የሌለው አቋሙ ነው” ሲል አክሎ ተናግሯል።
ሪፍ ሚስት ወይም የሴት ጓደኛ አልነበረውም። አቪ የልጁን ታሪክ መናገር ሲጀምር ግን ብዙ ሴቶች ብቅ እያሉ የሪፍን የዘር ፍሬ ተቀብለው ልጅ ለመውለድ ፍላጎት አሳዩ።
ይህ ሃሳብ “የሕይወቱ ተልዕኮ” ሆኗል።
ሐማስ መስከረም 26 እስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች ተገድለው 251 ሰዎች ታገተው ወደ ጋዛ ከተወሰዱ በኋላ እስራኤል በምላሹ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ከፍታለች።
በዚህም ከ39 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል። በጦርነቱ ወደ 400 የሚጠጉ እስራኤላውያንም ተገድለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የዘር ፍሬ አቀዝቅዘው የሚያስቀምጡ እስራኤላውያን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የሪፍ ቤተሰቦች አንዱ ናቸው።
የእስራኤል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ ከመስከረም 26 ጀምሮ ወደ 170 ከሚጠጉ ወጣቶች (ሲቪሎች እና ወታደሮች ናቸው) የወንድ ዘር ፍሬ ተሰብስቧል። ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ይህ አሃዝ በ15 እጥፍ ያህል ከፍ ያለ ነው።
ሂደቱ ከወንድ የመራቢያ አካል በቤተ ሙከራ የዘር ፍሬውን ለይቶ በማቀዝቀዣ ማኖር ነውን የሚያካትት ነው።
የዘር ፍሬዎች አንድ ሰው ከሞተ እስከ 72 ሰዓታት ድረስ ሊኖሩ ቢችሉም ግለሰቡ ከሞተ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከተከናወነ ሴሎቹን የማግኘቱ ስኬት ከፍተኛ ይሆናል።
የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጥቅምት ወር ሂደቱን ለማከናወን ወላጆች የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጣቸው የሚጠይቀውን መስፈርቱን አንስቷል። የአገሪቱ ጦር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልጆቻቸው የሞቱባቸው ወላጆችን ፍላጎት ለማሟላት የበለጠ እየሠራሁ ነው ብሏል።
የወንድ የዘር ፍሬን ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ ቀላል እየሆነ መጥቷል። ባሎቻቸው የሞቱ ሚስቶች ወይም ወላጆች የወንድ የዘር ፍሬውን ጽንስ ለመፍጠር ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ ግን ፍርድ ቤት ሄደው ሟቾች ልጅ የመውለድ ፍላጎት እንደነበራቸው ማሳመን አለባቸው። በተለይም ልጆቻቸውን በሞት ላጡ ወላጆች ሂደቱ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።
በእስራኤል ውስጥ የሞተ የልጃቸውን የወንድ የዘር ፍሬ ለመጠበቅ እና ለመጠቀም የቻሉት የመጀመሪያዎቹ ወላጆች ራቸል እና ያኮቭ ኮኸን ናቸው። ልጃቸው ኬይቫን እአአ በ2002 ጋዛ ሰርጥ ውስጥ በፍልስጤማዊ አልሞ ተኳሽ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን የአገሪቱ ጦር አስታውቋል።
በዘር ፍሬው የተወለደችው የልጅ ልጃቸው ኦሸር አሁን 10 ዓመት ሆኗታል።
ኬይቫን ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መልሳ እንዳገኘቸው ያህል እንደተሰማት ራቸል ገልጻለች። “ወደ ክፍሉ ሄጄ ነበር። የእሱን ጠረን ለማግኘት ፈለግኩኝ። ጫማውን ጭምር አሸተትኩኝ” ትላለች።
“ፎቶው ላይ ሆኖ አነጋገረኝ። ልጆች እንዳሉት እንዳረጋግጥ ጠየቀኝ።”
ራቸል “በጣም ተቃውሞ ገጥሟቸው” እንደነበር ተናግራለች። በመጨረሻ ላይ ግን ለውጥ ያመጣ የሕግ ውሳኔ እንዳገኘች ተናግራለች። ቀጥሎ ለልጇ ልጅ እናት ልትሆን የምትችል እናት ለማግኘት ማስታወቂያ አወጣች።
ማንነቷ እንዳይታወቅ አይሪት በሚል ስም ብቻ መጠራት የፈለገች ግለሰብ ለማስታወቂያው ምላሽ ከሰጡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች መካከል ናት።
ትዳርም ሆነ ጓደኛ አልነበራትም። በሥነ-ልቦና ባለሙያ እና በማኅበራዊ ሠራተኛ እንደተገመገመች ትናገራለች። በኋላም በፍርድ ቤት ፍቃድ የወሊድ ህክምናዋን እንደጀመረች ትናገራለች።
“አንዳንዶች ከፈጣሪ ጋር ትግል እንደገጠምን ይገልጻሉ። እኔ ግን እንደዚያ አይመስለኝም” ትላለች።
“አባታቸውን በሚያውቁ ልጆች እና በዘር ባንክ ልገሳ በተጸነሱ ልጆች መካከል ልዩነት አለ” ስትል ተናግራለች።
ኦሸር አባቷ በሠራዊቱ ውስጥ ሲያገለግል እንደተገደለ ታውቃለች። ክፍሏ በዶልፊኖች አጊጧል። አባቷ ዶልፊኖቿን እንደሚወድ ታምናለች።
“የወንድ የዘር ፍሬውን ወስደው ድንቅ የሆነች እናት ፈልገው መወለዴን አውቃለሁ” ስትል አክላ ተናግራለች።
ኦሸር አያቶች፣ አጎቶች እና የአጎት ልጆች አሏት ብላለች አይሪት።
በሻሚር ሜዲካል ሴንተር የወንድ የዘር ፍሬ ባንክ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ኢታይ ጋት ለሟች ቤተሰቦች “የወንድ የዘር ፍሬን መጠበቅ ትልቅ ትርጉም አለው” ብሏል።
“ይህ ዘርን የማስቀጠል ምርጫን ለመጠበቅ የመጨረሻው ዕድል ነው” ይላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሂደቱ “ትልቅ የባህል ለውጥ” እያገኘ ነው ሲል ተናግሯል። አሁን ያሉት ደንቦች ግን የፍቅር ጓደኛ ወይም ትዳር የሌላቸው ወንዶች ጉዳይ ላይ ግጭትን ፈጥረዋል።
ዶ/ር ጋት እንደሚሉት ከሆነ ብዙውን ጊዜ ግልጽ የሆነ የስምምነት መረጃ የለም። ይህ ደግሞ ቤተሰቦች የዘር ፍሬው ከቀዘቀዘ በኋላ ሊጠቀሙበት እንዳይችሉ የሚያደርግ “በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ” ውስጥ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
“ልጅ ስለማዋለድ እየተወያየን ነው... ያለ አባት የሚያድጉ መሆናቸውን እናውቃለን” ሲልም ተናግሯል።
አብዛኛውን ጊዜም ሟች አባት የልጁን እናት አያውቅም። ትምህርቱ እና የወደፊት ዕጣቸውን ጨምሮ ሌሎች የልጆቹ ሁሉም ውሳኔዎች እናትየው ላይ ያርፋል።
ቀደም ሲል ከሟቹ ግልጽ ፍቃድ ከሌለ በስተቀር የዘር ፍሬን መጠበቅ ላይ ተቃውሞ ነበረው። አሁን ባለው ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ካገኘ በኋላ ግን አመለካከቱ እየተቀየረ ነው።
“ለእነርሱ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው እና አንዳንድ ጊዜም እንዴት እንደሚያጽናናቸው አይቻለሁ” ብሏል።
በቴል አቪቭ የሚገኘውን ዞሃር የአይሁድ ማዕከልን የሚመራው ታዋቂው ራባይ ዩቫል ሼርሎ የሟቹ ፈቃድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ብሏል።
በአይሁድ ሕግ ውስጥ ያሉ ሁለት አስፈላጊ መርኆች እንደሚካተቱም ገልጿል። እነዚህም የሰውን የዘር ሐረግ ማስቀጠል እና የሞተ ሰውን ሙሉ አካል መቅበር ናቸው።
አንዳንድ ራባዮች የዘር ሐረግ መቀጠል በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የዘር ፍሬውን ለማግኘት በሰውነት የሚደርሰው ጉዳት ተገቢ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በጭራሽ መከናወን የለበትም ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ አሁን ያሉት ደንቦች በ2003 በአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወጡት መመሪያዎች ናቸው። እስካሁን ግን በሕግ የተደነገጉ አይደሉም።
የእስራኤል ሕግ አውጪዎች የበለጠ ግልጽ ሕግጋትን ለማውጣት ረቂቅ ሕግ ለማዘጋጀት ቢሞክሩም እስካሁን በጅምር ላይ ነው የቀረው።
ለሂደቱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሟች ሊጠየቅ የሚገባው ግልጽ ፍቃድ እና ሕጻናቱ በግዳጅ ላይ ለተገደሉት ወታደሮች ልጆች የሚሰጠውን ጥቅማጥቅም አያገኝም የሚለው ላይ ግጭት ተፈጥሯል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ባሎቻቸውን በሞት ባጡ ሚስቶች እና በሟች ወላጆች መካከል የዘር ፍሬውን ምን ያህል የመቆጣጠር ሥልጣን አላቸው በሚለው ላይ አለመግባባት መፈጠሩን ዘግበዋል።
ለአቪ ሐዘኑ ውስጥ ሆኖም ቁርጠኝነት አለ።
በልጁ ማስታወሻዎች፣ አልበሞች እና ትውስታዎች የተሞላ የልጁን ትዝታዎችን ይመለከታል።
ለሪፍ ልጅ እስኪያገኝ ድረስ እረፍት እንደማያገኝ ተናግሯል። “አምናለሁ…ልጆቹ ይህንን ሳጥን መጥተው ይቀበላሉ” ብሏል።