ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፉት 10 ወራት በእስራኤል የተገደሉ 4 ቁልፍ የሐማስ አዛዦች እነማን ናቸው? እንዴት ተገደሉ?
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ ገብቶ የፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ክፉኛ ያስቆጣ ነበር። በሐማስ ጥቃት 1200 ያህል ሰዎች ሲገደሉ ከ150 በላይ ሰዎች ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
ሐማስ ለወትሮ ከጋዛ ሮኬቶችን በማስወንጨፍ እስራኤልን ሲያስደነግጣት ቆይቷል። ዕድሉን ሲያገኝ ደግሞ ወታደሮቿን ድንገት ሲያጠቃ እና ሲገድል ነበር።
ነገር ግን በመስከረም መጨረሻ ላይ የፈጸመው የተቀናጀ ጥቃት ለእስራኤል ዱብ ዕዳ ነበር። ለዚህም ነው እስራኤል የሐማስ መሪዎችን እና ተዋጊዎቹን ከጋዛ ለመጠራረግ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተችው።
በዚህም በችግር ተቆራምዶ በእርዳታ የሚኖረውን የጋዛ ነዋሪ በውስጡ ከተሰማሩት የሐማስ አባላት ሳትለይ እስራኤል እያካሄደችው ባለው የምድር እና የአየር ዘመቻ በአስር ሺዎች አልቀዋል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው እስራኤል በግዛቲቱ ውስጥ ባለፉት 10 ወራት የገደለቻቸው ሰዎች ወደ 40 ሺህ ተጠግተዋል። ከእነዚህ ሁሉ የአራቱ ነፍሶች ለእስራኤል ልዩ ድል የሚባሉ ናቸው።
ከአራቱ ሁለቱ ሕይወታቸውን ያጡት ከጋዛ ውጭ ነው።
ሞሳድ እግር በእግር እየተከታተለ የእስራኤል ጠላት የሚላቸውን ያድናል።
ኔታንያሁ በቅርቡ እንዳመኑት፣ ሞሳድ ለሚባለው የውጭ የስለላ ድርጅታቸው አንድ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። “የትኛውም የሐማስ ከፍተኛ አመራር፣ ማንም ይሁን ማን፣ በተገኘበት ይገደል” የሚል።
ሞሳድ ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል። ኢስማኤል ሃኒያን በባላንጣዋ ኢራን ዋና ከተማ በቴህራን ውስጥ በልዩ ጥንቃቄ እንዲገደል ያደረገው ሞሳድ እንደሆነ ይታመናል።
እስራኤል ግን በሉዓላዊቷ አገር ግዛት ውስጥ ስለተፈጸመው የኢስማኤል ሃኒያ ግድያ እንደወትሮዋ “የእምነትም ሆነ የክህደት” ቃሏን አልሰጠችም።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ ባለፉት አስር ወራት ከሃኒያ በተጨማሪ ሦስት የሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጦር መሪዎች እንደወጡ ቀርተዋል።
ለመሆኑ አራቱ የሐማስ ቁልፍ ሰዎች እነማን ናቸው? እንዴትስ ተገደሉ?
ኢብራሒም ባያሪ
ስም፡ ኢብራሒም ባያሪ
የተገደለበት ቀን፡ ጥቅምት 20/2016ዓ.ም.
ኃላፊነት፡ የሐማስ ኮማንደር
ዕድሜ፡ አይታወቅም
ዕለቱ ማክሰኞ ነበር። የእስራኤል አየር ኃይል ሰሜናዊ ጋዛን ደበደበ። በጃባሊያ መጠለያ ጣቢያ ብዙ ሺህ ፍልስጤማውያን ተጠልለዋል። የእስራኤል ጥቃት ግን ኢብራሒም ባያሪ ላይ ያነጣጠረ ነበር።
እሱን ለመግደል የመቶዎች ሕይወት ተቀጠፈ። ሕጻናት ይበዛሉ።
ዓለም ተቆጣ፤ እስራኤል ግን አስተባበለች።
በርካታ የሐማስ አሸባሪዎች ተኮልኩለው ስለነበረ ነው መጠለያውን በቦምብ የደበደብኩት አለች።
ሐማስ በበኩሉ በዚያን ወቅት እንዲያውም ኢብራሒም ባያሪ በጭራሽ እዚያ ቦታ አልነበረም ይላል።
ኢብራሒም ባያሪ መስከረም 26 በሐማስ የተፈጸመውን መብረቃዊ ጥቃት ያቀነባበረው ኮማንደር ሳይሆን አይቀርም።
የጃባሊያ ባታሊዮን መሪ ነበር። ከአስር ዓመት በፊት በአሽዶድ ወደብ ለ13 እስራኤላውያን ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ያቀነባበረውም እሱ ነው ይባላል።
ሳሊህ አልአሩሪ
ሙሉ ስም፡ ሳሊህ አልአሩሪ
የተገደለበት ቀን፡ ታኅሣሥ 15/2016 ዓ.ም.
ኃላፊነት፡ የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ ምክትል
ዕድሜ፡ 57
አልአሩሪ በሐማስ የሥልጣን እርከን ከፍተኛ የሚባል ቦታ ያለው ሰው ነበር። በፖለቲካም በወታደራዊም ዘርፍ አንቱ የሚባል ነበር።
በሟቹ ኢስማኤል ሃኒያ የሚመራ የነበረው የሐማስ ፖለቲካ ቢሮ ምክትል ነበር። ኢዘዲን አል ቃሲም ብርጌድ የሚባለውን የሐማስ መቺ ወታደራዊ ክንፍ ከፈጠሩት አንዱ ነው።
አልአሩሪ የሚኖረው ሊባኖስ ዋና ከተማ በቤይሩት ነበር። ከሞሳድ ዕይታ ግን አላመለጠም። ከቤይሩት ወጣ ብላ በምትገኘው ዳሂያ በምትባል ቦታ በተጠመደ ቦምብ ተገደለ።
አሩሪ ሐማስን የተቀላቀለው በ1987 (እአአ) ሲሆን፣ በዌስት ባንክ የሐማስ አደራጅ ነበር። በሐማስ እና በሒዝቦላህ መካከል እንደ ድልድይ ያገለገለው ሳሊህ አሩሪ መገደሉ ለሐማስ መጥፎ ዜና ነው።
ሳሊህ አልአሩሪ እንደ ብዙዎቹ የሐማስ አባላት በእስራኤል እስር ቤቶች ፍዳውን በልቷል።
ከተለቀቀ በኋላ ጊላድ ሻሊት የተባለ የእስራኤል ወታደር እንዲታገት በማድረግ ወታደሩን በአንድ ሺህ ፍልስጤማውያን መንዝሮ አስፈትቷል። ከእስራኤል ጋር የተደረገውን ድርድር የመራውም ራሱ ነበር።
እስራኤል በሐማስ መብረቃዊ ጥቃት ከተፈጸመባት ከ20 ቀናት በኋላ በዌስት ባንክ የሳሊህ አል አሩሪን መኖርያ ቤት አውድማለች። ወር ቆይታ ደግሞ በቤትይሩት እሱን አገኘችው።
መሐመድ ዴይፍ
ስም፡ መሐመድ ዴይፍ
የተገደለበት ቀን፡ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም.
ኃላፊነት፡ የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ
ዕድሜ፡ አይታወቅም
መሐመድ ዴይፍን ለመግደል እስራኤል ብዙ ለፍታለች።
ከገደለችው በኋላም ስለመሞቱ እርግጠኛ መሆን የቻለችው ከሳምንታት በኋላ ነው።
መሐመድ ዴይፍ የተገደለው በሐማሌ ወር መጀመሪያ ሳምንት በጋዛ ሰርጥ፣ በኻን ዩኑስ ሰፈር በአየር ጥቃት ነው።
መሐመድ ዳይፍ የመስከረም 26ቱን ጥቃት ካቀነባበሩት እና ከመሩት የሐማስ ወታደራዊ አዛዦች አንዱ ነበር ትላለች እስራኤል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የዴይፍ መገደል ሐማስን ለማጥፋት ‘ወሳኝ እርምጃ’ ነው ማለታቸው የሰውየውን አቅም የሚያሳይ ነው።
ድርጅቱ ሐማስ ገና የዴይፍን ሞት በይፋ አላመነም።
እዚህ ሞተ ሲባል እዚያ ብቅ የሚለው መሐመድ ዴይፍ ምናልባት በሕይወት ካለ ሐማስን ጨርሶ ማጥፋት እንደማይቻል ማሳያ ይሆን ይሆናል።
ወይም ደግሞ እስራኤል እንደምትለው እስከወዲያኛው አሸልቧል።
ኢስማኤል ሃኒያ
ስም፡ ኢስማኤል ሃኒያ
የተገደለበት ቀን፡ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም.
ኃላፊነት፡ የሐማስ የፖለቲካ መሪ
ዕድሜ፡ 62
ኢራን ውስጥ የተገለደው ኢስማኤል ሃኒያ ከእስራኤል የደኅንነት ሰዎች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብሎ ሐማስን ወክሎ የሚደራደር ጎምቱ የፖለቲካ ሰው ነበር።
ከቅርብ ዓመታት በፊት ኑሮውን በኳታር ቢያደርግም ተደጋጋሚ ጉዞዎችን ወደ ኢስታንቡል፣ ካይሮ እና ቴህራን አድርጓል።
ሃኒያ እንደ ሁለተኛ ቤቱ የሚቆጥራት ቴህራን የተጓዘው ለአዲሱ የኢራን ኦእሬዝዳንት በዓለ ሲመት ነበር። መንፈሳዊውን መሪም በዚያ አግኝቷቸዋል።
የአዲሱን የኢራን ፕሬዝዳንት መስኡድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ታድሞ ወደተዘጋጀለት ማረፊያ አመራ።
የእሱ ማረፊያ ቤት ሁልጊዜም ትታወቃለች። ከዚህ ቀደምም ወደ ቴህራን ሲሄድ እዚያ ነበር የሚያርፈው። ጥበቃው ጥብቅ ነው። አብረውት ሦስት የሐማስ መሪዎች ነበሩ። እነሱን የሚጠብቁ ብዙ ዘቦች ተኮልኩለው ነበር።
ሞሳድ እንዴት ሾልኮ ሊገድለው ቻለ የሚለው እስካሁን ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ።
መጀመሪያ ላይ ከድሮን ላይ የተወነጨፈ ሚሳኤል በቀጥታ ሃኒያ ያረፉበትን ክፍል መትቶ ለህልፈት አብቅቶታል ቢባልም ሌላ መረጃም እየወጣ ነው።
አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሞሳድ ሃኒያ የት ክፍል ሊያርፍ እንደሚችል መረጃ ነበረው። ተቀጣጣይ ቦምብ ወደዚህ የእንግዳ ማረፊያ በድብቅ እንዲገባ የተደረገው ቀደም ብሎ ነበር።
አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን እንደተናገሩት ይህ ቦምብ ከ2 ወራት በፊት ነው ቴህራን ወደሚገኘው የእንግዳ ማረፊያ በድብቅ እንዲገባ የተደረገው።
እንግዳ ማረፊያው ባለቤትነቱ የኢራን ሪፐብሊካን ዘብ ጓድ ነው። የሚገኘው በቴህራን ውድ በሆነው ነሻት በሚባል ሰፈር ነው።
ሃኒያ ወደዚህ ማረፊያ እንደተመለሱ በድብቅ የገባው ፈንጂ ከርቀት እንዲፈነዳ ተደረገ። ፍንዳታው የኢስማኤል ሃኒያን አንድ ጠባቂ ሕይወትም አጥፍቷል።
እስራኤል ዛሬም ድረስ በጉዳዩ ላይ አንደበቷ እንተለጎመ ነው። አጋሯ አሜሪካም በግድያው ላይ መረጃ እንደሌላት ነው የምትገልጸው።
ይህ ግን የመካከለኛው ምሥራቅን ፖለቲካ ለሚከታተል ሰው የማይመስል ነገር ነው። እስራኤል የአሜሪካንን ቡራኬ ሳታገኝ ኢስማኤል ሃኒያን ልትገድል የምትችልበት ዕድል ጠባብ ነው።
እስራኤል እስካሁን የሐማስ አራት ቁልፍ ኮማንደሮችን እስትንፋስ አቁማለች።
የሐማስን እስትንፋስ ማቆም ትችላለች ወይ የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው።