እስራኤል በቤይሩት ከፍተኛ ፍንዳታን ያስከተለ ከባድ ጥቃት ሰነዘረች

እስራኤል ከፍተኛ መጠን ያላቸው 11 ቦምቦችን በመጠቀም ቤይሩትን ደበደበች። ይህ ጥቃት የተሰነዘረው ዐርብ ሊነጋጋ ሲል ነው። ፍንዳታው ከፍተኛ ነበር ተብሏል።

ፍንዳታው የተከሰተው ከቤይሩት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብዙም ሳይርቅ ነው።

እስራኤል ኢላማ ያደረገችው ምን እንደሆነ ባይገለጽም የሊባኖስ ሚዲያዎች ግን የሐሰን ነስረላህ ምክትሎ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁትን ሰው መሸሸጊያ ምሽግ ለመምታት የተሰነዘረ ነበር ሲሉ ዘግበዋል።

የእስራኤል ሚዲያዎችም በተመሳሳይ የነስረላህ ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉትን ሐሺም ሰይፉዲንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ነበር ብለዋል።

ሐሺም ነስረዲን በዚህ ጥቃት ስለመገደላቸው ከእሰራኤልም ሆነ ከሔዝቦላህ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።

ሐሺም ሰይፉዲን ከሔዝቦላህ መሥራቾች አንዱ ናቸው። በቅርቡ የተገደሉትን የሔዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህን ይተካሉ ተብሎ በስፋት ሲነገር ነበር።

የእስራኤል የዛሬ ማለዳው ጥቃት ከፍተኛ እንደነበር ተነግሯል። የተሰነዘሩት ቦምቦችም ምሽግን ሰንጥቀው መግባት የሚችሉ ነበሩ።

ጥቃት ከተሰነዘረበት ስፍራ አቅራቢያ የሚገኘው አየር ማረፊያው ዳሂህ የሚባለውን የሔዝቦላህን ይዞታ የሚጎራበት ነው።

በቤይሩት ንጋት ላይ የፍንዳታው ጭስ ከርቀት ይታይ እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ አቅጣጫ የሊባኖስ መንግሥት ሁለት ወታደሮቼ ድንበር ላይ ተገድለውብኛል ብሏል።

እስራኤል መጠነ ሰፊ ዘመቻ በሔዝቦላህ ላይ ለማድረግ ማቀዷን ተከትሎ ከድንበር አካባቢ በቅርብ ርቀት የሚገኙ 20 ከተሞች ነዋሪዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

የእስራኤል መከላከያ እንዳለው ወታደሮቹ በርካታ የሔዝቦላህ ተዋጊዎችን ገድለዋል።

ሔዝቦላህ በበኩሉ በሁለቱም ግንባሮች የእስራኤል ወታደሮችን እየተዋጋ እንደሆነ አስታውቋል።

እስራኤል ወደ ሊባኖስ እግረኛ ማስገባት ከጀመረች ዛሬ ሦስተኛ ቀኗ ነው።

የእስራኤል መከላከያ በነባቲህ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስቸኳይ ቦታውን ለቀው እንዲሰደዱ መክሯል። ከሊታኒ ወንዝ ሰሜን አቅጣጫ የሚገኙና ከድንበር በ30 ኪሎ ሜትር የሚርቁ ሁሉንም ነዋሪዎች የሚመለከት ነው።

በሊባኖስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ማቲው ሆሊግዎርዝ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ‘አስጨናቂ’ ሲሉ ገልጸውታል።

የዛሬ ማለዳው የቤይሩት ፍንዳታ እስራኤል በዋና ከተማዋ አንድን ሕንጻ በቦምብ ካወደመች ከ24 ሰዓት በኋላ የሆነ ነው።

ከሐዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ምግባረ ሰናይ ኤጀንሲ በአደጋው ነፍስ ለማዳን በአካባቢው ከደረሱ ሠራተኞቹ ዘጠኙ ተገድለውብኛል ብሏል።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ደግሞ 40 የእሳት አደጋ እና የአደጋ መከላከል ሠራተኞች በሦስት ቀናቱ የእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

የእስራኤል አየር ኃይል ሐሙስ ኢላማ ያደረገው የሔዝቦኣለህ የደኅንነት ዋና ሥሪያ ቤትን እና የመሣሪያ ማምረቻና ማከማቻ ግምጃ ቤትን ነበር።

ባለፉት ሁለት ሳምንታ የእስራኤል ጥቃት 1300 ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።