ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱጃሩ ኢላን መስክ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተጠርቷል፤ ይገኝ ይሆን?
የአሜሪካ ፌዴራል ፍርድ ቤት ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ሐሙስ ዕለት ችሎት ፊት እንዲቀርብ አዟል።
በቀድሞ ስሙ ትዊተር ቀጥሎ ደግሞ መስክ ባወጣለት ስም ኤክስ የሚታወቀው ማኅበራዊ ሚድያን በተመለከተ ነው ኢላን ችሎት ፊት እንዲቀርብ የታዘዘው።
ቢሊየነሩ ትዊተርን ሲገዛ አንዳንድ ስህተቶች ፈፅሟል በሚል ከጠበቆች የሚቀርብለትን ጥያቄ መመለስ ግድ ይሆንበታል።
አሁን የፋይናንሱ ዓለም እየጠየቀ ያለው አንድ ጥያቄ አለ። እውን መስክ ችሎት ፊት ይቀርባል?
ባለፈው ወር የአሜሪካ ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንግ ኮሚሽን ሎስ አንጀለስ ግዛት የሚገኝ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቢያዘውም አሻፈረኝ በሚል ሳይገኝ ቀርቷል።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ቢሊየነሩ መስክ ከ44 ቢሊዮን ዶላር በላይ አፍስሶ ትዊተርን የሸመተው በአውሮፓውያኑ 2022 ነው።
መስክ ይህን በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉትን የማኅበራዊ ሚድያ ትስስር መድረከረ ለመግዛት በሚል አክሲዮን ሲያጠራቅም ከርሟል ወይ የሚል ምርመራ ተከፍቶበታል።
መስክ ከዚህ ቀደም ትዊተርን እገዛለሁ፣ ዘግይቼ የገዛሁት በስህተት ነው እንጂ አውቄ አይደለም ብሎ ነበር።
የአሜሪካ የአክሲዮን ገበያን የሚቆጣጠረው መሥሪያ ቤት ቢሊየነሩ ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት ካልቀረበ ቅጣት እጥለበታለሁ ሲል ዝቷል።
መሥሪያ ቤቱ እንደሚለው ባለፈው ወር ኢላን መስክ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥያቄዎችን ይመልሳል በሚል ለሦስት ጠበቃዎች በሺዎች የሚቆጠር ዶላር መድቦ ነበር።
ነገር ግን ቀጠሮው ሊደርስ ሦስት ሰዓታት ሲቀሩት የመስክ ጠበቆች ደንበኛቸው መገኘት እንደማይችል አሳወቁ።
ጠበቆቹ እንደ ምክንያት ያቀረቡት መስክ ስፔኤክስ የተባለ የጠፈር ምርምር ተቋሙ ለሚያስወንጭፈው መንኩራኩር ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ተጉዟል የሚል ነው።
መንግሥት የቀጠራቸው ለመስክ ጥያቄ ያቀርባሉ የተባሉት ጠበቆች በቢሊየነሩ ድርጊት ደስተኛ አይደሉም። ሕግ አዋቂዎቹ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት መስክን አስገድዶ እንዲያቀርበው ጠይቀዋል።
ኢላን 44 ቢሊዮን ዶላር አውጥቶ ትዊተርን ሙሉ በሙሉ ከመግዛቱ በፊት በርካታ አክሲዮኖች ሲሸምት ነበር። ይህ ደግሞ የአክሲዮን ገበያ ሕግን የሚጥስ ነው ይላሉ ጠበቆች።
የኤክስ ባለቤት ሁለት ጊዜ ቃሉን ሰጥቷል። የእሱ ጠበቆች እንደሚሉት ለሦስተኛ ጊዜ ቃሉን እንዲሰጥ መጠየቁ አስፈላጊ አይደለም።
ነገር ግን ዛሬ ችሎት ፊት ሳይቀርብ ከቀረ ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል። ቀጠሮ እንዲቀየርለት ከፈለገ ደግሞ አስቀድሞ ማሳወቅ ነበረበት።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታሙ ሰው ኢላን መስክ በኤክስ ገፁ ሐሳቡን ያለመታከት በመግለፅ ይታወቃል።
ብሉምበርግ እንደሚለው የኢላን የተጣራ ሀብት 228 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል። አብዛኛው ገንዘቡ 13 በመቶ ድርሻ ካለው ቴስላ ከተባውለ ድርጅቱ የሚመዘዝ ነው።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ወደ ሲሊከን ቫሊ የቴክኖሎጂ ዓለም የመጣው የ53 ዓመቱ ባለሀብት የተወለደው በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ ነው።
መስክ ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው የኮምፒውተር ጌም የሠራው።