ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሐሳን ናስራላህ መገደል በኋላ ሄዝቦላህ ሕይወት ይኖረዋል?
የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል ሊገደሉ እንደሚችሉ ከድሮም ስጋት ነበር። በዚህ የተነሳ ይፋዊ አድራሻ አልነበራቸውም።
ለዓመታት ተደብቀው ነው የኖሩት። ለደጋፊዎቻቸው በቴሌቪዥን የሚቀርብ ንግግር ሲያደርጉም ካልታወቀ ስፍራ ነበር።
ናስራላህ በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቅ ተጽእኖ የነበራቸው መሪ ነበሩ።
የእርሳቸው መገደል ለእስራኤል ትልቅ ድል ነው። የደጋፊዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ቤይሩት ነዋሪዎች በክስተቱ ከፍተኛ ስጋት እና ድንጋጤ ውስጥ ገብተዋል።
አገራቸው ወደለየለት ጦርነት ትገባ ይሆን የሚለው እንቅልፍ የሚነሳ ነው።
እስራኤል ከሐሳን ናስራላህ ግድያ በኋላም አላረፈችም። ተከታታይ ጥቃቶችን ወደ ሌባኖስ እየሰነዘረች ነው። ሄዝቦላህም በሐዘን ተኮራምቶ ዝም አላለም። ብዙም ጉዳት ባያደርሱም ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ቀጥሎበታል።
አሁን ሁሉም እያነሳ ያለው አንድ ጥያቄ ነው። ሄዝቦላህ ከዚህ ወዲያ ተስፋ አለው?
ሄዝቦላህ ዕድሜ ዘመኑን በኢራን ነው ሲደገፍ የኖረው። በርካታ ምዕራባውያን አገራት በአሸባሪ ድርጅትነት ፈርጀውታል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምም ድርጅቱን በአሸባሪነት ነው የሚያውቁት። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ አረብ አገራትም ሄዝቦላህ አሸባሪ ብለው ነው የጻፉት።
የናስራላህ መገደል ድርጅቱን ሊያከስመው እንደሚችል የሚገምቱ አሉ። ድርጀቱ ካለም ከዚህ ወዲያ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ሊኮሰምን ይችላል።
ከአሁን በኋላ ዋነኛ ጠላቱ አድርጎ በሚመለከታት በእስራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚችል አደገኛ ቡድን ሆኖ የመቀጠል ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።
“የናስራላህ መገደል ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የሚኖረውን አቋም አይቀይርም። በተለይ በጋዛ ያለው ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ" ይላል ኢብራሂም ባይራም።
ባይራም ‘አልናህር’ በተባለ የሊባኖስ ጋዜጣ የፖለቲካ ተንታኝ ነው። ለቢቢሲ አረብኛ በሰጠው አስተያየት የሐሳን ናስራላህ መገደል አንድ ነጠላ ክስተት እንጂ ሌላ አይደለም ብሏል።
እሱ እንደሚለው፣ “ከዚህ ወዲህ ድርጀቱ ናስራላህ በዘረጋው መንገድ ትግሉን ይቀጥላል።”
በሊባኖስ ውስጥ ስላለው ስሜት ሲጠየቅ፣ “የናስራላህ መገደል ተስፋ እና ደስታ የሰጣቸው እንዳሉት ሁሉ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገቡም በርካታ ናቸው።”
ይህ የሊባኖስ ጋዜጠኛ “ናስራላህ ቀድሞው ይህ ቀን እንደሚመጣ ያውቅ ነበር” ይላል። ሐሳን ናስራላህ ወደ መሪነት ከመምጣቱ በፊት የነበረው የሄዝቦላህ መሪ አባስ አልሙሳዊ ተመሳሳይ ዕጣ ነው የገጠመው።
ሙሳዊ ከሄዝቦላህ መሥራቾች አንዱ ነበር። በአውሮፓውያኑ 1992 በእስራኤል ተገደለ።
እስራኤል ሐሳን ናስራላህን ከገደለች በኋላ ሌላ ብዙ ወታደራዊ ድሎች እንደሚኖሩ ጠቁማለች።
ኢራን እና ሄዝቦላህ
ዓርብ መስከረም 17/2017 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት የኢራን የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አመራርም ተገድሎባታል።
ከናስራላህ ግድያ ወዲህ ሸሸግ የተደረጉት አያቶላህ ኾሜኒ ለሄዝቦላህ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ ነገር ግን ኢራን የበቀል እርምጃዋ ምን ሊሆን እንደሚችል ያሉት ነገር የለም። ይህ የተመለደ ተግባር አይደለም።
መንፈሳዊው መሪ አያቶላህ እስራኤልን “አርቃ የማታስብ ጅላጅል አገር” ሲሉ ወርፈዋታል። ይህን ያሉት በተለይ በሊባኖስ ንጹሐን በጥቃቱ መገደላቸውን አስታከው ነው።
አያቶላህ በቅዳሜው ንግግራቸው የናስራላህን ስም ሳይጠቅሱ ማለፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ሆኖም “አጋሮቻችን” ያሏቸው ቡድኖችን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
አያቶላህ ኾሜኒ በዚህ ንግግራቸው በመላው ዓለም ያሉ ሙስሊሞች ለሊባኖስ ሕዝብ እና ለሄዝቦላህ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ምን ሊከሰት ይችላል?
ኢራን የናስራላህ ሞት የሚቀይረው ነገር የለም ትላለች። የአንድ መሪ ሞት ትግልን አይገድልም ባይ ናት።
“ሄዝቦላህ በርካታ መሪዎችን አሠልጥኗል፤ ለሰማዕት ሁልጊዜም ሌላ ተተኪ አለው” ይላል አህመድ ቫሂዲ።
ቫሂዲ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የቁዱስ ልዩ ብርጌድ የቀድሞ አዛዥ ነው።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን “የናስራላህ ሞት መካከለኛው ምሥራቅን ሰላማዊ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።
የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህን ሕጋዊ ቡድን አድርጎ ነው የሚመለከተው። አባላቱም በሊባኖስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ናቸው።
የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር እና ጋዜጠኛ የሆኑት መሐመድ አል ሞቃሊድ ይህ አጋጣሚ ሄዝቦላህ ለዘብ ያለ የፖለቲካ አቋም እንዲይዝ እና በአገር ውስጥ ፖለቲካ ላይ ያለው ተሳትፎው ላይ እንዲተኩር ሊያደርገው ይችላል ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት የናስራላህ መገደል ምናልባት ሄዝቦላህ በሊባኖስ የሚኖረውን የፖለቲካ ተሳትፎ አዲስ አቅጣጫ ሊያሲዘው ይችላል። ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲደረግም መንገድ ሊከፍት ይችላል።
ሞቃሊድ እንደሚገምቱት ምናልባት የናስራላህ መገደል በድርጅቱ ውስጥ ክፍፍል ሊፈጥርም ይችላል።
ወደፊት ትንንሽ ቡድኖች ተነጣጥለው የሽምቅ ውጊያ ሊጀምሩ እና ዋናው ቡድን ደግሞ የኢራንን አጋርነት ገሸሽ አድርጎ ትኩረቱን በሊባኖስ ፖለቲካ ላይ ብቻ ሊገድብ ይችላል።
ድንጋጤ እና ቁጣ
የናስራላህ መገደል በቤይሩት ከፍተኛ ድንጋጤ እና ቁጣን ፈጥሯል።
የተወሰኑ የሄዝቦላህ ደጋፊዎች አጋርነታቸውን ለማሳየት አደባባይ ወጥተዋል። ቁጣቸውንም፣ ሐዘናቸውን በአባባይ የገለጹ ብዙ ናቸው።
ሌሎች ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ የእስራኤል ጥቃት የፈጠረባቸውን ህመም አጋርተዋል።
የሄዝቦላህ ቴሌቪዥን “አል መናር” ከናስራላህ ግድያ በኋላ የቁርዓን ንባብ ሲያደርስ ነበር።
የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ነው ያሉት። ጎዳና የሚኖሩ ቤተሰቦች በሺህ ይቆጠራሉ። እስከ አሁን በጥቃቱ 800 ሰዎች ተገድለዋል።
ቢቢሲ ‘በአይን አልምራይሰህ’ አካባቢ የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያንን ስለ ናስራላህ መገደል አስተያየት በጠየቃቸው ጊዜ አንዳንዶች መሬት ላይ ሲንከባለሉ፣ ሌሎች ባለማመመን ሲያነቡ ነበር።
አንዲት ሴት “ሁላችንንም ገድለውን ናስራላህ ቢተርፍ እመርጥ ነበር” ብላለች።
ሐሳን ናስራላህ ለብዙ ደጋፊዎቹ አንድ የፖለቲካ መሪ ብቻ አይደለም። ከሕይወትም በላይ ነው።
በቤይሩት ሁሉም ዜጋ የሄዝቦላህ ደጋፊ ነው ማለት አይደለም። በእርሱ መገደል ደስተኛ የሆኑ እንዳሉ ግን አይዘነጋም።
በዚያው መጠን አደባባይ ወጥተው ያለቀሱ፣ ራሳቸውን የሳቱ ደጋፊዎቹም በቁጥር ቀላል አይደሉም።
ናስራላህን ማን ይተካቸዋል?
የሐሳን ናስራላህ መገደል በሄዝቦላህ ውስጥ የእርሳቸውን ጫማ ማን ይሞላዋል የሚል ጥያቄን ጭሯል።
ጋዜጠኛ ባይራም፣ “የናስራላህ ተተኪው ማንም ይሁን ማን፣ ፓርቲውን በመንፈስም በመዋቅርም አንድ ማድረግ አይችልም” ይላል።
የሄዝቦላህ ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐሺም ሳፊ አል ዲን ምናልባት ናስራላህን ሊተኩ ይችላሉ።
ጋዜጠኛው ባይራም እንደሚለው ለአራት ዐሥርታት የገዘፈ ስም እና ዝና እንዲሁም ቅቡልነት ያላቸውን ናስራላህን መተካት ቀላል ሊሆን አይችልም።
የሐሳን ናስራላህ ተተኪ የማግኘት እና የሄዝቦላህ በሊባኖስ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚኖረው ቀጣይ ዕጣን በሚመለከት የሚነሳውን ጥያቄ የበለጠ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቹ የመገደላቸው ነገር ነው።
በዓርብ ዕለቱ የእስራኤል ጥቃት የሄዝቦላህ መሪ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮቹ ጭምር መገደላቸውን እስራኤል እና ራሱ ድርጅቱ ያወጧቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
እስራኤል ቤይሩት ባለው የቡድኑ ዋና ጽህፈት ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት ከናስራላህ ጋር ሌሎች 20 በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮችን መግደሏን አስታውቃለች።
በዚህም የሄዝቦላህ ደቡባዊ ግንባር መሪ አሊ ካራኪ፣ የናስራላህ ደኅንነት ጥበቃ ቡድን መሪ ኢብራሂም ሁሴን ጃዚኒ፣ የናስራላህ የረጅም ጊዜ አማካሪ ሳሚር ታውፊቅ ዲብን ጨምሮ በርካታ የሄዝቦላህ አመራሮች መገደላቸው ተገልጿል።
እንዲሁም ሄዝቦላህ ራሱ እንዳሳወቀው የቡድኑ የመከላከያ ደኅንነት ምክር ቤት ቁልፍ አባል እና የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት ናቢል ቃውቅ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
ናስራላህ የሄዝቦላህን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ክንፍ በዕኩል ማስተሳሰር የቻሉ መሪ ነበሩ። ስለዚህም ቡድኑ የእሳቸውን ሚና በአግባቡ የሚወጣ መሪ ለማግኘት ረዥም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል እየተባለ ነው።
ሐሳን ናስራላህ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ ደግሞ በሊባኖስ ውስጥ ትተውት ያለፉት ውርስ እንደ ሕይወታቸው ውስብስ እና ለቀጣይ በርካታ ዓመታት እያከራከረ የሚቆይ ነው።
አሁን ዓለም የሚጠይቀው ቁልፍ ጥያቄ አንድ ነው። እሱም ሄዝቦላህ እንደ ፓርቲም እንደ ወታደራዊ ቡድንም የመቀጠል ተስፋ አለው ወይ? የሚል ነው።