የወዳጇ ሄዝቦላህ መሪ የተገደሉባት ኢራን የእስራኤል ጥቃት ከቀጠለ ዝም ብላ ታያለች?

ኢራን ትዕግስቷ በዝቷል። የኑክሌር ሳንቲስቶቿ በእስራኤል ተገድለውባታል፤ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ።

የሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ተገድለዋል።

አሁን ደግሞ አጋሯ ሄዝቦላህ ከፍተኛ ጥቃት እየተሰነዘረበት ሰንብቶ መሪው እና የቅርብ ወዳጇ የሆኑት ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

እነዚህ ሲደማመሩ ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ምክንያቶች ይመስላሉ - ለኢራን። ጦርነት ባይሆንም ተመጣጣኝ የበቀል እርምጃ በእስራኤል ላይ ለመውሰድ። ሆኖም ኢራን ለዘብ ብላለች። ወይም ደግሞ ለመወሰን ተቸግራለች።

በኢራን አክራሪ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ዜጎች በመንግሥታቸው ጨከን አለማለት (ወይም መልፈስፈስ ሊባል ይችላል) አዝነዋል።

አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ማክሰኞ፣ በኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ፣ እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከኮነኑ በኋላ በሊባኖስ የጀመረችው ተመሳሳይ ጥቃት በዋዛ እንደማይታለፍ ጠቆም አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንደ ቀደሞዎቹ የኢራን መሪዎች “እስራኤልን ከመካከለኛው ምሥራቅ እናጠፋለን” ዓይነት ዛቻ አልተጠቀሙም። ይልቅ ባልተመደ ሁኔታ በንግግራቸው ቁጥብ እና ለስላሳ ሆነዋል።

“ከሁሉም አገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን ነው የምንሻው፣ ከእስራኤልም ቢሆን” ብለዋል።

ከዚህም አልፈው መንግሥታቸው ከምዕራብ አገራት ጋር በተቋረጠው የኑክሌር ስምምነት ጉዳይ አዲስ ንግግር እንዲጀመር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ሌሎች የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዦች የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጥበቃ ኃላፊዎችን ጨምሮ ባልተለመደ ሁኔታ በእስራኤል ላይ ስለሚወሰደው የበቀል እርምጃ ሲናገሩ ቆጠብ እና ለዘብ ብለው ነበር።

ኢራን ሄዝቦላህን ከማስታጠቅ ጀምሮ ስንቅ እና ሥልጠናም ትሰጣለች። የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህን የሚያደርጉት ቡድኑ እስራኤል በቀጥታ ወደ ኢራን ልትሰነዝር የምትችለውን ጥቃት እንዲያመክን በመሻት ይመስላል።

ሄዝቦላህ ለኢራን ጋሻዋ እንዲሆን የተመሠረተ ይመስላል።

ሄዝቦላህ ከተመሠረተ ከ1980ዎቹ ወዲህ በዚህ ደረጃ ጥቃት ሲደርስበት ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ምናልባትም ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

ኢራን ለምን “ፖለቲካዊ ልምምጥን” መረጠች?

ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል የምትተኩሳቸው ድሮኖች እና ሚሳዔሎች፣ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ከኢራን የሚገኙ ናቸው።

አሜሪካ እንደምትለው ደግሞ በየዓመቱ ኢራን ለሄዝቦላህ 700 ሚሊዮን ዶላር ትለግሳለች።

ባለፈው ሳምንት በሊባኖስ የኢራን አምባሳደር ሞጅታብ አማኒ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህም የሆነው ፔጀር የተባለው ገመድ አልባ የመስክ ስልክ ፈንድቶባቸው ነው።

እስራኤል እንደፈጸመችው በሚገመተው በዚህ ጥቃት በድምሩ 39 ሰዎች ሞተዋል።

ኢራን ለድርጊቱ እስራኤልን ብትከስም “እበቀላለሁ” ግን አላለችም። ቢያንስ ይህን በይፋ አልተናገረችም።

ይሁን እንጂ እስራኤል በሚያዝያ ወር በደማስቆ የኢራን ቆንስላን በአየር ደብድባ 8 ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ስትገድል ኢራን በቸልታ አላለፈችውም።

መጀመሪያ ዛተች። ከዚያም ተበቀለች። በበቀል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እና ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል ተኩሳለች።

ኢራን ከዚህ ወዲያ የበቀል ዛቻ ያደረሰችው የሐማሱ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ በቴህራን ባለፈው ሐምሌ በተገደሉ ጊዜ ነው።

ይሁን እና ዛቻዋን እስከ ዛሬ ተግባራዊ አላደረገችም።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ኢራን ዝታ ነገር ግን ሳትተገብር መቅረቷ በተለይ በኢራን ጠጠር ያለ ፖለቲካ አቋም የሚያራምዱ ዜጎችን እያስቀየመ ይገኛል።

አገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ብቻም ሳይሆን በውጭ አገር የሚኖሩ የሄዝቦላህ ደጋፊዎችን፣ የየመን ሁቲዎችን ወዘተ ቅር የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል።

ባለፈው ሰኞ የኢራኑ ፕሬዝዳንት በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር እስራኤል ኢራንን “ሆን ብላ፣ ጎትታ ወደ ጦርነት ለማስገባት እየሞከረች ነው”' ሲሉ ከሰዋል።

“አገሬ ኢራን ግን ውጥረቱን ለማርገብ ትሻላች፤ እስራኤል ያን ለማድረግ ከፈቀደች” ብለዋል።

በኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኾሚኒ ዙርያ የሚገኙ ፖለቲከኞች ይህ ለዘብ ያለ የፕሬዝዳንታቸው ንግግር አላስደሰታቸውም።

ለዘብ ያሉ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን ቀጥታ ቃለ መጠይቆችን እንዳይሰጡም ግፊት እያደረጉባቸው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በኒውዮርክ ሊሰጡት የነበረው ቃለ ምልልስ የተሰረዘው በዚህ ነቀፌታ ይሁን አይሁን ለጊዜው አልታወቀም።

በኢራን ትልልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በመንፈሳዊው መሪ አሊ ኾሜኒ እና በአብዮታዊው ዘብ ነው። የፕሬዝዳንቱ ጉልበት በሦስተኛ ደረጃ የሚታይ ነው።

የሚገርመው ደግሞ መንፈሳዊው መሪ አያቶላህ አሊ ኾሜኒም ቢሆን በቅርቡ የአገሪቱን ቁልፍ ሰዎች ሲያነጋግሩ ስለ በቀል እርምጃ አለማንሳታቸው ነው። ይህ ያልተለመደ ነው።

ሁለት የምዕራብ አገር የፖለቲካ ተንታኞች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ሄዝቦላህ በዚህ ጦርነት ኢራን እገዛ እንድትሰጥ ጠይቋል።

ኢራን በበኩሏ “አሁን ያን ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ አይደለም” የሚል ምላሽ መስጠቷን የእስራኤል ዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ማይዳን የሚባል የኢንተርኔት ቲቪ አቅራቢ፤ ለኢራን ወታደራዊ ዘብ ቅርብ የሆነ ጋዜጠኛ ነው፤ እንደዘገበው እስራኤል በኢራን የጦር አዛዦች ላይ ልዩ ኦፕሬሽን በማድረግ የተወሰኑትን ገድላ ሰነዶችን ወስዳለች።

ኢራን ግን ይህን ዜና አፍና ደብቃለች ይላል።

ለኢራን ቅርብ የሆነው ተስሚን ዜና አገልግሎት በበኩሉ ይህ ዘገባ ሐሰት ነው ብሏል።

እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ሲታዩ ኢራን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች ይመስላል።

ኢራን እስራኤልን በዚህ ወቅት ከተተናኮሰች አካባቢው ወደለየለት ጦርነት መግባቱ አይቀርም።

የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ ያሰሯት ገመዶች ብዙ ናቸው።

አንደኛው ኢራን በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ ሰባብሯታል፤ ኢኮኖሚዋን አሽመድምዶታል።

ዜጎቿ ኑሮ ከብዷቸዋል። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ታዲያ ከእስራኤል ጋር ወደ ግጭት ከገባች የውስጥ አመጽ ተቀስቅሶ ቀውስ ሊከተል ይችላል።

የውስጥ አመጹ ደግሞ የፖለቲካ ለውጥ ሊያስከትል፤ የኾሜኒን አገዛዝም ሊገረስስ ይችላል።

ኢራን ዛቻዎቿ ዛቻ ብቻ ሆነው ከቀሩ ደግሞ እሱም ራሱን የቻለ ራስ ምታት ይዞ ይመጣል። ለምሳሌ እንደ ሁቲ እና ሄዝቦላህ በመሳሰሉ አጋሮቿ ዘንድ ትዝብት ላይ ይጥላታል።

ከእነርሱ ይልቅ ራሷን የምታስቀድም ራስ ወዳድ አገር አድርገው ይስሏታል። ሐቀኛ አጋር እንዳልሆነች ይገነዘቡም ይሆናል።

ይህ ደግሞ ኢራን በአካባቢው ያላትን ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸረሽረው ይሆናል።

በዚህም ሳቢያ ከሰሞኑ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ አንጻር ኢራን በከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ አጠብቂኝ ውስጥ ናት።