ትራምፕ በእሳቸው አመራር ሥር አሜሪካ "ወርቃማ ዘመን" ይጠብቃታል አሉ

ፕሬዝደንት ትራምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካ "ወርቃማ ዘመን" እንደሚጠብቃት ተናግረዋል።

ትራምፕ በካፒቶል ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ፣ የበዓለ ሲመት ድግስ ሲታደሙና ዋይት ሀውስ ከገቡ በኋላም ለአሜሪካ ያላቸውን ዕቅድ ሲናገሩ አምሽተዋል።

ያደረጓቸው አወዛጋቢ ንግግሮች ደጋፊዎቻቸውን ሲያስደስቱ ተቺዎቻቸውን አስቆጥተዋል። ዋነኛ ትኩረታቸው የስደተኞች ጉዳይና ምጣኔ ሃብት ነበር።

አሜሪካ በእጣ ሰዎችን ወደ ግዛቷ መቀበል እንደምታቆምና ዕውቅና ያላቸው ፆታዎች ሴት እና ወንድ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ትራምፕ በአስተዳደራቸው ስለሚኖረው ብሩህ ዘመን የተናገሩት የጆ ባይደን አስተዳደርን በማጥላላት ነበር።

ባይደንና ሌሎችም ዴሞክራቶች ትራምፕ ንግግር ሲያደርጉ ቆዝመው ታይተዋል።

ትራምፕ የቀድሞው አስተዳደር "በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል። የፍትሕ ሥርዓቱን በኢ-ፍትሐዊ መንገድ መሣሪያ አድርጓል" ብለዋል።

ከአሜሪካውያን ሃብት የሚበዘብዝ "ሙሰኛ ሥርዓትን" እንደሚያስወግዱ ተናግረዋል።

ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉት ንግግር ባለፉት ዓመታት ሲያደርጉ እንደነበረው የአብዛኛውን ሕዝብ ልብ የሚኮረኩርና የልሂቃንን ትርክት የሚገዳደር ነው።

ለትራምፕ ድጋፍ ለመስጠት ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና ቢልየነሮች በቦታው ተገኝተዋል።

በስደት፣ የኃይል አቅርቦት፣ ንግድ፣ ትምህርትና ሌሎችም ጉዳዮች አፋጣኝ ለውጥ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

በሜክሲኮ ድንበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ የአሜሪካን ወተደሮች ማሰማራት የሚችሉበት አሠራርን እንደሚተገብሩ ተናግረዋል።

ይህም የጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት የሚገድብ ነው።

ትራምፕ ኃይል ለማመንጨት የሚደረግ ቁፋሮ እንደሚቀጥል፣ ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ አካባቢ ገልፍ ኦፍ አሜሪካ እንደሚባልና ፓናማ ካናልን አሜሪካ እንደምትወስድ ተናግረዋል።

ቻይና በፓናማ ካናል ያለውን አካባቢ እየተቆጣጠረች እንደሆነ ባልተረጋገጠ መረጃ ተናግረዋል። የአሜሪካ መርከቦች በፓናማ ካናል ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ነውም ብለዋል።

"አሜሪካ ያደገች አገር ናት። ሃብታችንን አሁንም እንጨምራለን። ግዛታችንን እናስፋፋለን" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ትራምፕ ግሪንላንድን የመጠቅለልና ካናዳን የአሜሪካ 51ኛ ግዛት የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ሲናገሩም ተሰምቷል።

ትራምፕ ቃል የገቡት ብዙ ነው። "ወርቃማ ዘመን" ያሉት የአሜሪካ ገጽታ ምን አንደሚመስል ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

ጆ ባይደን ሥነ ሥርዓቱን ታድመው ከወጡ በኋላ ትራምፕ የ2020 ምርጫ እንደተጭበረበረና በካፒቶል ሂል ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ትራምፕ የዘንድሮውን ምርጫ በሰፊ ልዩነት እንዳሸነፉም ገልጸዋል።

ትራምፕ ኬክ ሲቆርሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ኬክ ሲቆርሱ

የባይደን አስተዳደር ሥር የተላለፉ ውሳኔዎችን በመከለስ አዳዲስ ሹመቶች ሰጥተዋል። ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትም አሜሪካን አስወጥተዋል።

"ጆ ባይደን ይሄን ሊያደርግ አይችልም" ብለዋል ትራምፕ።

የመንግሥት ሽግግር ተምሳሌት በሆነ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ትራምፕ "መንግሥትን እንደ መሣሪያ መጠቀምን" እንደሚያቆሙ ገልጸዋል።

ፊርማቸውን ያኖሩበትን እስኪርብቶ ለሕዝቡ አሻምተዋል።

ከዚያም ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ አቅንተው በካፒቶል ሂል ከተነሳው ነውጥ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ ከ1,600 በላይ ሰዎችን ይቅር ብለዋል።

አሜሪካ ውስጥ ለሚወለዱ የስደተኞች ልጆች ዜግነት መስጠት እንደሚቆም ትራምፕ አስታውቀዋል።

ሜክሲኮና ካናዳ ላይ 25% ቀረጥ እንደሚጣል ተናግረዋል።

ትራምፕ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል። አዳዲስ ፖሊሲዎቻቸው የሚተገበሩ ወይም በጊዜያዊነት ለደጋፊዎች የተባሉ ስለመሆናቸው በጊዜ ሒደት የሚታይ ይሆናል።