ነዳጅ ከመሸጫ ዋጋ በላይ የሚሸጡ ነጋዴዎችን እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ አዋጅ ጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነዳጅ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ የሚያደርግ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ።
በአዋጁ መሠረት ከመሸጫ ዋጋ በላይ በመሸጥ የሚፈጸም የመጀመሪያ ጥፋት ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል።
ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ የገንዘብ መቀጮው ላይ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚኖር አዋጁ ያትታል።
ይህን ቅጣት የያዘው እና "የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ" የወጣው አዋጅ፤ ሐሙስ ጥር 1/2017 ዓ.ም. በተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
አዋጁ ከሁለት የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ከአንድ የምክር ቤት አባል ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦ ገጥሞታል።
ባለፈው ሰኔ ወር ለምክር ቤቱ ቀርቦ የነበረው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከነዳጅ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚጣሉ የቅጣት ውሳኔዎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል።
በአዋጁ መሠረት "የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ" ማንኛውም ሰው፤ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል። ከዚህ በተጨማሪም የተያዘው የነዳጅ ውጤት እንደሚወረስ አዋጁ ያትታል።
የነዳጅ ምርቶችን "ሆን ብሎ" ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
ሌላው ለቅጣት የሚያስከትለው ድርጊት መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ የነዳጅ ምርቶችን መሸጥ ነው። ይህ ድርጊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጸም ቅጣቱ ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ሲሆን፣ ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት እስራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ያስቀጣል።
የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሰረውን መቁረጥ ወይም ልኬቱን ማዛባትም በተመሳሳይ ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ደንግጓል።
በአዋጁ መሠረት የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ማጓጓዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ስፍራ ውጪ ማራገፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ፤ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከ400 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር ያስቀጣል።
ከሚመለከተው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች መሸጥ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ጥፋት ነው።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣንን ወይም የሚመለከተውን አካል የቁጥጥር ሂደት መቃወም እና ማሰናከል ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ያስቀጣል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይህ የአዋጁ የቅጣት ድንጋጌ "በሥራ ላይ ካለው የወንጀል ሕግ ጋር እንዴት ይታያል?" የሚል ጥያቄ አንሰተዋል።
የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ "ቅጣቶቹ በጣም የተጋነኑ ሁነው ነው ያየኋቸው" ሲሉ ተደምጠዋል። ዶ/ር ደሳለኝ አክለውም "[አዋጁ] ቅጣት ላይ ብቻ ያተኮረ፤ ቅጣትን ማዕከል ያደረገ [ነው]" ብለዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፤ "ቅጣቱን በተመለከተ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ነው ያስቀመጥነው" ብለዋል።
"ቅጣቱ ከፍተኛ አይደለም" ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ "ነዳጁ ተሽጦ የሚገኘውን ትርፍ መጠን እና ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ስናይ እዚህ ላይ የተቀመጡት የገንዘብ ቅጣቶች በጣም ትንሽ ናቸው" ሲሉ መልሰዋል።
አዋጁ ከቅጣቱ በተጨማሪ "ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂፒኤስ የመግጠም ግዴታ አለበት" የሚል አዲስ ድንጋጌ ተካትቶበታል።













