በአይደር ሆስፒታል በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የሆድ እቃ ክፍተትን 'ቦቶክስ'ን በመጠቀም የተሳካ ቀዶ ሕክምና ተደረገ

በአይደር ሆስፒታል ሲወለድ እምብርቱ አካባቢ ትልቅ ክፍተት የነበረበትን እና የሆድ እቃዎቹ ወደ ውጭ ወጥተው የነበረውን ጨቅላ በአፍሪካ የመጀመርያው ነው በተባለ መንገድ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገለት ዶ/ር ይርጋለም ተክለብርሃን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በትግራይ ክልል መቀለ በሚገኘው አይደር ሆስፒታል በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ እንብርት አካባቢ የተፈጠረን ትልቅ ክፍተት ቦቶክስ (Botulinum toxin) በመጠቀም የሆድ እቃዎቹን የመመለስ የተሳካ ቀዶ ሕክምና መደረጉን ዶ/ር ይርጋለም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉት የሕጻናት ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ይርጋለም ተክለብርሃን የሆድ ግድግዳ ክፍተት ወይንም (omphalocele) በተፈጥሮ የሚከሰት መሆኑን ያስረዳሉ።

ኦምፋሎሴል (Omphalocele) የሕፃኑ የሆድ ዕቃ እንደ አንጀት፣ ጉበት ወይም ሌሎች የአካል ክፍሎች በእምብርቱ ሥር ባለው የሆድ ግድግዳ ቀዳዳ በኩል የሚወጣበት የወሊድ ችግር ነው።

ይህ ጉድለት በፅንሱ እድገት ወቅት የሆድ ግድግዳ ሙሉ በሙሉ በማይዘጋበት ጊዜ ይከሰታል።

ከእንብርት በታች የሚገኝ የሆድ እቃ ክፍል ግልጽ በሆነ በስስ ቆዳ ወይንም ከረጢት ተሸፍኖ የተለያዩ የውስጥ አካል ክፍሎች (አንጀት፣ ጉበት፣ የሽንት ፊኛ አልፎ አልፎ ጨጓራ) ወደ ውጭ ወጥቶ በግልጽ የሚታዩበት መሆኑን ዶ/ር ይርጋለም ጨምረው አብራርተዋል።

የሆድ እቃ ክፍተት አዲስ በሚወለዱ ጨቅላ ሕጻናት ላይ የሚከሰት ሲሆን በምዕራባውያን ጥናት መሠረት ከ5000 ሕጻናት መካከል አንዱ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊያጋጥም ይችላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ነፍሰጡር እናቶች የሚያደርጉት የእርግዝና ክትትል ዝቅተኛ በመሆኑ ይህ ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ዶ/ር ይርጋለም ተናግረዋል።

ቀዶ ሕክምናው የተደረገው ቦቱሊነም ቶክሲን (botulinum toxin) ወይንም በአጭሩ ቦቶክስ የተሰኘውን መድሃኒት በመጠቀም መሆኑን የተናገሩት የሕክምና ባለሙያው ይህ ደግሞ ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ቦቶክስ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ፊት ላይ የሚፈጠርን መሸብሸብ ለማስወገድ ስለሆነ ውድ መሆኑን የሕጻናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል።

በሌሎች ዓለማት አንዳንድ ጊዜ ከቀዶ ሕክምና በኋላ ትልቅ ክፍተት የሚኖር ከሆነ መድሃኒቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል የገለፁት ዶ/ር ይርጋለም፣ በጨቅላ ሕጻናት ላይ ደግሞ በመላው ዓለም ከአስር በታች የሆኑ ቀዶ ሕክምናዎች ይህንን መድሃኒት ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል።

"በአፍሪካ አገር እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት ቦቱሊነም ቶክሲን ተጠቅሞ ኦምፋልሲሌ [የሆድ ግድግዳ ክፍተት] መዘጋቱን የሚያሳይ ሪፖርት የለም።"

ዶ/ር ይርጋለም ጨቅላ ሕጻኑ ወደ ሕክምና ክፍላቸው ከመምጣቱ በፊት ከስዊዲን የመጡ ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ምክክር ወቅት ትልቅ የሆድ ግድግዳ ክፍተትን ለመዝጋት 'ቦቶክስ' ጥቅም ላይ እንደሚውል እና ውጤታማ መሆኑን እንደ ነገሯቸው ያስታውሳሉ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ የአራት ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ትልቅ የሆድ ግድግዳ ክፍተት ኖሮት ወደ ክፍላቸው መምጣቱን ተናግረዋል።

መጀመርያ ክፍተቱ ባለበት የሆድ እቃ ላይ የሚቀባ መድሃኒት (ጂቪ) መስጠታቸውን እና በኋላ ላይ ቦቶክስ (botulinum toxin) በመርፌ እንደሰጡት ይናገራሉ።

የሚቀባው መድሃኒት ስስ ከረጢት የነበረውን የሆድ እቃውን ክፍል ቀስ በቀስ የሆዱ ግድግዳ በቆዳ እንዲሸፈን ያደርጋል።

ቆዳው ግን ያበጠ ስለሚሆን ቀዶ ሕክምና በማድረግ ማስተካከል እንደሚያስፈልገው ጠቅሰው "አርተፊሻል እንብርትም" እንሰራለታለን ብለዋል።

ቦቱሊነም ቶክሲን ለተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት ሰጥቶ የተፈጠረውን ክፍተት መዝጋት በኢትዮጵያ የመጀመርያ መሆኑን ዶ/ር ይርጋለም ይናገራሉ።

"ለአገራችንም ለአፍሪካም ይህንን መድሃኒት ተጠቅሞ [የተፈጠረው ክፍተት] የተዘጋላቸው ሕሙማን ጥቂት ቁጥር ነው ያላቸው።"

ጨቅላው እንደተወለደ ክፍተቱ ትንሽ ከሆነ ወድያውኑ ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ተወስዶ እንዲዘጋለት ይደረጋል የሚሉት ዶ/ር ይርጋለም፣ አሁን በአይደር ሆስፒታል እንደተሰራው ዓይነት ትልቅ ክፍተት ከሆነ ግን ሕክምናውን ውስብስብ ያደርገዋል ይላሉ።

የአራት ቀን ዕድሜ የነበረው ጨቅላ ወደ እነርሱ ጋር ሲመጣ "ሙሉ ጉበቱ፣ ትልቁም ትንሹም አንጀቱ ውጭ ነበር፤ በጣም ሰፊ ነበር። ክፍተቱ ስምንት ሴንቲ ሜትር ድረስ ይደርሳል" ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

በተለምዶ እንዲህ ዓይነት የሆድ ክፍተት ያለባቸው ሕጻናት ሲመጡ ቀዶ ሕክምናውን አድርጎ፤ግድግዳውን ራሱ በራሱ ሰፍቶ መዝጋት ስለማይቻል "እስኪያድጉ የተወሰኑ ዓመታትን እንጠብቃቸዋለን" ይላሉ።

በዚህ ወቅት የሚቀባ ቅባት ተሰጥቷቸው የሆድ እቃቸውን የሸፈነውን ስስ ከረጢቱን እንዲቀቡት እና "ያ ከረጢት ቀስ በቀስ ወደ ቆዳነት ተቀይሮ፣ ቆዳ ብቻ የተሸፈነ ግን የግድግዳ ክፍተት ኖሯቸው፣ ሕጻናቶቹም አድገው ትልቅ ልጅ ከሆኑ በኋላ ሆዳቸው በደንብ ሲሰፋላቸው በቀዶ ሕክምና ይዘጋል" ሲሉ የሕክምናውን ሂደት ያስረዳሉ።

የአራት ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ላይ ግን ቦቶክስ የተሰኘውን መድሃኒት የተጠቀሙት ገና በሦስተኛ ቀኑ መሆኑን ተናግረዋል።

መድሃኒቱ በደንብ ለመስራት ከሦስት እስከ አምስት ሳምንታት መጠበቅ ያስፈልጋል የሚሉት ዶ/ር ይርጋለም ልጁን ከመድሃኒቱ አንድ ወር በኋላ ሲያዩት በጎን በኩል ያሉት የሆዱ ግድግዳ ጡንቻዎቹ በደንብ አድገው ነበር።

በዚህ ወቅት ቀዶ ሕክምናውን ማድረግ እና ክፍተቱን ሙሉ በሙሉ መዝጋት የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ የጨቅላውን ሆድ መዝጋታቸውን አብራርተዋል።

የሆድ ግድግዳ ክፍተት ያለባቸው ሕጻናት አብዛኛው ጊዜ በሌላ የአካል ክፍላቸውም ላይ ክፍተት እንደሚያጋጥማቸው ዶ/ር ይርጋለም ያብራራሉ።

"አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ክፍተት ሲኖራቸው ልባቸው ላይ ክፍተት ሊኖረው፣ የኩላሊት የቱቦ፣ ጀርባ ላይ የነርቭ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል" በማለት ተገቢውን የእርግዝና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

የሆድ ግድግዳ ያለባቸው ሕጻናት አንዳንድ ጊዜ እብጠቱ ራሱ ፈንድቶ፣ የውስጥ አካል ክፍል ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ስለሚወጣ ለመዝጋትም ከባድ ሊሆን እና የሕጻኑ ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል ይናገራሉ።

የሆድ ግድግዳ ክፍተት የሚከሰተው በዚህ ምክንያት ነው የሚመጣው ብሎ እቅጩን ለመናገር እንደሚከብድ ዶ/ር ይርጋለም ያብራራሉ።

ነገር ግን ለዚህ ችግር የሚያጋልጡ ነገሮች አሉ በማለት የሚያጨሱ፣የሚጠጡ ወይንም ከ40 ዓመት በኋላ ዘግይተው ያረገዙ እናቶች እንዲህ ዓይነት የጤና እክል ያለበት ልጅ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

የሆድ ግድግዳ ክፍተት በዘር የሚመጣበት ዕድል መኖሩንም ገልፀዋል።

ቦቶክስ (botulinum toxin) ለሆድ ግድግዳ ክፍተት ሕክምና ሲሰጥ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመርያው መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ይርጋለም፣ በዓለም ላይም ከ10 በታች ቀዶ ሕክምናዎች ብቻ በዚህ መንገድ መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ነፍሰ ጡር እናቶች ተገቢውን የእርግዝና ክትትል ስለማያደርጉ የሆድ ግድግዳ ክፍተት ያለባቸው ጨቅላ ሕጻናት በብዛት ይወለዳሉ።

በእርግዝና ወቅት ጽንሱ ይህ ችግር እንዳለበት ቀድሞ ከታወቀ አስፈላጊ ምርመራዎችን እና ሕክምናዎችን ለማድረግ ይረዳል የሚሉት ዶ/ር ይርጋለም፣ ዘግይቶ የታወቀ ከሆነ ደግሞ ወደ ትልልቅ ሆስፒታሎች ሪፈር በማድረግ አነስ ያለ ክፍተቶች ቶሎ እንዲዘጉ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።