ኢትዮጵያ፡ ልቡ በቀኙ በኩል ለሚገኘው ታዳጊ የተደረገው ስኬታማ ውስብስብ ቀዶ ሕክምና

በሰው ልጆች ተፈጥሮ ከተለመደው ውጪ የሰውነት ክፍሎቹ በተቃራኒው ለሚገኙት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ በኢትዮጵያ ውስጥ ውስብስብ እና የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል።

በኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምናውን የመሩት የሕጻናት እና የአዋቂዎች የልብ ሐኪም ዶ/ር ሺቢቆም ታምራት ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በተለምዶ ከሚታወቀው አፈጣጠር በተቃራኒው ልቡ በቀኙ በኩል ለሚገኘው ታዳጊ ከአሥር ቀናት በፊት ቀዶ ሕክምና ማካሄድ ተችሏል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ቡርጂ ዞን፣ ሶያማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የታዳጊው አባት አቶ ጂማ ሒዶ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የልጃቸው ችግር “በጣም ከባድ” እንደሆነና “በኢትዮጵያ ደረጃ መታከም ሊከብድ እንደሚችል” ተነግሯቸው ነበር።

ታዳጊው ሂዶ ጂማ ሂዶ የተደረገለት ቀዶ ሕክምና ስምንት ሰዓታት የፈጀ መሆኑን ዶ/ር ሺቢቆም ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ የውጭ አገር ሕክምናን የሚጠይቀው ይህ ውስብስብ የልብ ቀዶ ሕክምና በአገር ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

አቶ ጂማ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ “ልጄ እግዚአብሔር ይመስገን ታክሞ እየተጫወተ ይገኛል” በማለት ደስታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዶ/ር ሺቢቆም ቀዶ ሕክምናውን የገለጹት “ከባድ፣ በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቅ እና ውስብስብ” በማለት ነው።

“የሞተ ልጅ ተመልሷል”

የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ጂማ ቀዶ ሕክምናው የተደረገው ለበኩር ልጃቸው ሂዶ እንደሆነ ይናገራሉ።

“እስከ ስምንት ዓመቱ ድረስ እንደ ታይፈስ ዓይነት ቀለል ያለ ህመም ነበር የሚገጥመው” ያሉት አባት፣ ባለፈው ዓመት ታሞ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ የልጃቸው የሰውነት ክፍሎች ከሌላው ሰው በተለየ በተቃራኒ ስፍራ ላይ እንደሚገኙ እንደተነገራቸው ያስታውሳሉ።

ልጃቸው አምና የህመም ምልክቶች ከማሳየቱ በፊት ጤናማ እንደነበር ገልጸዋል።

“በጣም ይንቀሳቀሳል። ትምህርት ላይም ንቁ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ሮጦ ሮጦ ጨዋታውን ጠግቦ ሲመጣ 'ራሴን አመመኝ፣ አላበኝ' ማለት ጀመረ። ማስመለስም ነበረው። ነገር ግን ታሞ አልጋ የያዘበት ጊዜ አልነበረም” ብለዋል።

ችግሩ የልቡ እንደሆነና የልብ ክፍተትን ጨምሮ ልቡ እንደ አብዛኛው ሰው በግራ የደረቱ ክፍል ሳይሆን በቀኝ በኩል እንደሚገኝ ከተገለጸላቸው በኋላ ቀዶ ሕክምናው “በጣም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል” መባላቸውን ይናገራሉ።

“ከአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ የልብ ማዕከል ተላኩኝ። ጉዳዩ በጣም ከባድ በመሆኑ መፍትሄ ስፈልግ ነው ዶ/ር ሺቢቆምን ያገኘሁት” ሲሉ አስታውሰዋል።

ዶ/ር ሺቢቆም እንደሚናገሩት፣ የተካሄደውን ቀዶ ሕክምና የተለየ የሚያደርገው የታዳጊው ጂዶ የሰውነት ክፍሎች ከአብዛኛው ሰው በተቃራኒ ቦታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ነው።

አቶ ጂማ በበኩላቸው ከአምና ጀምሮ የሕክምና ሙከራ ሲያደርጉ “ተስፋ አለው” ብለው ነበረ። “እየሞከርኩ እያለ የሚሆነው ማየት አለብኝ ብዬ የቻልኩትን ሳደርግ ቆይቻለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

ልጃቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ቀዶ ሕክምናውን ማግኘት እንደሚችል ከተነገራቸው በኋላ “በጣም ልዩ ደስታ ነው የተሰማኝ። ልጄ ሊተርፍ ነው ብዬ ደስ አለኝ” ይላሉ።

ሕክምናው ውጭ አገር ቢካሄድ “እስከ አምስት ሚሊዮን ብር” ሊያስወጣ እንደሚችል ተነግሯቸው ነበረ፣ “ከተባለው በተቃራኒው ልጄ እዚሁ አገር ታክሞ ሰላማዊ ሆኖ እግዚአብሔር ይመስገን እየተጫወተ ይገኛል” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

“ልጄን አግኝቻለሁ። የሞተ ልጅ ተመልሷል ብዬ ነው የወሰድኩት” ብለዋል አባት።

የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ፣ ኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር ውል ተፈራርሞ የልብ ቀዶ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ላሉ ሕጻናት ያለ ክፍያ የቀዶ ሕክምና እየሰጠ እንደሆነ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን ተድላን ጠቅሶ ጽፏል።

ተቃራኒው የሰውነት ክፍሎች አቀማመጥ

ዶ/ር ሺቢቆም ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ቀዶ ሕክምናውን ለየት ከሚያደርጉት አንደኛው የታዳጊው “አፈጣጠር” ነው።

“አፈጣጠሩ የተለየ ነው። ይህም ከ10 ሺህ ሰው አንድ ወይም ከ25 ሺህ ሰው አንድ ሊገጥም የሚችል ነው። አንድ ባለሙያ በልብ ቀዶ ሕክምና አንዴ፣ ገፋ ቢል ሁለቴ ሊገጥመው የሚችል ችግር ነው የገጠመን” ብለዋል።

ታዳጊው ከተለመደው አፈጣጠር በተለየ ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ የሆነ የሰውነት ክፍሎች አፈጣጠር እና አቀማመጥ እንዳለው አስረድተዋል።

“በተለምዶው አፈጣጠር የምናውቀው ልብ በግራ በኩል እንዳለ ነው። የዚህ ታዳጊ ልብ ግን በቀኝ በኩል ነው። ጉበት በቀኝ በኩል ነው መሆን ያለበት የእሱ ግን በግራ በኩል ነው። ጨጓራ በግራ በኩል ነው መሆን ያለበት። የእሱ ግን በቀኝ በኩል ነው። የሳምባ ክፍሎቹም እንደዚሁ የቀኝ እና የግራ የተዘዋወሩ ነበሩ።”

ይህ ሁኔታ አብሮት እንዳደገ ገልጸው፣ የደም ሥሮቹም አቀማመጥ አስቸጋሪ እንደሆነ አክለዋል።

“እኛ በተልምዶው የምንሠራቸው የልብ ቀዶ ሕክምናዎች በታካሚው በቀኝ በኩል ነው። ለታዳጊው ግን በግራ በኩል ሆነን ነበር የምንሠራው” ሲሉ ቀዶ ሕክምናውን ሂደት ገልጸዋል።

ይህ በተቃራኒ የሚደግ ቀዶ ሕክምና “ለመሥራት አስቸጋሪ እና ፈታኝ” እንደሆነ ባለሙያው አብራርተዋል።

“ቀዶ ሕክምናውን አከናወንን። ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና በስኬት ነው ያበቃው። አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። እያገገመ ነው” ሲሉ ዶ/ር ሺቢቆም ተናግረዋል።

አቶ ጂማም ልጃቸው ደኅና እንደሆነ ገልጸዋል። “ልጄ አሁን ደኅና ነው። በራሱ ይጫወታል። ይወጣል፣ ይገባል። ይበላል። ሰላም ነው” ብለዋል።

የሰውነት ክፍሎች በተቃራኒው ሲቀመጡ “ብዙም ተጽዕኖ አይፈጥርም” ያሉት ሐኪሙ “እንደ ማንኛውም ሰው መኖር ይቻላል” ሲሉ አስረድተዋል።

በሰውነት ክፍሎቹ ላይ እክል እስካልገጠመ ድረስ የሰውነት ዕድገትም ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሆኖም ግን እነዚህ በተቃራኒው የተፈጠሩ የሰውነት ክፍሎች ህመም ሲገጥማቸው፣ የሚያስፈልጋቸው ቀዶ ሕክምና ከተለመደው ውጪ ስለሆነ ፈታኝ ይሆናሉ።

“ከተለመደው ቀዶ ሕክምና የወጣ መሆኑ ፈታኝ ያደርገዋል። ባለሙያዎች እያንዳንዱን የሚሠሩትን ነገር፣ እያንዳንዷን ክር እና መርፌ ሳይቀር የሚያሳልፉት በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው” ይላሉ።

የዘጠኝ ዓመቱ ታዳጊ ሂዶ እስከ አምና ድረስ የሰውነት ክፍሎቹ በተለየ ሁኔታ ቢቀመጡም ከልቡ ውጪ ሰውነቱ በጥሩ ሁኔታ እየሠራ እንደነበር ሐኪሙም አባትየውም ተናግረዋል።

“በምርመራ የደረስንበት ችግር የልቡን ነው። የልቡንም አስተካከልንለት። ከዚያ በኋላ ተጨማሪ ቀዶ ሕክምና አያስፈልገውም። ሳምባው፣ ጉበቱ፣ ኩላሊቱ ላይም ችግር አላየንም” ብለዋል ሐኪሙ።

በሂደት ችግር ሊከሰት ከቻለ በሚል ግን ናሙናው ወደ ውጭ አገር ለምርመራ ተልኳል።

“ያንን አይተን ቀድመው የሚደረጉ ነገሮች ካሉ እነሱን ለማድረግ በቀጣይ እናቅዳለን። ጤናማ ከሆነ በዚሁ እንዲቀጥል እናደርጋለን” ብለዋል ሐኪሙ።

ዶ/ር ሺቢቆም እንዳሉት ታዳጊው ሲጫወት ሲደክመው እና ትንፋሽ ሲያጥረው እንዲሁም ሲያልበው ወደ ሕክምና ከመወሰዱ በፊት ልቡን እንደሚያመው አልታወቀም።

አቶ ጂማም ለሕክምና ሲወስዱት “ታይፎይድ ነው። ታይፈስ ነው” ይባሉ እንደነበር ገልጸዋል።

አምና በተደረገ ምርመራ ግን ታዳጊው ልቡ ላይ ችግር እንዳለ እና አቀማመጡም ከተለመደው በተቃራኒው እንደሆነ ተነገራቸው።

ከዚያ በኋላ ነው ከዶ/ር ሺቢቆም ጋር የተገናኙት።

ዶ/ር ሺቢቆም “ችግሩ በቀዶ ሕክምናው ዘርፍ ከባድ፣ በጣም ጥንቃቄ የሚጠይ እና ውስብስብ እንደሆነ ተረዳሁ” ሲሉ ቀዶ ሕክምናውን ገልጸዋል።

ፈታኙ ቀዶ ሕክምና

በስምንት ሰዓቱ ቀዶ ሕክምና ፈተና ከሆኑት ነገሮች መካከል የደም ሥሮቹ አቀማመጥ አንዱ መሆኑን ባለሙያው ይጠቅሳሉ።

“የደም ሥሮቹ አቀማመጥ ተቃራኒ ከመሆናቸውም በላይ አንደኛው ደም ሥር ከቀኝ የልብ ክፍሉ ይነሳል። መነሳት የነበረበት ግን ከግራው ክፍል ብቻ ነበር። ይሄ ቀዶ ሕክምናውን አስቸጋሪ አድርጎታል።”

የቀዶ ሕክምናውን ሂደትም “ትክክለኛውን መንገድ ጠብቆ እንዲሄድ የምንከተለው አሠራር አለ። ያንን ስንሠራ ደሙ ምንም ዓይነት መቀላቀል ሳይፈጠር ዑደቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቅ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

አያይዘውም “የተወሰነ ሚሊሜትር እንኳን መስመር ሳት ብናደርግ የቀኝ እና የግራው የልቡ የደም ዑደቶች የተቀላቀሉ ይሆኑ ነበር” በማለት ቀዶ ሕክምናው የጠየቀውን ጥንቃቄ አስረድተዋል።

ችግሩ እንዴት ነው የሚከሰተው?

በእንግሊዝኛው ‘Situs inversus’ የተባለው የሰውነት ክፍሎች በተቃራኒው ቦታ ላይ ተቀምጠው መፈጠር በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ነው።

ከተለመደው የሰውነት አፈጣጠር በተቃራኒው የሰውነት ክፍሎች ለምን በተቃራኒው እንደሚቀመጡ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዶ/ር ሺቢቆም፣ የተረጋገጡ አጋላጭ ምክንያቶች እንደማይታወቁ አስረድተዋል።

የሰውነት ክፍሎች ለምን በተቃራኒ ቦታ ላይ ይመጣሉ? ለሚለው “ያልተረጋገጡ ብዙ መላ ምቶች አሉ” ያሉት ባለሙያው “የሰውነት ክፍሎች አቀማመጥን የሚወስኑት ዘረ መሎች ላይ ችግር ሲፈጠር የሚከሰት ነው የሚለው አንደኛው ነው” ብለዋል።

ችግሩ በብዛት የሚከሰት ስላልሆነ ጥናቶቹም ጥቂት እንደሆኑ አክለዋል።

“የተረጋገጡ አጋላጭ ምክንያቶች አለመታወቃቸው ፈታኝ ነው። ለዚህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና የሚሆኑ መጽሐፎችም የሉም። ዕውቀት እና ክህሎትን አዋህዶ ሕክምናው እንዴት መሠራት እንዳላበት መጠየቅ ያስፈልገዋል” ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነት ችግር የገጠማቸው ታዳጊዎች አንድ ዓመት ሳይሞላቸው በፊት ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላቸው በመጥቀስ “ልክ እንደ ታዳጊው ዘጠኝ ዓመት ሲሞላቸው ግን የሳምባ ግፊታቸው ከፍ ያለ ይሆናል።

“ስለዚህም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በሳምባ ግፊት ምክንያት ችግር ውስጥ እንዳይገባ፣ ልቡም እንዳይጎዳ ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብን። ሂደቱን ማባበል ነበረብን። ያ ጊዜ ይፈጃል። ለወትሮው ከምናደርገው ጥንቃቄ የበለጠ ይፈልጋል” ሲሉ አብራርተዋል።

በልብ ሕክምና በኢትዮጵያ ከሚታወቁ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሺቢቆም “እስካሁን ካደረግኳቸው ቀዶ ሕክምናዎች ከፈታኝነቱ ባሻገር ሲሠራ ሊያታልል የሚችል ቀዶ ሕክምና” ሲሉ ነው የገለጹት።

የታዳጊው ሂዶ አባት የሆኑት አቶ ጂማ አሁን ያላቸውን ስሜት ሲገልጹ፣ “ደስታዬን መቆጣጠር በማልችለው ደረጃ ነው ያለሁት። ልጄን አግኝቻለሁ” በማለት ለልጃቸው ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉትን ባለሙያዎች አመስግነዋል።