ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የየመን የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ከክላሽ እስከ ቦምብ ትዊተር ላይ እየሸጡ እንደሆነ ተደረሰበት
የየመን የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች በቀድሞው ትዊተር በአሁን መጠሪያ ኤክስ ላይ በግልፅ ክላሺንኮቭ እና የእጅ ቦምብ እየሸጡ እንደሆነ ተደረሰበት።
ነጋዴዎቹ በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ እና በሌሎች በሁቲ አማፂያን ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች ነው በንግድ ሥራቸው የሚንቀሳቀሱት።
የሁቲ አማፂያን በኢራን መንግሥት የሚደገፉ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ እና የአውስትራሊያ መንግሥታት ሽብርተኛ ናቸው ሲሉ ይፈርጇቸዋል።
“እኒህ የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ለሁቲ አማፂያን እየሠሩ አይደለም ማለት ከባድ ነው” ይላሉ በየመን የቀድሞው የብሪታኒያ አምባሳደር ኤድመንድ ፊተን-ብራውን።
ካውንትር ኤክስቲሪሚዝም ፕሮጀክት ለተሰኘ ተቋም የሚሠሩት የቀድሞው አምባሳደር አክለው “በግላቸው የሚንቀሳቀሱ የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ሆነው ለየመን መንግሥት መሣሪያ እያቀረቡ ቢሆን ኖሮ በፍጥነት ነበር የሚጠፉት” ይላሉ።
ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ባጠናቀረው የምርመር ዘገባ መሠረት አብዛኛዎቹ የየመን የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ኤክስ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚንቀሳቀሱት ‘ብሉ ቲክ’ [የማንነት ማረጋገጫ] አድርገው ነው።
ኤክስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ታይምስ ጋዜጣ እና ቢቢሲ ቢጠይቁም እስካሁን ምላሽ አላገኙም።
ኢላን መስክ በአውሮፓውያኑ 2022 ኩባንያውን ከገዛው በኋላ በርካታ የይዘት ተቆጣጣሪዎች [ኮንቴንት ሞደሬተርስ] ከሥራቸው ተባረዋል።
የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ማስታወቂያ የሚሠሩት በአረብኛ ሲሆን በዋናነት ዒላማ የሚያደርጉት ሀገር ቤት ያሉ የመናዊያንን ነው። በየመን የጦር መሣሪያ ቁጥር ከሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ ሲሆን አንድ ሰው ቢያንስ ሶስት የጦር መሣሪያ እንዳለው ይገመታል።
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ በርካታ የኤክስ ገፆች የጦር መሣሪያ በየመኒ እና ሳዑዲ ሪያል ለመሸጥ ሲያስተዋውቁ መመልከት ችሏል።
ከጦር መሣሪያ ፎቶዎች ጋር የሚለጠፉት ፅሑፎች ገዢዎችን ለማማለል የተዘጋጁ ናቸው።
“በከፍተኛ ጥራት የተሠራ እና ዋስትና ያለው” ይላል አንድ ማስታወቂያ። አስከትሎ ደግሞ “የመን ውስጥ የተሻሻለው ኤኬ የእርስዎ ምርጫ ነው” ሲል ያስተዋውቃል።
በጨለማ የተቀረፀው የማስታወቂያ ቪድዮ አንድ ግለሰብ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ የሆነ የጦር መሣሪያ ይዞ 30 ዙር ጥይት ሲያርከፈክፍ ያሳያል።
በሌላኛው ማስታወቂያ ደግሞ ግራጫ ቀለም ያላቸው ፓኪስታን የተመረቱ አነስተኛ የእጅ ሽጉጦች እያንዳንዳቸው በ900 የአሜሪካ ዶላር ለሽያጭ ቀርበዋል።
ለወትሮው እንዲህ ያሉ የጦር መሣሪያዎች እና ሌሎች ሕጋዊ ያልሆኑ ነገሮች ‘ዳርክ ዌብ’ በተሰኘ ድረ-ገፅ ላይ ነበር የሚሸጡት። አሁን ግን በግልፅ በርካታ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ኤክስ ላይ እየተሸጡ ይገኛሉ።
መቀመጫውን ዩኬ ያደረገው ቲች አጌንስት ቴረሪዝም የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ማኅበራዊ ሚድያዎች የሁቲ አማፂያንን የሚደግፉ ይዘቶችን እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርቧል።
ከተራራማው የየመን አካባቢ የመጡት የሁቲ አማፂያን በአውሮፓውያኑ 2014 ነው በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት ገልብጠው አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት።
ከዚያ በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች በምትገኘው የመን በሳዑዲ አራቢያ የተመራ ጥምር ኃይል አማፂያኑን ለማስወገድ 7 ዓመት የፈጀ ዘመቻ ቢያካሂድም አልተሳካለትም።
የሁቲ አማፂያን ከኢራን የተበረከቱትን ጨምሮ በርካታ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ያሏቸው ሲሆን በ2023 መጨረሻ ቀይ ባሕርን ተሻግረው የሚያልፉ የንግድ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ ጀምረው ነበር።
ሁቲዎች ይህን የሚያደርጉት በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማዊያን ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት እንደሆነ ቢናገሩም አብዛኛዎቹ ዒላማ የሆኑ መርከቦች የእስራኤል ንብረት አልነበሩም።
በሁቲዎች ጥቃት ምክንያት የግብፁን ሱዌዝ ካናል የሚያቋርጡ መርከቦች እክል ገጥሟቸው ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የተመራ የባሕር ኃይል ሁቲዎች በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ማስቆም ተስኖት ቆይቷል።