ፆታዊ ጥቃት፡ “የሕግ ክፍተት” ወይስ “ማኅበረሰባዊ ቀውስ”?

ሄቨን አወት፣ ካሚላት መህዲ፣ ሃና ላላንጎ፣ መዓዛ ካሳ፣ ፋጡማ ኡጋስ፣ አያንቱ ሙስጠፋ፣ አዳናዊት ይሄይስ፣ ጫልቱ አብዲ.....

እነዚህ ስድስት ሴቶች በተለያየ የዕድሜ፣ የማኅበረሰብ እና የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ ናቸው። እንስቶቹ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው። ከመሃል አዲስ አበባ እስከ ምሥራቅ ሐረረጌ፣ ከባሕር ዳር እስከ ጅግጅጋ።

ከሰባት ዓመቷ ሄቨን እስከ የሁለት ልጆች እናቷ አያንቱ ሁሉም ግን የአሰቃቂ ፆታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል።

ሩጣ ይልጠገበችው ሄቨን አወት በቅርብ በምታውቀው ሰው ተደፍራ ተገድላለች። ሃና ላላንጎ እና ፋጡማ ኡጋስ በአሰቃቂ ሁኔታ በደቦ ተደፍረው ተገድለዋል።

እነዚህ ሴቶች አይተዋወቁም። አብረው ማዕድ አልተጋሩም። የደረሰባቸው ግፍ ግን ያመሳስላቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱት ግጭቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የፀጥታ መደፍረሶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን አባብሰውታል።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው አሰቃቂ ጦርነት ውስጥ ፆታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ መዋሉን የመንግሥታቱ ድርጅት ይፋ አድርጎ ነበር። ጦርነቱ ካበቃ በኋላም በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አላቆመም።

የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት በሚያደርጉበት የአማራ ክልል ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመድፈር ወንጀሎች መበራከታቸውን የክልሉ ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርታቸው አመልክተዋል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በጦርነት እና በግጭት አውድ ውስጥ ብቻ የሚፈጸሙ አይደሉም። ግጭት በሌለበት ጊዜም በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሴቶች ጥቃቶች ይፈጸማሉ።

ሌላ ጥቃት. . . ሌላ ስጋት. . .

አዳናዊት ይሄይስ ስትገደል 17 ዓመቷ ነበር። ከአስር ዓመቷ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በእንጀራ አባቷ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጸምባት ነበር።

በ2015 ዓ.ም. መጀመሪያ በእንጀራ አባቷ ሲፈጸምባት የነበረው ተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ከእናቷ ጆሮ ኋላ ላይም ወደ ፖሊስ ይደርሳል።

ፖሊስ ተከሳሹን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ወንጀሉን የፈጸመው ሚካኤል ሽመልስ የተባለው ግለሰብ ከአካባቢው ይርቃል።

ከሰዓታት በኋላ ወደ ቤቱ የተመለሰው ግለሰቡ ከእናቷ ጋር የነበረችውን አዳናዊት ይሄይስን “ለፖሊስ የጠቆምሽው እና ያዋረድሽኝ አንቺ ነሽ” በማለት በስለት ወግቶ ገድሏታል።

ይህ ክስተት ከሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ጋር በብዙ ተመሳሳይነት አለው። ሴቶች የደረሰባቸውን ጥቃት በመናገራቸው ብቻ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። የቅርብ ዘመዶቻቸው ሳይቀሩ ለደኅንነታቸው ይሰጋሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጇ በቤት አከራይዋ ተደፍራ የተገደለችባት አበቅየለሽ አደባ ለዚህ ማሳያ ናት።

የሰባት ዓመቷን ሄቨን አወት ደፍሮ የገደለው ጌትነት ባዬ የተባለው ወንጀለኛ በዐቃቤ ሕግ ክስ ሳይመሠረትበት በፊት ከእስር ቤት አምልጦ ነበር።

ይህን ተከትሎም አበቅየለሽ እና ሁለተኛ ልጇ ለመደበቅ ተገድደው ነበር።

ጌትነት ከእስር ያመለጠው ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ያሉት የፋኖ ታጣቂዎች አባሎቻቸውን ለማስፈታት እሱ ታስሮበት የነበረውን እስር ቤት ከሰበሩ በኋላ ነበር።

ከእስር ያመለጠው ጌትነት መሳሪያ ታጥቆ የሄቨንን እናት ይፈልግ ጀመር። ግለሰቡ ለአንድ ወር ያህል አልታሰረም ነበር።

የከተማው የፀጥታ ኃይሎች ጌትነትን እንደገና ለማሰር ቸልተኝነት እንደታየባቸው የምትናገረው እናት፤ በድጋሚ እንዲይዙትም መለመን ነበረባት። በዚህ ሁሉ መካከል ጌትነት ያስፈራራት ነበር።

ልጇን ከማጣት ሰቆቃ በላይ የግለሰቡ ማስፈራራት የተደራረበባት አበቅየለሽ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት እንዲሁም ሥራዋን በተደጋጋሚ ለመልቀቅ ተገዳለች።

ከአምስት ዓመታት በፊት ወርሃ ጥር ላይ መዓዛ ካሳ የተባለች የሁለት ልጆች እና በሥራ ባልደረባዋ በስለት ተወጋች። መዓዛ ለሁለት ወራት ያህል ህክምና ስትከታት ቆይታ ሕይወቷ አልፏል።

መዓዛን ለሞት የዳረጋትን ጥቃት ያደረሰባት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለህክምን ከእስር ቤት በወጣበት አምልጧል። ከዚያ በኋላም በስልክ እየደወለ ቤተሰቦቿን ያስፈራራ እንደነበር በጊዜው ተዘግቦ ነበር።

ይህ የፀጥታ ተቋማት ላይ የሚስተዋል ቸልተኝነት ተጠቂዎችን መልሶ ለአደጋ ይዳርጋል።

ወንጀለኞች ተፈርዶባቸው ወደ ወህኒ ከወረዱም በኋላ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከእስር ቤት ይወጣሉ።

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከ17 ዓመታት በፊት በ1999 ዓ.ም. የገና ዋዜማ ካሚላት መህዲ ላይ አሲድ ደፍቶ ቅጣት የተላለፈበት ወንጀለኛ ጉዳይ ነው።

ደምሰው ዘሪሁን የተባለው ግለሰብ የሞት ቅጣት ከተላለፈበት በኋላ በይግባኝ ወደ ዕድሜ ልክ ተሻሽሏል። ነገር ግን ግለሰቡ 12 ዓመት ከሰባት ወራት ከታሰረ በኋላ፤ ከእስር ቤት ተፈትቷል።

ደምሰው ዘሪሁን የተባለው ይህ ግለሰብ ከ30 በላይ ሴቶችን በማጭበርበር በቁጥጥር ስር መዋሉን ብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቲቪ ዘግቦ ነበር።

በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው፤ “ማረሚያ ቤት አካባቢ ራሱ ችግር ነበረበት። ተደጋጋሚ ጊዜ ታስሯል፣ በተለያየ ቦታ ተደጋጋሚ ምርመራዎች አሉት ግን ጠበቅ ብሎ ወደ ሕግ እንዲቀርብ የተሄደበት መንገድ ግን ትክክል አልነበረም” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።

ይህ የፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት አስተማሪ አለመሆን ለፆታዊ ጥቃቶች መባባስ ምክንያት መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ካሚላት መህዲ ከስድስት ዓመት በፊት “የኔ ጥቃት እንደ ዋዛ እንደ ተራ ነገር ሆኖ ለሌሎቹ መጥፎ ምሳሌ ሆኗል። አሁን አሲድ ጥቃት እንደ ፌዝ ሆኖ የዐይን ብርሃንን እስከማጥፋት ደርሷል። በሰዓቱ የማያዳግም ውሳኔ ቢወሰን ኖሮ ዛሬ በአሲድ የተጠቃን ሴቶች አንበረክትም ነበር” ስትል ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።

ብዙዎቹ ፆታዊ ጥቃቶች የሚያመመሳስላቸው ነገር ጥቃት ፈጻሚዎቹ የቅርብ ሰው መሆናቸው ነው።

የሴታዊት እንቅስቃሴ መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑው ዶ/ር ስኂን ተፈራ፤ “እነዚህን ወንዶች ማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ የእኛው ወንድሞች፣ አባቶች ጓደኞች ናቸው ከሌላ ቦታ መጥተው አልደፈሩም” ይላሉ።

“በሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣሉ”

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች እና የእንስታዊ እንቅስቃሴ አቀንቃኞች የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት ለፆታዊ ጥቃት መባባስ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

ዶ/ር ስኂን ተፈራ፤ “ከፍተኛ ክፍተት ያለው የፍትሕ ሂደቱ ላይ ነው” ይላሉ።

ዶ/ር ስኂን “አጥፊዎች የእውነት ቢያዙ፣ የእውነት ቢቀጡበት የፍርድ ሂደቱ ይሄ ሁሉ ክፍተት ኖሮበት ብዙ ሰው ስለሚያመልጥ እና ያለ ቅጣት ስለሚኖር ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች “ሪፖርት አያደርጉም” የሚል ችግር ይነሳ እንደነበር የሚጠቅሱት የሴታዊት ዳይሬክተር፤ “ከዚያ በኋላ ግን ብዙ ክፍተት እያየን ነው። ብዙ ጊዜ ሴቶች በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ፖሊስ ጋር ሲሄዱ ከዚያ በኋላ የሚያገኙት ምላሽ ነው እውነት ተስፋ የሚያስቆርጠው። ፖሊሶች ይሳለቁባቸዋል፤ ፋይል ለመክፈት ዳተኝነት ይታያል። ሕፃናት ተደፍረው ሲሄዱ አለማመን አለ” ሲሉ ይናገራሉ።

በፖሊስ እና በዐቃቤ ሕግ መካከል “ከፍተኛ ክፍተት” እንዳለ ዶ/ር ስኂን ያነሳሉ። ይህ ክፍተት የፆታዊ ጥቃት ወንጀሎች ምርመራ በሚከናወንበት ጊዜ አለመናበብ እና “ንትርክ” እንዳለ ያክላሉ።

ጠበቃ እና የሕግ አማካሪዋ አዲስ መሐመድም በተመሳሳይ “የፍትሕ ሂደቱ ላይ ክፍተት አለ” በሚለው አስተያየት ይስማማሉ። ለስምንት ዓመታት የሴቶች እና የሕፃናት ዐቃቤ ሕግ ሆነው የሠሩት አዲስ፤ በወንጀል ሕጉ ላይ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ የሰፈሩት ድንጋጌዎች “መሻሻል አለባቸው” ይላሉ።

የሕግ አማካሪዋ አክለውም፤ “የወንጀል አፈጻጸሙ በጣም ዘግናኝ ሲሆን እና የደረሰው ጉዳት የማይተካ ሲሆን ቅጣቱ በጣም አስተማሪ መሆን አለበት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮች

አዲስ መሐመድ በወንጀል ሕጉ ላይ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ከሚሏቸው ጉዳዮች መካከል ድንጋጌዎች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚው ነው።

ከዚህ በተጨማሪ “የቅጣት ሁኔታው ቢሻሻል የማስጠንቀቅ አቅሙ በጣም ከፍተኛ ይሆናል” ሲሉ ወንጀለኞች ላይ የሚተላለፉ ቅጣቶችን የሚወስኑት የሕጉ ድንጋጌዎችም ሊሻሻሉ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያዋ ያነሳሉ።

ቅጣት ከተላለፈ በኋላም አፈጻጸሙ ላይ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ጠበቃ አዲስ ጠቁመዋል። “አፈጻጸሙን በተመለከተ ከሴቶች እና ሕፃናት ጋር በተያያዘ በጣም ዘግናኝ የሆኑ ወንጀሎች ተፈጽመው [ወንጀለኛው] ቢበዛ ዕድሜ ልክ ነው የሚቀጣው ይህ መሆኑ ማኅበረሰቡ እንዳይማር አድርጎታል” ይላሉ።

ዶ/ር ስኂን በበኩላቸው ይህን የሕግ “ክፍተት” ማሻሻል ብቻውን “ችግሩን ይፈታዋል ብዬ አላምንም” ይላሉ። አክለውም፤ “‘ሕጉ አንሷል’ የሚሉ ሰዎች [አጥፊዎቹ] ሕጉ በሚፈቅደው መጠን እየተቀጡ አለመሆናቸውን ሳያገናዝቡ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

የሴታዊት ዳይሬክተሯ አክለውም “ያሉትን ክፈተቶች የአሠራር ሂደቶች ነው ማስተካከል ያለብን፤ ያለውንም ሕግ መቼ ሠራንበት መጀመሪያ” ሲሉም የጠይቃሉ።

“በሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣሉ” የሚሉት፤ ዶ/ር ስኂን “ዐቃቤ ሕግ የሚከስበት የሕግ ድንጋጌ የትኛው ነው? የሚለው ራሱ የዚያን ተከሳሽ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው። የሕግ ክፍተቱ ለመመዘን ይከብዳል” ሲሉ ያስረዳሉ።

የሕግ ባለሙያዋ አዲስ መሐመድም፤ “ሕጎቹን ብቻ ማሻሻል መፍትሔ አይደለም፤ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች እንዲቀንሱ ዕድል ይፈጥራል” ይላሉ።

ነገር ግን ከሕግ ድንጋጌዎች ማሻሻያ ጎን ለጎን ወንጀሉን ከሚጠረጥሩት ጀምሮ ፍርድ እስከሚሰጡት ሰዎች ድረስ “የተለየ ሥልጠና መውሰድ አለባቸው” በማለት ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎች ያነሳሉ።

አዲስ መሐመድ “ኃላፊነት የማይሰማቸው መርማሪዎች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ዐቃቤ ሕጎች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ዳኞች ሲሆኑ የተጓደለ ፍትሕ እንዲሰጥ ዕድል ይፈጥራል” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሴቷ የደረሰባት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ጉዳት የሚያስከትል ጥያቄ የሚጠይቁ ዳኞችም እኮ አሉ” የሚሉት ጠበቃ አዲስ፤ ፆታዊ ጥቃቶችን የሚመለከት “ልዩ ችሎት መቋቋም አለበት” ሲሉም አክለዋል።