ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሁለት ኮሪያውያንን “አግቶ ለአልሸባብ ሰጥቷል” ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሰ
ባለፈው ሳምንት ኬንያ ውስጥ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የተወሰዱት ሁለት የኮሪያው፤ መንግሥት “ሸኔ” እያለ በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ታግተው ለአልሸባብ ተላልፈው መሰጠታቸውን” የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ።
ታጣቂ ቡድኑ፤ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር “ቀጥታ ግንኙነት አለው” ሲልም መንግሥት ከስሷል።
ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለቀረበበት ክስ ከቢቢሲ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ክሱን አስተባብሎ፣ ከሶማሊያው ታጣቂ ቡድን ጋርም ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።
አገልግሎቱ ይህንን የገለጸው፤ የኬንያው የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኑረዲን ሐጂ ረቡዕ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ነው።
ኑረዲን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተቋማት “በመረጃ ልውውጥ እና በፀጥታ እና በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመሥራት” በተፈራረሙት “የጋራ መግባቢያ ሰነድ” መሠረት እንደሆነ የኢትዮጵያ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንደተጠቀሰ ተዘግቧል።
“በበርካታ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እና ግምገማ” እንዳደረጉ የጠቀሰው የተቋሙ መግለጫ፤ በውይይቱ ላይ “በሱዳን ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት፣ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ጉዳይ እና የሳይበር ደኅንነት” ጉዳዮች መነሳታቸውን አስታውቋል።
በመግለጫው ላይ በዋነኛነት የተጠቀሰው የሁለቱ አካላት የውይይት አጀንዳ “በሁለቱ አገራት ድንበር እና በኬንያ ውስጥ” የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጉዳይ ነው።
ታጣቂ ቡድኑ በድንበር አካበቢ እና ኬንያ ውስጥ “ገባ ወጣ እያለ የተለያዩ እኩይ ተግባራት” እንደሚፈጽም የጠቀሰው መግለጫው፤ ቡድኑ በአካባቢው እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ “ለመግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ” ምክክር መደረጉን ይገልጻል።
ተቋሙ፤ “ቡድኑ በተለይም ሲፈጽማቸው የነበሩ ዜጎችን የማገት፣ ንብረት የመዝረፍ እና የማውደም እንዲሁም የሰዎችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ተግባር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኬንያ ዜጎችንም ጭምር ችግር ላይ መጣሉ ተነስቷል” ብሏል።
ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም. በኬንያ ማርሳቢት ግዛት በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በሚገኝ ቦታ ላይ ታግተው የተወሰዱት ሁለት ኮሪያውያን ግለሰቦች ጉዳይም በተቋሙ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
በአካባቢው የነበሩት ሁለቱ ኮሪያውያን ታግተው የተወሰዱት ታጣቂዎች በአንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ መሆኑ የኬንያው ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።
ሌላኛው የአገሪቱ ጋዜጣ ስታር ደግሞ ታጣቂዎቹ “ከኢትዮጵያ በኩል ተሻግረው” እንደመጡ የአካባቢው ነዋሪዎችን በመጥቀስ ዘግቧል። የማርሳቢት ግዛት ባለሥልጣናት በክስተቱ ማግስት ባወጡት መግለጫ ታጋቾቹ ያሉበት እንዳልታወቀ ገልጸው ነበር።
የአንድ የአካባቢው ባለሥልጣን፤ የአንደኛው ታጋች የሞባይል ስልክ ሲግናል የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢን አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜ ስልኩ በመጥፋቱ መከታተል እንዳልተቻለ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የግዛቱ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ፤ እገታው በተፈጸመበት ዕለት ታጣቂዎች ድንበር አካባቢ ምግብ ሲያጓጉዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ስምንት ሰዎችን መግደላቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ከመሆኑ ሦስት ቀናት አስቀድሞ ታጣቂዎች ንብረትነቱ “የኢትዮጵያ” የሆነ “ቡልዶዘር” ተሽከርካሪን ማቃጠላቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ በሁለት ኮሪያውያን ዜጎች ላይ ለተፈጸመው እገታ “የሸኔ የሽብር ቡድን” ሲል የጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ አድርጓል።
ቡድኑ በሁለቱ አገራት ድንበር አቅራቢያ “ያገታቸውን” ግለሰቦች በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን “አሳልፎ እንደሰጠም” መግለጫው ጠቅሷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ የቀረበበት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ገልጾ “ከአልሸባብ ጋር የሚያገናኘን አንዳች ነገር የለም” በማለት ቡድኑ የያዘው የውጭ ዜጋ የለም ሲል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ አስተባብሏል።
“ቡድኑ በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት” እንዳለው ከኬንያው የመረጃ ተቋም ጋር በተደረገው ውይይት ላይ መነሳቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ “ሁለቱ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው እና በቀጠናው የደቀኑትን የሽብር ስጋት በጋራ ለመከላከል እና ለመቀልበስ እንደወሰኑ” አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ “የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፤ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት እና ማዘዋወር ሥራዎች” ላይ እንደተሰማራ በመግለጫው ሰፍሯል። እነዚህን የታጣቂ ቡድኑን “ሥራዎች ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ” ሁለቱ ተቋማት “አቅጣጫ” እንዳስቀመጡ ተገልጿል።
የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች፤ “ድንበር አካባቢ እና በኬንያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድን አመራሮች እና ታጣቂዎች ላይ የጀመሩትን ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል” ተስማምተዋል ተብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት አርብ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር ላይ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ ለተፈጸመት “ተኩሶች፣ የማቃጠል ተግባር እና እገታ የመጀመሪያ ተጠርጣሪ” የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ገልጾ ነበር።
“በኢትዮጵያ በኩል ካለው ድንበር የተሻገሩት” ታጣቂዎች ጥቃት የፈጸሙት “በኦሮሞ ተወላጆች እና የውጭ ዜጎች” ላይ እንደሆነ ቡድኑ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
“ይህ ዓይነቱ ሆነ ተብሎ በንጹሃን ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ድርጊት ጉዳት በደረሰባቸው ላይ የተፈጸመ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ነው” ሲልም ድርጊቱን አውግዞ ነበር።
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙት በአብዛኛዎቹ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የኬንያ ፖሊስ እንዳስታወቀ ሠራዊቱ በመግለጫው አስታውሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት በቀጣናው ላይ “አለመረጋጋትን ሲያመጣ” ቆይቷል በማለት የከሰሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ “ምርመራዎች በሂደት ላይ ቢሆኑም ቀዳሚው ተጠርጣሪ ሆኖ ይታያል” ሲል ወንጅሏል።