ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሚኬል አርቴታ፡ በፈተና የተሞረደው ወጣቱ የአርሰናል አሠልጣኝ
ፔፔ ሬይና እና ሚኬል ተደራራቢ አልጋ የተጋሩ ባልንጀሮች ናቸው። በባርሴሎና ቤት።
ሬይና የላይኛው አልጋ ላይ ነው ወገቡን የሚያሳርፈው። አርቴታ ደግሞ ከተቻ። ከሆነ አቅጣጫ ድምፅ ይመጣል።
የቀድሞው የሊቨርፑል እና የናፖሊ ግብ ጠባቂ ይናዘዛል “በጣም አንኮራፋ ነበር እና ክፍሉ ውስጥ የነበሩ ሁሉ ይናደዱብኛል።”
“ሁሉም ያገኘውን ይወረውርብኛል። ነጠላ ጫማ፣ ታኬታ. . . ነገር ግን እኔን ሳይሆን አርቴታ ነበር የሚመቱት።”
አርቴታ እና ሬይና ገና ታዳጊ ሳሉ ወደ ላ ማስያ ገቡ። ሊዮኔል ሜሲ፣ አንድሬስ ኢኔሽታ እና ዣቪን ያበቀለ ቤት ነው።
ይህ አካዳሚ ከካምፕ ኑ መንገድ ተሻግሮ ከሚገኝ አንድ የግብርና መሬት ላይ ያረፈ ነው።
ሬይና እንደሚለው፤ አርቴታ ለዛሬ ማንነቱ ያበረከቱ፤ ተስፋ ካላቸው ምርጥ የአውሮፓ አሠልጣኞች አንዱ እንዲሆን ያደረጉ ባሕሪያትን መላበስ የጀመረው እዚህ አካዳሚ ሳለ ነው።
በአርቴታ የተመራው ወጣቱ አርሰናል ቡድን የዘንድሮ ሁለተኛ ወጥቷል፤ ከ2016/17 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ተመልሷል።
“13 ወይም 14 ዓመታችን ነበር። እህት ወንድሞቻችን፤ ቤተሰቦቻችን ይናፍቁናል። አስታውሳለሁ አንድ ቀን ከቤት የተላከልኝን ደብዳቤ ሳነብ አንዳንድ ልጆች ያለቅሱ ገቡ” ይላል ሬይና።
“ላ ማስያ ውስጥ ለመቆየት ጥንካሬ ሊኖርህ ይገባል፤ ቁርጠኛ መሆን አለብን፤ ዋንጫ ለማግኘት አሊያም ያሰብከውን ለማሳካት የማትወጣው ዳገት አይኖርም።”
ከአእምሮ ዕድገት በተጨማሪ በፔፕ ጉዋርዲዮላ መሪነት የዘመናዊ እግር ኳስ ፍልስምናን ካጠኑ መካከል አንዱ አርቴታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዣቪ ነው።
ሬይና እንደሚለው ሦስቱም አሠልጣኞች በተጫዋችነት ዘመናቸው አማካይ የነበሩት በግጥምጥሞሽ አይደለም።
የጉዋርዲዮላ እና አርቴታ አስተማሪ የነበረው ፓኮ ሴይሩሎ የባርሴሎና አጨዋወት ‘ስታይልን’ ጠንቅቆ ያውቃል።
በፈረንጆቹ 1994 ዮሃን ክራይፍ ፤ ፓኮን የባርሴሎና የመጀመሪያው ቡድን የአካል ብቃት አሠልጣኝ አድርጎ ሾመው።
“አንደኛው ፍልስፍና የነበረው የቡድን አጋሮችህን ከራስህ አስበልጥ የሚል ነው” ይላል ፓኮ።
ከስፔኗ ባሕር ዳርቻ እስከ ለንደን
አርቴታ በተጨዋችነት ዘመኑ እንዲሁም በአሠልጣኝነቱ ባመጣው ስኬት እንደ ሳን ሴባስቺያን ሰዎች ደስ የሚለው አይኖርም።
አርቴታ፤ በዚህ የባሕር ዳርቻ ከተማ ነው የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው።
ከአንድ የውበት ሳሎን እና ቀለመ ዳልቻ ሕንፃ መካከል ባለ አንቲጉዎኮ የእግር ኳስ ክለብ ነው አርቴታ በልጅነቱ ኳስ ያንጠባጥብ የጀመረው።
በትንሽየዋ ስታድየም አንድ ጥግ ላይ የሁለት የእግር ኳስ ከዋክብት ሥዕል ዐይነ-ግቡ ሆኖ ተሰቅሏል።
ዣቢ አሎንሶ እና ሚኬል አርቴታ።
ምንም እንኳ አርቴታ በባርሴሎና አካዳሚ ቢያድግም ለባርሴሎና ዋናው ቡድን ከወዳጅነት ውጪ ተጫውቶ አያውቅም።
የአማካይ ሥፍራውን ወጣቶቹ ዣቪ እና ኢኒየሽታ ይዘውታል። ከዚያ ሲተርፍ ደግሞ ጫማ ለመስቀል የተቃረበው ጉዋርዲዮላ አለ።
በ2000/01 የውድድር ዘመን ባርሴሎና ወጣቱ አርቴታን በውሰት ወደ ፒኤስጂ ላከው። ሮናልዲንሆ፣ ጄይ ጄይ ኦኮቻ እና ኒኮላስ አኔልካ በወቅቱ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ነበሩ።
ከ18 ወራት በኋላ አርቴታ የስኮትላንዱን ታላቅ ክለብ ሬንጀርስ ተቀላቀለ። እያደርም የክለቡ አርማ ይሆን ጀመር።
በ2002/03 የውድድር ዘመን ሬንጀርስ እና የዘመናት ተቀናቃኛቸው ሴልቲክ በጎል ልዩነት ተለያይተው በነጥብ እኩል እንዳሉ የመጨረሻው ቀን ደረሰ።
ሬንጀርስ በመጨረሻው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አገኘ። ይህች ኳስ መረቡን ከነካች ዋንጫው የአርቴታ እና የሬንጀርስ ይሆናል።
የ21 ዓመቱ አርቴታ ኳሷን ታቅፎ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት መምቻው አመራ። አርቴታ ጎሏን አስቆጥሮ በሬንጀርስ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ስሙን አሰፈረ።
ከሬንጀርስ ቀጥሎ አርቴታ ወደ ኤቨርተን አመራ። ብዙዎች ሚኬል አርቴታ ኃላፊነት መውሰድ የተማረው በኤቨርተን ቤት ነው ብለው ያምናሉ።
ነሐሴ 2011 አርቴታ ወደ አርሰናል አቀና። በወቅቱ አርሰናል ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ አቅንቶ 8 ለ 2 ተሸንፎ ነበርና መሪ ያስፈልገዋል ሲባል ነው አርቴታ የመጣው።
በአርሰን ቬንገር ጥላ ሥር የነበረው አርቴታ፣ የቡድኑ አምበል ሲሆን ነው ልቡ ወደ አሠልጣኝነት ይሸፍት የጀመረው።
ሬይና፤ አርቴታ ወደ ሲቲ አቅንቶ በጉዋርዲዮላ ጥላ ሥር ለሦስት ዓመታት መቆየቱ “ከሃርቫርድ በማስተርስ ዲግሪ” ከመመረቅ የማይተናነስ ነው ብሎ ያስባል።
2019 አርቴታ ወደ አርሰናል ቤት ተመልሶ መጣ። በመጀመሪያው ዘመኑ ማንቸስተር ሲቲን ረትቶ ለፍፃሜው በመድረስ የኤፍ ኤ ዋንጫን አነሳ።
መንገዱ ግን አልጋ በአልጋ አልሆነለትም።
በተከታታይ የውድድር ዘመን 8ተኛ ሆነው የጨረሱት አርሰናሎች በ2021/22 የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ተሸነፉ።
በወቅቱ አንድ በይነ-መረብ ላይ የተሰበሰበ የሕዝብ ድምፅ 70 በመቶ የአርሰናል ደጋፊዎች ክለቡን ለቆ እንዲወጣ እንደሚፈልጉ አሳየ።
ነገር ግን ፈተናን ማለት በላ ማስያ የተማረው አርቴታ በጩኸት አልተረታም። እንደ ኦዚል እና ኦባሜያንግ ያሉ ኮከብ ተጫዋቾችን አሰናብቶ በወጣቶች የሚመራ ቡድን ይሠራ ያዘ።
አርሰናል በ2022/23 የውድድር ዘመን አብዛኛውን ክፍል ሊጉን ሲመራ ቆይቶ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የሲቲን ግስጋሴ መቋቋም አቃተው።
አሁን የአርሰናል ደጋፊዎች በአርቴታ ላይ ያላቸው እምነት እየተመለሰ የመጣ ይመስላል።