ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሌክስ ፈርጉሰን ከዩናይትድ ሊለቁ እንደሆነ ሲሰማ ምን ተፈጠረ? ያልተሰማ ታሪክ
ሰኞ ግንቦት 8/2023 (እአአ) ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ካሳደጉት እና ካሳደጋቸው ቤታቸው ለቀው ከወጡ አሥር ዓመት የደፈነበት ቀን።
እሳቸው ከኦልድ ትራፈርድ መለቀቃቸውን በይፋ ከማወጃቸው አንድ ቀድሞ ዜናው ወጣ።
ማንቸስተር ዩናይትድ የፈርጊን መልቀቅ ዜና በድብቅ ለመያዝ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፤ ነገር ግን አልተሳካለትም።
እነሆ ክለቡ ከዝነኛው አሠልጣኝ ከተለያዩ አሥር ዓመት ቢሆነውም ከሕመሙ አላገገመም።
ስኮትላንዳዊው አሠልጣኝ አሁን በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ሜዳሊያ ያጠለቁ እንደሆኑ አሉ።
አሥራ ሦስት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን አንስተዋል፣ አምስት ጊዜ ኤፍ ኤ ዋንጫ፣ ሁለት ቻምፒየንስ ሊግ፣ የአውሮፓ አሸናፊዎች ዋንጫ፣ የአውሮፓ ሱፐር ዋንጫ፣ ኢንተርኮንቲናል ዋንጫ እንዲሁም የዓለም የክለቦች ዋንጫ።
ፈርጊ የዩናይትድ አሠልጣኝ በነበሩበት ጊዜ ሳያነሱት የቀረ ዋንጫ፣ ያላጣጣሙት ድል የለም በማለት ደፍሮ መናገር ይቻላል።
አሠልጣኙ ድልን የተቀደጁት በኦልድ ትራፈርድ ብቻ አይደለም የስኮትላንዱ የአበርዲን አሠልጣኝ ሳሉም በዋንጫ ተንበሽብሸዋል።
የ81 ዓመቱ ፈርጊ ‘አሌክስ ፈርጉሰን’ በተሰኘው የግለ-ታሪክ መጽሐፋቸው ከ27 ዓመታት በኋላ አሠልጣኝነት ለምን እንደለቀቁ ያወሳሉ።
2012 (እአአ) ሊጀመር ሲቃረብ “ጡረታ ልወጣ ነው” ሲሉ ለሚስታቸው ካቲ ነገሯቸው።
“ለምን ብለህ?” ሚስታቸው ጠየቁ።
ካቲ በወቅቱ እህታቸውን በሞት አጥተው ጎስቆል ብለው ነበር። ትንሽ ጊዜ ቢውስድባቸውም በፈርጉሰን ሐሳብ ተስማሙ።
“ከዚያ ቀጥሎ ለክለቡ ማሳወቅ ነበረብኝ። መጋቢት 31 ጡረታ ልወጣ እንደሆነ ለክለቡ አሳውቅሁ” ይላሉ በመፅሐፋቸው።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ግሊ አንጋፋ ከሚባሉት ክለቦች እንዱ የሆነው ዩናይትድ ይህን ዜና እንደምንም አምቆ ቆየ።
ፈርጊ በመጨረሻ ጨዋታቸው ከዌስት ብሮም 5 ለ 5 ተለያዩ። ይህን ጊዜ ዜናው ይፋ ሆኖ የዓለም መገናኛ ብዙኃን የስፖርት ቀዳሚ ዜና እና መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የሪያል ማድሪድ ጨዋታ
ፈርጉሰን ስለመልቀቃቸው ዜና መጀመሪያ የነገሩት በውቅቱ የዩናይትድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለነበሩት ዴቪድ ጊል ነው።
ስብሰባውን የጠሩት ጊል ናቸው። ነገር ግን የስብሰባው ዋና ዓላማ እራሳቸው [ጊል] ሥራ ሊለቁ እንደሆነ ለፈርጊ ሊያሳውቋቸው እንጂ ዋናውን ዱብ ዕዳ ለመስማት ተዘጋጅተው አልነበረም።
ከ10 ዓመት በላይ ከፈርጉሰን ጋር የሠሩት ጊል፣ ለአሠልጣኙ ዜናውን ሊነግሯቸው የፈለጉት ሁለቱ ካላቸው ቅርበት አንፃር ነው።
ጊል ሕልማቸው የኃያሉ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል መሆን ነበር።
ነገር ግን ፈርጊ ዜናውን ሲያረዷቸው ደንገጡ። ዜናውን እስኪያላምጡ ጊዜ ወሰደባቸው።
ይህም ዜና ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ማንም ሳይሰማው ምስጢር ሆኖ ለሦስት ወራት ቆየ።
ዜናውን የሰሙት ጥቂት የዩናይትድ ባለሥልጣናት እና የክለቡ ባለቤት የሆኑት የግሌዘር ቤተሰብ ናቸው።
ነገር ግን ወደኋላ ዞር ብለን ስናየው ፈርጉሰን ዩናይትድ ሊለቁ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።
መጋቢት 5፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አድርጎ በአከራካሪ መንገድ ከውድድሩ ተሰናበተ።
በጊዜው ማድሪድን እየመራ የነበረው ዩናይትድ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጣበት። ናኒ። ይህን ያዩት ፈርጉሰን ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ንዴታቸውን ገለጹ።
ፈርጉሰን ሲናደዱ አጠገባቸው ያሉ ረዳቶቻቸው ብቻ ሳይሆን የዱር አራዊት ይደነግጣሉ።
ጨዋታው ሲጠናቀቅ የቡድኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጊል የፈርጉሰን ምክትል ወደነበሩት ማይክ ፌላን አቅኑ።
ፈርጉሰን ከቢቢሲ ጋር ጥል ነበሩ። ቢቢሲ በአንድ ዘጋቢ ፊልም ልጃቸው ጄሰንን በማንሳቱ ፈርጊ ለብሪታኒያው የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ቃለ-ምልልስ ላለመስጠት ምለው ለሰባት ዓመታት ሸፍተው ነበር።
በዚህም ምክንያት ጊዜ ቃለ-መጠይቅ ይሰጡ የነበሩት ማይክ ፌላን ነበሩ። አልፎም ፈርጊ ለአንድ ሚድያ ብቻ ከጨዋታ በኋላ ድምፃቸውን የሚሰጡት ከአውሮፓ ጨዋታዎች በኋላ ነው። ይሄም የሆነው ሕጉ ስላስገደዳቸው እንጂ ፈልገው አልነበረም።
የጨዋታው ክብደት እና አከራካሪነት እንዳለ ሆኖ ፈርጉሰን ግን ቃለ-መጠይቅ መስጠት ስለማይወዱ ፌላን ወደ መገናኛ ብዙኃን ድምፅ ማጉያ እንዲሄዱ ጊል አዘዙ። ፈርጊም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ።
ነገሩ ወዲህ ነው። ጊል፤ ፈርጉሰን በንዴት ሌላ ነገር እንዳይናገሩ ስለፈሩ ነው ይህ ያደረጉት።
ሥራ አስፈጻሚው መጥተው ፌላን “ፈርጊ በጣም ብስጭት ውስጥ ስለሆኑ መገናኛ ብዙኃንን ማናገር ፈቃደኛ አይደሉም” አሉ።
ፈርጉሰን እና ጊል የሚያውቁት፤ ፌላንን ጨምሮ ሌሎች ምንም ያልገባቸው ነገር ፈርጉሰን እንዲያ የተበሳጩት የመጨረሻው የቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያቸው ስለሆነ ነበር።
ዕቅድ ማውጣት
ሚያዚያ 2013 (እአአ) መጨረሻ ላይ የፈርጊን መልቀቅ ዜና የሰሙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ጀመረ። እንዲያም ሆኖ ዜናውን የሰሙ አፋቸውን ይዘው እንዲቀመጡ ታዘዙ።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሮቢን ቫን ፐርሲ አስተን ቪላ ላይ ሃት-ትሪክ ሠርቶ ዩናይትድ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋገጠ።
የዩናይትድ ተጫዋቾች የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን በማንሳታቸው በክፍት አውቶብስ ከተማዋን ይዞራሉ ብሎ ማንም አልጠበቀም።
በ2008 (እአአ) የፕሪሚዬር ሊግ እና የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባነሱ ወቅት እንኳ ይህን አላደረጉም።
በክለቡ ውስጥ መሰል ዝግጅቶችን የሚያሰናዱ ሰዎች አውቶብሱን እንዲያሳጥቡና ቀለም እንዲያስቀቡ ተነገራቸው። ቢሆንም የተሰጣቸው “ለ20ኛ ጊዜ ዋንጫ ስላነሳን” የሚል ምክንያት እንጂ ለፈርጉሰን መሸኛ ነው የሚል አይደለም።
የፈርጉሰን ጡረታ መውጣት ዜና ረቡዕ ግንቦት 8/2013 (እአአ) እንዲነገር ቀጠሮ ተያዘ።
ማክሰኞ ጠዋት የክለቡ ሠራተኞች ስብሰባ ተጠርተው አንድ ትልቅ ዜና እንዳለ ተነገራቸው። ሠራተኞቹ የዝውውር አሊያም የስፖንሰር ጉዳይን የተመለከተ ይሆናlእ ብለው ነበር የጠበቁት።
ነገር ግን ስብሰባው ሲበተን አንድ ድምፅ “ንጉሡ አረፉ። ንጉሡ ለዘላለም ይኑሩ” አለ። አዳራሽ ውስጥ የነበሩ የፈርጉሰንን የስንበት ዜናን የሚያውቁ ሰዎች ቆሌያቸው ተገፈፈ።
ስብሰባ ከተበተነ በኋላ ሁሉም ጥጉን ይዞ ቡናውን ፉት እያሉ ይንሾካሸክ ገባ። ይሄኔ ነው የክለቡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወሬው ከእጃቸው እንደወጣ የገባቸው።
መገናኛ ብዙኃን ጭምጭምታው ደርሷቸው ኖሮ የዩናይትድ ሠራተኞች በፅሑፍ መልዕክት እና በስልክ ያጨናንቋቸው ገቡ።
መግለጫው እና የመጨረሻው ጨዋታ
ማክሰኞ ማታ ፈርጉሰን ጡረታ ሊወጡ እንደሆነ የሚናገር ዜና ኢንተርኔቱን አጨናነቀው።
በቀጣዩ ቀን ረቡዕ ጠዋት ራደዮ እና ቴሌቪዥኑ ሌላውን ዜና እርግፍ አድርጎ ትቶ ትኩረቱን በፈርጉሰን ጉዳይ ላይ አደረገ።
ፈርጉሰን በዚህ ደስተኛ አልነበሩም። ዜናው ከእሳቸው እንዲመጣ ነበር የሻቱት።
አብረዋቸው የሚሠሩ ሰዎች ጠዋት ሥራ ሲገቡ ጠርተው ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ጠይቀው ዜናውን እሳቸው ራሳቸው እንዲናገሩ ለማድረግ አቅደው የነበረ ቢሆንም ከእጃቸው መውጣቱን ተናገሩ።
ፈርጊ በወቅቱ ጤናቸው መልካም ነበር። ሥራ የለቀቁት በጤናቸው ምክንያት መሆኑን የሚጠቁም ፍንጭ አይታይባቸውም።
ፈርጉሰን ወደ ተጫዋቾቻው ሄዱ። በተመሳሳይ ሰዓት መልቀቃቸውን የሚያረዳው ይፋዊ መግለጫ እየተሰናዳ ነበር።
ተጫዋቾቻቸው ወጣቶች ናቸውና ዜናውን በቀልድ አጅበው ተቀበሏቸው። ቁጣ ሊቀር ነዋ፤ ተመልሰው መቼ ነው የሚመጡት. . . በመሳሰሉ አስተያቶች እና ጥያቄዎች ጉዳዩን ቀለል አድርገው ተቀበሉት።
የቡድኑ ይፋዊ መግለጫ ቅንጣት ስህተት እንዳይታይበት ሆኖ ደግሞ ደጋግሞ አርትዖት ተደረጎበት እንዲዘጋጅ ተደረገ።
መግለጫው የፈርጉሰን፣ የጊል እና የጆዌል አቭራም ግሌዘርን ረዘም ያለ መልዕክት ያዘለ ነው።
መግለጫው በዩናይትድ ድረ-ገፅ ላይ ለዓለም ይፋ ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ድረ-ገፁ የጎብኝዎችን ብዛት መሸከም አቃተው።
የመጨረሻው ጨዋታቸው በኦልድ ትራፈርድ ከተካሄደ በኋላ ፈርጉሰን “ይህን ክለብ የምልቀበት ጊዜ ስለሆነ ነው ይህን ከባድ ውሳኔ የወስንኩት። ያሰብኩትን አሳክቻለሁ ብዬ አስባለሁ” አሉ።
ሚስታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን አመሰገኑ። ተጫዋቾቻቸውን እና የክለቡን ሠራተኞችንም አልረሱም። ሰር ቦቢ ቻርልተን፣ ጊል እና የግሌዘር ቤተሰብ አልቀራቸውም።
የዩናይትድ ተጫዋቾች ለፈርጉሰን ውድ የእጅ ሰዓት ስጦታ አበረከቱላቸው። የፎቶ አልበምም አከሉበት።
የንግድ ማኅበር ሱቅ ጠባቂ የነበሩት ፈርጉሰን፤ እግር ኳስ ስትጠራቸው ዐይናቸውን አላሹም። ሁሌም ስለሥራ ማውራት ይወዳሉ።
ከመጨረሻው ጨዋታ በፊትም ለቡድናቸው አባላት ያስተላለፉት መልዕክት ይህ ነበር። “እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ተጫወቱ፤ ለማሸነፍ ተፋለሙ” የሚል ምክር ለገሱ።
ምንም እንኳ በመጨረሻው ጨዋታ የዌስት ብሮሙ ሮሜሉ ሉካኩ ሃት-ትሪክ ሠርቶ ውጤቱን ከ5 ለ 2 ወደ 5 ለ 5 ቢቀይረውም ፈርጊ የሚታወቁበትን ቁጣ የሞላበት ፊት አላሳዩም።
የፍፃሜው ፍፃሜ
በመጨረሻው ጨዋታ ምሽት የክለቡ ቁልፍ ሰዎች ተሰባስበው ወደፊት ምን እናድርግ ሲሉ አንድ ሁለት እየተጎነጩ ተወያዩ።
ዴቪድ ሞይስ ጉምቱውን አሠልጣኝ ተክተው ሲመጡ ፈርጊ ምንም ዓይነት ጫና ማሳደር ስላልፈለጉ ሙሉ በሙሉ ነው ዙፋኑን ያስረከቧቸው።
አስገራሚ የነበረው ውሳኔ ዴቪድ ሞይስ የዩናይትድ አሠልጣኝ ሆነው በይፋ የተቀላቀሉት ከመጨረሻው ጨዋታ አንድ ወር ተኩል በኋላ ነው።
በሚቀጥሉት 12 ወራት ፈርጉሰን ብቻ ሳይሆን፤ ጊል፣ ሰኮልስ፣ ፌላን፣ የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ኤሪክ፣ ቪዲች እና ፓትሪስ ኤቭራ ዩናይትድን ለቀቁ።
ጊግስ ጫማ ሰቀለ። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የወጣቶች ቡድን አሠልጣኙ ፖል እና የአካዳሚ ዳይሬክተሩ ብራያን ዩናይትድን ለቀው ወጡ።
እነሆ የፍፃሜው ፍፃሜ ሆነ። ማንቸስተር ዩናይትድ ያለ ፈርጉሰን ማንቸስተር ዩናይትድ መሆን አቃተው።