ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ ከዩክሬን የገዛው የእርዳታ ስንዴ ኢትዮጵያ ደረሰ
ከዩክሬን የተገዛውን የእርዳታ እህል የጫኑ ስልሳ የጭነት መኪናዎች በዛሬው እለት፣ ጳጉሜ 2/ 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ደረሱ ።
እህሉ የተገዛው በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅት ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ለሚደረገው እርዳታ እንዲውል የታሰበ ነው።
ስንዴውን የጫነችው መርከብ በጥቁር ባህር የምትገኘውን የዩክሬኗን ፒቭደንኒን ለቃም ከወጣች አንድ ወር ያህል ገደማ አስቆጥሯል ።
ባለፈው ሳምንት ጂቡቲ የደረሰችው መርከብ የሊባኖስ ባንዲራ ያላትና ብሬቭ ኮማንደር የምትሰኝ ሲሆን፣ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ጭነት መያዟ ተነግሯል።
ሩስያ በዩክሬን ያደረገችውን ወረራ ተከትሎ ወደ አፍሪካ የደረሰው የመጀመሪያው የእህል ጭነት ነው።
ኢትዮጵያ የደረሰው የስንዴ አቅርቦት ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ በችጋር ላይ ያሉ ሰዎችን ለአንድ ወር ለመመገብ የሚረዳ መሆኑን የአለም ምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ ተናግሯል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ክሌር ኔቪል ከዚህ ቀም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ስንዴው ተቋሙ በጦርነት እና በአስከፊ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ለመመገብ የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል።
ከ22 ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት ችግር ላይ ያሉ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን እንዲሁም በአፋር እና በአማራ ክልሎች ያሉ ሕዝቦችን ለመርዳት እንደሚውል ክሌር አክለው ገልጸዋል።
ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥትና የአማራ ልዩ ኃይል በጥምረት ከትግራይ ኃይሎች እየተደረገ ያለው የርስ በርስ ጦርነት ማገርሸቱ የእርዳታ አቅርቦቱን ሊያደናቅፍ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምግብ፣ መድኃኒትና እና ነዳጅ እገዳ በተጣለባት ትግራይ ማስገባት ችሏል።
ነገር ግን የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተርማይክል ደንፎርድ እንዳሉት ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ ለትግራይ ክልል የሚደርሰው እርዳታ ቆሟል ብሏል።
"በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ውስጥ የምናደርገው እንቅስቃሴ ቆሟል። በአሁኑም ወቅት የፀጥታውን እና ህዝቡን የምንደርስበትን ሁኔታ እየገመገምን ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት ሶስት ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ እና የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖራቸው እጅግ አስከፊ ነው” ብለዋል ማይክል ደንፎርድ።
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ በመመታቷ እና በበርካታ ግጭቶች ሳቢያ 20 ሚሊዮን የሚሆነውን ሕዝቧን እርዳታ የሚሻ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ጂቡቲ የደረሰውም ስንዴ ከሚያስፈልገው ጋር ሲነፃጸር የውቅያኖስ ጠብታ ያህል ነው ተብሏል።
ሐምሌ 15/2014 ዓ.ም. ሩሲያ በዩክሬን ወደቦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ያነሳች ሲሆን፣ ይህም መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል ባለው መተላላፊያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ አስችሏቸዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር መተላለፊያ (ኮሪደር) ሰኔ 15/2014 ዓ.ም. ከተከፈተ ጀምሮ 560 ሺህ ቶን እህል እና ሌሎች የምግብ ዓይነቶች ከዩክሬን ወደቦች ተልከዋል።
ይህ ጭነት 451 ሺህ 481 ቶን በቆሎ፣ 41 ሺህ 622 ቶን ስንዴ፣ 6 ሺህ ቶን የሱፍ ዘይትን ይዟል።
70 በመቶው የሚሆነው እህልና ምግብ ወደ ቱርክ፣ ኢራን እና ደቡብ ኮሪያም አቅንቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን እህል ዋነኛ ገዢ ሲሆን፤ ይህንንም እህል በረሃብ አደጋ ውስጥ ወደሚገኙ አገሮችም ይልካል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን 60 ሺህ ቶን ስንዴ ከዩክሬን በመግዛት በችግር ላይ ላሉ አገራት ለመላክ ችያለሁ ብሏል።