አሜሪካ እና ዩኬ በሁቲዎች ላይ አዲስ ጥቃት ከፈቱ

የፎቶው ባለመብት, UK MOD © CROWN COPYRIGHT 2024
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን የሁቲ አማጽያንን ኢላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ።
ፔንታገን እንዳለው ስምንት ኢላማዎች መትተዋል። ይህም የሁቲዎችን ሚሳኤል ማከማቻና የስለላ ማዕከል ያካትታል።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ቀይ ባሕር ላይ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን ጥቃት ሲያደርሱባቸው ነበር።
አሜሪካ እና ዩኬ “የንግድ ሂደቱን በነጻነት ለማሳለጥ” እየሞከሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ተጨማሪ ጥቃቶች ሁቲዎች ላይ እንደሚሰነዘርም ሁለቱ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
“አላማችን ቀይ ባሕርን ወደቀድሞ መረጋጋት መመለስና ውጥረት ማርገብ ነው። የሰዎችን ሕይወትና የዓለም ቀዳሚው በሆነው የውሃ መጓጓዣ የንግድ ፍሰትን ከመጠበቅ ወደኋላ እንደማንል የሁቲ አመራሮች እንዲያውቁ እንሻለን” ብለዋል።
አገራቱ ስምንት ጊዜ ነው ሁቲዎችን ኢላማ ያደረጉት። አውስትራሊያ፣ ባሕሬን፣ ካናዳ እና ኔዘርላንድስ ድጋፍ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ተዋጊ ጀት ዩኤስኤስ አይዝንሀወር በዚህ ጥቃት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን አሜሪካና ዩኬ ሌሎች ከባድ መሣሪያዎችንም ተገልግለዋል።
“የአየር ኃይላችን ኢላማ ጠቋሚ መሣሪያ ተጠቅሟል። የተለያዩ ኢላማዎችንም መቷል። ይህም በሰንአ የአየር ክልል ነው። እነዚህ አካባቢዎች በቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ውለው ነበር” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
ዩኬ ጥልቅ ምርመራ አድርጋ ዕቅድ ካወጣች በኋላ ጥቃቱ እንደተፈጸመ ገልጻለች። ይህም የሲቪሎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ነው።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ ጥቃቱ “መቋቋም ካልተቻለው” የሁቲዎች ጥቃት “ራስን መከላከል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“የሁቲን አቅም ማዳከም ነው አላማው። ዓለም አቀፍ ንግድን ስጋት ውስጥ የመክተት ዕድላቸውን ለመቀነስ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው” ብለዋል።
በሁቲ የሚተዳደረው አል ማሲራ የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደዘገበው በየመን፣ ሰንአ፣ ታይዝ እና ባይዳ ግዛቶች ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
በመዲናዋ አቅራቢያ ያለው አል-ዳሊሚ የአየር ኃይል መቀመጫ ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል።
ከአስር ቀናት በፊት አሜሪካና ዩኬ ጥምር ጥቃት በሁቲ አማጽያን ላይ ቢሰነዝሩም፣ ሁቲዎች አሁንም ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል።
በየመን በኩል የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በስህተት የሩሲያ ነዳጅ የጫነ መርከብ ተመቷል።
ፔንታገን እንዳለው አማጽያኑ ጥቃት ለመፈጸም ሲያዘጋጇቸው የነበሩ ሚሳኤሎች በጥቃቱ ተመተዋል።
የምዕራባውያን የደኅንነት መረጃ እንደሚጠቁመው ቢያንስ 30% የሁቲ ሚሳኤሎች ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል።
ሁቲዎች እስራኤልን ኢላማ በማድረግና ሐማስን በመደገፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
አሜሪካና ዩኬ መሪዎቻቸው ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው ለሁለተኛ ዙር ጥቃት የከፈቱት።
ሁለቱ መሪዎች “ለንግድ ነጻነት፣ ለዓለም አቀፍ ንግድ መሳለጥና ጥቃትን ለመከላከል” ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸው ተዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ ጥቃት መጀመሯን ተከትሎ ጥቃት መፈጸም የጀመሩት ሁቲዎች ከኅዳር ወዲህ በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላብ ብዙ ጥቃት አድርሰዋል።
ይህ የባሕር መተላለፊያ ለንግድ መርከቦች መጓጓዣነት በመዋል ቀዳሚ ከሆኑት መካከል ነው።












