ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ ዐይኑ የጠፋው ደራሲ ሰልማን ሩሽዲ አዲስ መጽሐፍ እየጻፈኩ ነው አለ
እንግሊዛዊው ዝነኛ ደራሲ ሰልማን ሩሽዲ ዳግም ወደ ጽሑፍ መመለሱን ይፋ አደረገ።
ሥመ ጥሩ ደራሲ ሩሽዲ ባለፈው ዓመት ኒውዮርክ ላይ መድረክ ላይ ወጥቶ ንግግር ለማድረግ ሲዘጋጅ አንድ ግለሰብ በድንገት ደርሶ በተደጋጋሚ በስለት ወግቶት ነበር።
ሩሽዲ ጥቃቱን ተከትሎ ለስድስት ሳምንታት ሆስፒታል ነበር። ዘለግ ላሉ ቀናትም ራሱን ስቶ ቆይቷል።
በጥቃቱ አንድ ዐይኑን ያጣው ደራሲ ሰልማን ሩሽዲ አሁን ወደ ድርሰቱ ዓለም ተመልሻለሁ ብሏል።
መቼ ድርሰቱን እንደሚጨርስ የተጠየቀው ሰልማን ሩሽዲ “ያን ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም፤ አሳውቃችኋለሁ” ብሏል።
የዝነኛው ቡከር ሽልማት አሸናፊ የሆነው ሰልማን ሩሽዲ ትናንት በዊንሰር ካስል የሽልማት ድግስ ተገኝቶ ነው አዲስ መጽሐፍ እየጻፈ እንደሆነ ያበሰረው።
በዚህ በዊንሰር ካስል በተደረገ የሕይወት ዘመን ሽልማት ሥነ ሥርዓት ከልዕልት አን እጅ ሜዳሊያ ተቀብሏል።
“ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፤ ቢሆነም አሁን ወደ ሥራ ተመልሻለሁ” ሲል ንግግር ያደረገው ሰልማን ሩሽዲ ‘ቢሆንም ግን ድሮ እንደነበርኩት ፈጣን አንባቢ አይደለሁም አሁን” ሲል አንድ ዐይኑ መጥፋቱ ያሳደረገበትን ተጽእኖ ተናግሯል።
ሰልማን ሩሽዲ እስልምናን የሚያንቋሽሽ “ሳታኒክ ቨርስስ” የተሰኘ ድርሰት ጽፈሃል በሚል ነበር በኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ በተገኘበት የሞት ፍርድ የተረፈደበት።
ይህም የሆነው ከ35 ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 1988 ዓ/ም ነበር።
ትናንት ከፍተኛ የቤተ መንግሥት ሉዑላኑ በተገኙበት የተበረከተለት ሽልማት በኮሜንዌልዝ ለሚገኙና የሕይወት ዘመን አገልግሎትን በኪነ ጥበብ፣ ሕክምና፣ ሳይንስ፣ ወይም አስተዳደር ለሰጡ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ታላቅ እውቅና ነው።