አከራካሪ የሆነው የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት የማሻሻል ጉዳይ

የደርግ ሥርዓት ውድቀትን ተከትሎ ሥልጣን የተረከበው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከተመራችበት አሃዳዊ አስተሳሰብ በተለየ የሚቃኝ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት አጽደቋል።

አዲሱ ሕገ መንግሥት በተለይ ‘ብዝሃነትን’ የሚያንጸባርቅ ተብሎ ሲነገርለት የቆየ ቢሆንም፤ አንዳንድ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ያገለለ እና ልዩነት ላይ ያተኮረ ተብሎም ይተቻል።

ይህ ፌዴራላዊ ሕገ መንግስቱ በ1987 ዓ.ም፤ እንዲሁም 1997 ዓ.ም ሁለት ማሻሻያዎች እንደተደረገበት መረጃዎች ያመላክታሉ።

የመጀመሪያው ስለ ግብር አከፋፈል ሥርዓት የሚመለከተው አንቀጽ 98 ሲሆን፣ ሁለተኛው ማሻሻያ ደግሞ የሕዝብ ቆጠራን የሚመለከተው አንቀጽ 103 ነው።

ይህ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት ከቀበሌ እስከ ወረዳ ለሁለት ዓመት ያህል ሕዝባዊ ውይይት እና ጉባኤ እንደተካሄደበት ይነገራል።

በተጨማሪም የአገሪቱ ምሁራን እንዳጠኑት እና ተጋርጦ የነበረው የመበታተን አደጋ የታደገ እንደሆነ ቢነገርለትም በተለይ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞችን ያገለለ በማለት ሂደቱን የሚተቹም አልጠፉም።

ይህ መሠረታዊ ለውጥ ሳያደርግ ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው ሕገ መንግሥት የሚቀርቡበትን ቅሬታዎች እና ትችቶችን መሠረት ያደረገ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ የሚጠይቁ አካላት ነበሩ።

ይህ ሕገ መንግሥት ከያዛቸው አንቀጾች መካከል አንዳንዶቹ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የተለወጡ ነገሮች መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ።

ለዚህም እንደማሳያ ሕገ መንግሥቱ ለዘጠኝ ክልሎች እውቅና ቢሰጥም ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በአገሪቱ ሁለት አዳዲስ ክልሎች መፈጠራቸው እና ሌላ ሦስተኛ ክልል ለመመስረትም ሕዝበ ውሳኔ መካሄዱን ያነሳሉ።

እንዲሁም አምስት ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑም በመንግሥት ዘንድ ፍላጎት እንዳለ ተነግሯል።

በአገር ውስጥ በተለያዩ ምሁራን እና ፖለቲከኞች የሚነሱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚልም በፕሮፌሰር በየነ የሚመራው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት ጥናት አካሂዷል።

የጥናቱ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላም ትችታቸውን የሰነዘሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ ደግፈው አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖችም አሉ።

ለመሆኑ ጥናቱ እንዴት ነው የተካሄደው? ምን ያህል አካታች ነው? የማንን ፍላጎት ነው የሚያንጸባርቀው? ለምንድነው አወዛጋቢ የሆነው የሚሉትን እና የመሳሰሉት ለሁለት ምሁራን እና ፖለቲከኞች ጥያቄ አቀርበናል።

በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት ማን ተሳተፈ?

በፖሊሲ ጥናት ተቋም አማካይነት በተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናት በተለይ የቡድን መብቶችን በሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተመረጡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ላይ ያተኮረ ነው።

በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ‘እኛ ብሔር ብሔረሰቦች’ የሚለውን፣ በአንቀጽ 8 ላይ “ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” የሚለው፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ፣ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ፣ የክልሎች አደረጃጀት እና የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ‘እስከ መገንጠል’ የሚለውን አንቀጽ 39 እንዲከለስ የሚል ሐሳብ ቀርቧል።

አወዛጋቢው የአዲስ አበባ ጉዳይም እንዲሁም የሕገ መንግሥት ጉዳይ ያልሆነው ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከት ርዕሰ ጉዳይ በጥናቱ ውስጥ ተካትቷል።

ይሄ ለሁለት ዓመት መደረጉ የተገለጸው ጥናት፣ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ በነበረችበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ መካሄዱ እና ጥቅምት 2015 ዓ.ም መጠናቀቁንም ያስረዳል።

እንዲሁም የትግራይ ክልል በጥናቱ አለመካተቱን ቢገለጽም፣ ይህንን የፌዴሬሽኑ አባል ያላካተተ የማሻሻያ ሃሳብ እንዴት እንደሚያስታርቀው ግን የተባለ ነገር የለም።

በተቀሩት ክልሎች ግን ከ41 አካባቢዎች ባሉ ብሔሮች ላይ ሁለት የጥናት ዘዴዎችን በመጠቀም በአጠቃላይ ለ1123 ሰዎች መጠይቅ [Questionaire] መበተኑ፣ እንዲሁም በተመረጡ ሰዎች ላይ በግል እና በቡድን ቃለ መጠይቅ መድረጉ ተገልጿል።

አብዛኞቹ [80 በመቶ] መላሾች ስለ ሕገ መንግሥቱ ግንዛቤ አለን ማለታቸውንም ጥናቱ አመልክቷል።

የሕግ መንግሥት ማሻሻያ ለምን አሁን?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ እንዲሁም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጥያቄ ላይ እምብዛም ተቃውሞ የላቸውም።

ሁለቱ ምሁራን ግን በሂደቱ፣ በይዘቱ እና በጊዜው ላይ ግን አይስማሙም።

ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፤ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል “አሁን ትክክለኛ ጊዜው ነው” የሚል እምነት አላቸው። “ምክንያቱም የብዙዎቹ ችግሮች ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው” ባይ ናቸው።

“ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በርካታ አወዛጋቢ ድንጋጌዎች አሉ። ለልዩነት በር የሚከፍቱ አንድነትን የሚያላሉ ድንጋጌዎች አሉ። በተግባርም ላለፉት 30 ዓመታት ያየነው ያንን ነው። ሕገ መንግሥቱ በተሟላ መልኩ ቢከለስ ወይንም ቢሻሻል ብዙዎቹ ችግሮች ይቀረፋሉ። ከዚያ በኋላ ግን የዴሞክራሲ ባህል የመግባባት እና የመነጋገር ልምድ መዳበር አለበት” ይላሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚለውን ሃሳብ ባይቃወሙትም፣ መቅደም ያለበት የጋራ መግባባት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት እንደሆነ ያምናሉ።

ፕሮፌሰር መረራ እንደሚሉት ሕገ መንግሥት አገራዊ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ መቀየር ይቻላል። ማሻሻያው ራሱ የዚህ መግባባት መንፈስ ውጤት እንጂ መነሻ ሊሆን አይችልም። በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መቅደም አለበት የሚል አቋምም አላቸው።

“ሕገ መንግሥት መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርዓን አይደለም። መቀየር ይቻላል። ነገር ግን የአገሪቷን ችግር ይፈታል ወይስ ተጨማሪ ችግር ያመጣል የሚለው ነው መታየት ያለበት” ይላሉ።

ሕገ መንግሥቱ መቀየር ላይ አሁንም ጉልህ ድርሻ ያለው አገሪቷን የሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ እንደሆነ የሚያምኑት ዶ/ር መረራ “አሁንም አንድ ፓርቲ ብቻ የአገሪቷን ፖለቲካ በበላይነት በተቆጣጠረበት ሁኔታ ሕገ መንግሥቱን መቀየር አገሪቷን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል” የሚል ስጋት አላቸው።

የማሻሻያ ሃሳቡ ለምን አወዛጋቢ ሆነ ?

አገሪቱ ከሰሜኑ ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መረጋጋት ለመፍጠር ጥረት በምታደርግበት ሁኔታ ላይ ብትሆንም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ግጭቶች ቀጥለዋል።

በትግራይም ቢሆን ገና እልባት ያላገኙ ጉዳዮች አሉ።

“አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት የለም” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ። “ሕገ መንግሥቱ የሚቀየር ከሆነ የብሔሮች መብት እና የክልሎችን ድንበር ለማፍረስ መሞከር በአገሪቷ ውስጥ እሳት እንደማቀጣጠል እንዳይሆን” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ዶ/ር ሲሳይ “አወዛጋቢ የሆነበት አንደኛው እና ዋነኛው ምክንያት ሕገ መንግሥቱ የአሸናፊዎች ስለሆነ ነው። በጊዜው በተካሄደው የትጥቅ ትግል ተሸናፊ ተደርገው የተወሰዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዳይሳተፉ ተከልክለው ነበር።

“ሁለተኛው ብሔር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ያሸነፉት። በዚህ ምክንያት ሁሉም ነገር ብሔር ወይም ቋንቋ ላይ የተመሰረተበት ሁኔታ ነበር። በዚህም አገራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ወይም አገራዊ የሆነ ዕይታ የነበራቸው ፖለቲከኞች እንዲገለሉ ተደርገው ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር መረራ አንድ ‘አገር የሚመራ ፓርቲ’ ሕገ መንግሥቱን መቀየር ከሞከረ ግን ያለውን ችግር ሊያባብስ እንደሚችል ይሞግታሉ።

“የአገሪቷን ፖለቲካ ሁኔታ ወደ አንድ የሚያግባባ ሁኔታ ሳያመጡ መስማማትን የሚጠይቅ ሕገ መንግሥትን መቀየር ችግር ሊያመጣ ይችላል። ለሚመጣው ችግርም ትልቅ ኃላፊነት የሚወስደው አገሪቷን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ይሆናል” ይላሉ።

የሕገ መንግሥት ማሻሻል የማን ፍላጎት ነው?

ባለፉት 30 ዓመታት ሕገ መንግሥቱ መተግበር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ ልሂቃን ሕገመንግሥቱ በታኝ እና የአገር አንድነትን የሚያላላ ነው የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል።

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በዚህ የተነሳ ዋል አደር ሳይባል ሕገ መንግሥቱ መቀየር አለበት ከሚሉት መካከል ናቸው።

“‘እኛ አይወክለንም’ ብለው በተለይም የአማራ ሕዝብ እና ውህድ ኢትዮጵያውያን የሚባሉት፣ ከተለያየ ማኅበረሰቦች የተወለዱ፣ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ አካል ነን ማለት የሚቸገሩ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው የሚጠሩ፣ በዚህ ሕገ መንግሥት ዕውቅና አላገኙም። በየትኛውም ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዲሳተፉ መብታቸው እንዲከበር አልረተደረገም” ይላሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ግን “ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር የአማራ ልሂቃን ላለፉት 30 ዓመታት ሲጠይቁ ነበር። በአማራ ልሂቃን የተመሠረቱ ፓርቲዎችም አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ይጠላሉ” በማለት ሃሳቡን ቢጋሩም በዚሁ መልኩ ማሻሻሉን አይደግፉም።

ዶ/ር ሲሳይ ግን “ከሁሉ በላይ ለልዩነት እንጂ ለአንድነት ትኩረት ያልሰጠ ሕገ መንግሥት ነው። የሉዓላዊ ሥልጣን ለብሔር ብሔረሰቦች ነው የተሰጠው። ‘እኛ ብሔር ብሔረሰቦች’ ብሎ እንጂ ‘እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች’ ብሎ ወደ አንድ ሊያመጣ የሚችል የሚያስተሳስር ነገር የለውም” በማለት ይከራከራሉ።

ስለጥናቱ የመረጃ አሰባሰብ ምን ይባላል?

መረጃ አሰባሰቡ ላይ ችግር እንዳለበት የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር መረራ፣ “ታማኝነቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል” በማለት ጥናቱ በአግባቡ እንዳልተካሄደ ይናገራሉ።

ዶ/ር መረራ “በጣም ያስገረመኝ ነገር 120 ሚልዮን ሕዝብ ባለበት አገር፤ ወደ አንድ ሺህ ሰው አናግረናል ነው የሚሉት። አብዛኛውን ደግሞ 80 በመቶው በከተማ ነው ያናገሩት፤ አብዛኛው ሰው [85%] ገጠር ውስጥ እንደሚገኝ እያወቁ፤ ይህንን የመሰለ ትልቅ ስህተት ሠርተዋል” በማለት የሥነ ዘዴ ችግር እንዳለበት ያስረዳሉ።

“እንደዚያም ሆኖ የት ሄደው እንደጠየቁ አይታወቅም። ኦሮሚያ ክልል ለምሳሌ የት ሄደው ነው የጠየቁት? የፖለቲካ ጨዋታ ነው የሚመስለው” በማለት ጥናቱን ይተቻሉ።

ዶ/ር ሲሳይ ደግሞ “የክልሎች አደረጃጀትን ካየን ቋንቋን እና ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ ነው እንጂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን ወይንም አስተዳደራዊ ፍትህን፣ የራስ በራስ ማስተዳደር አቅምን የተፈጥሮ ሃብትን የሰው ሃብት ስምሪትን የህዝብ ብዛትን የቆዳ ስፋትን እንደመስፈርት አልወሰደም” በማለት ያለውን የፌደራል ሥርዓት ቅርጽ ይተቻሉ።

“ስለዚህ ትልቅ ክልል አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ በትልቅ ክልል ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። የሆነ ትንሽ ክልል ደግሞ ተፈጥሯል። ይሔ አንዱ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” በማለት በመልከዓ ምድር መሠረት ያደረገ እንዲሆን የሚል የጥናቱን ዋና ምክረ-ሃሳብ ይደግፋሉ።

“ጥናቱ በቋንቋ የተካለሉት ክልሎች እንዲፈርሱ ነው የሚጠቁመው” የሚሉት ዶ/ር መረራ “አንዳንዶቹ በተለይ የትግራይ እና የኦሮሚያ ክልሎች እንዲፈርሱ ሲወተውቱ” ነበር ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ አጥኚዎቹ ከገጠር ሕዝብ ይልቅ በከተሞች ላይ ማተኮራቸውን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “መደምደሚያው ሆን ተብሎ ወደ ሚፈለገው ውጤት እንዲያዘንብል አድርገዋል” ብለው ይተቻሉ።

“ሲዳማ ስንት የሰው ሕይወት ጠፍቶበት በቅርቡ ነው በስንት መከራ ክልል የሆነው። አሁን አንድ የሲዳማ ተወላጅ ‘ክልሌ ይፈርስ’ ብሎ ሃሳብ ይሰጣል ማለት የማይመስል ነው’። በአፋር ክልል ይፍረስ ብሎ መልሷል’ ይላል። ይሄ ለማመን የሚከብድ ነገር ነው” በማለት በውጤቱ ላይ ፕሮፌሰር መረራ ጥያቄ አንስተዋል።

የጥናቱ መረጃ አሰባሰብ ላይ ያሉ ከጥናቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጥናቱን በበላይነት ከመሩት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

ማሻሻያው የሕገ መንግሥቱን መሠረት ይቀይራል?

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ አለመግባባት ከሚነሳባቸው አንቀጾች መካከል አንዱ አንቀጽ 39 ነው። የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥናትም ይህንን አንቀጽን እና ክልሎች የተዋቀሩበት መንገድ ዳሷል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው በአማራ እና በአፋር ክልሎች አብዛኞቹ መላሾች ይህንን አንቀጽ [በተለይ ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚለውን] እንዲቀየር የሚፈልጉ መሆናቸውን ያመላከተ ሲሆን፣ በተቀራኒው በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተገኙ መላሾች “ይህ አንቀጽ እንዳይነካ” ፍላጎት አላቸው።

ዶ/ር ሲሳይ “አንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥርን 1 ሲታይ አገር ለመመሥረት በቀላሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብሔር ብሔረሰቦች መገንጠል እንደሚችሉ ብሔር ብሔረሰብ መባል ብቻ በቂ እንደሆነ ተደርጎ የተቃኘበት ሁኔታ አለ። ሌሎች ብዙ ተመሳሳይ ነገሮችን ማንሳት እንችላለን በዚህ ምክንያት ይመስለኛል አወዛጋቢ የሆነው” በማለት አንቀጹ እንዲነሳ ይደግፋሉ።

ፕሮፌስር መረራ በዚህ አይስማሙም።

“ብዙ ሰው ይህንን አንቀጽ እንደ መገንጠል መብት ብቻ አድርጎው ነው የሚያየው። ነገር ግን የብሔሮችን መብት እና ምን ዓይነት ፌደራሊዝም መኖር እንዳለበት ያመለክታል። የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአፋር እና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የ50 ዓመት ትግል አሁን ላለው ድንበር መሠረት ሆኗል። ድንበርን ማፍረስ በአገሪቷ ላይ እሳት ማቀጣጠል ሊሆን ይችላል” በማለት አጽንኦት ይሰጣሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ይህ ጥናት ተግባራዊ ከተደረገ ሕገ መንግሥቱ በመሠረታዊነት እየተናደ ነው የሚል እምነት አላቸው።

“በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር ከፈለገ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ ይችላል። አሁን ያለው ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌደራሊዝም ዝም ብሎ የሚቀየር አይደለም። ምክንያቱም ፌደራሊዝሙን ማፍረስ አገሪቷን ሊያፈርስ ይችላልና።”

አገሪቱ “ከመጀመሪያውም በእኩልነት ላይ አልተመሰረተችም” የሚል አቋም ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ፣ ሕገ መንግሥቱ ከመቀየሩ በፊት አገራዊ መግባባት እንዲቀድም አጥብቀው ይመክራሉ።

ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር 2 እና አንቀጽ 39ን በመጥቀስ ብዙ ክልሎች ብሎም አገሮች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል ብለው ያምናሉ።

“አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ 76 ወይም 77 ብሔር ብሔረሰቦች በፌደሬሽን ምክር ቤት እውቅና አግኝተዋል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ክልል የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። ይኼ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ማሰብ እንችላለን” በማለት ይህ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ይመክራሉ።

ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ምን አማራጭ አለ?

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሕገ መንግሥት፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልን በተመለከተ አንቀጽ 105 እንዲህ ይላል።

በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ፣ ይህ አንቀጽ፣ እንዲሁም አንቀጽ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኋን ብቻ ይሆናል።

ሀ/ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት፣

ለ/ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና

ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው።

አንቀጽ 39ን ጨምሮ አብዛኞቹ አሁን የማሻሻያ ሃሳብ የቀረበባቸው ርዕሰ ጉዳዮች በምዕራፍ ሦስት የሚገኙ መሆናቸው ልብ ይሏል።

ጥናቱን ያካሄዱ ባለሙያዎች ሕገ መንግሥቱ ራሱ በሚፈቅደው መሠረት መሻሻል የተሻለ ነው ብለው ቢያነሱም ወደ ማጠቃለያ ኢ-መደበኛ ባሉት መንገድ እንዲሻሻልም ሃሳብ አስፍረዋል።

ዶ/ር ሲሳይም በዚሁ ይስማማሉ።

“የመሻሻያ አንቀጹ ራሱ አንቀጽ 105 ላይ የተቀመጠው ነገር አሳሪ ነው። በፍጹም ይህ ሕገ መንግሥት አንዳይሻሻል፣ እንዳይከለስ፣ እንዳያድግ እና እንዳይቀየርም የሚከለክል ነው” በማለት ሕገ መንግሥት ሕይወት ያለው ሰነድ ነው ስለሚባል አዳዲስ ጉዳዮችን እንዲያካትት ይጠይቃሉ።

ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው “መንግሥት፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ባለው ብቻም አይደለም። ከዚያ አልፎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለመቀየር እየፈለገ ነው። አሁን ያሉት ክልሎች አስራ ሁለት ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሁሉም መስማማት አለባቸው። በዚህ ላይ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር የጋራ መግባባት መኖር አለበት የምለው ለዚህ ነው” ይላሉ።