ቻይና በአህጉረ አፍሪካ የሳተላይት ቲቪን ማስፋፋት የፈለገችው ለምን ይሆን?

በዚህ ሰሞን የቻይና አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ቤጂንግ አቅንተዋል።

በዚህ ጉባዔ የቻይናው መሪ ዢ ጂፒንግ አዲስ ነገር ወደ ጠረጴዛ እንደሚያመጡ ይጠበቃል - የሳተላይት ቴሌቪዥንን።

ከ9 ዓመት በፊት ነው የቻይና አፍሪካ ፎረም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የተካሄደው። በዚህ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ዢ ለአፍሪካ መንግስታት መሪዎች፣ በ23 የአፍሪካ ሀገራት ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ገጠራማ አከባቢዎች ዲጂታል ቲቪ የሚያገኙበት አማራጭ ይቀርባል ሲሉ ቃል ገብተውላቸው ነበር።

ይህ ፕሮጀክት አሁን ወደ መጠናቀቂያ የተቃረበ ሲሆን እስካሁን ከ9 ሺህ 600 የሚልቁ አከባቢዎች የሳተላይት ቲቪ መሰረተ ልማቶች ተዘርግቶላቸዋል።

ይህ ትልቅ ዕቅድ ይፋ በሆበት ሰዓት የአፍሪካ እና ቻይና ግንኙነት እጅግ የጠበቀ ነበር። ፕሮጀክቱ ከቻይና የእርዳታ በጀት ተቃናሽ ተደርጎ ‘ስታር ታይምስ’ በተባለ የግል ኩባንያ የሚከናወን ነው። ኩባንያው በበርካታ የፍሪካ ሀገራት ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።

ይህ ተግባር የቻይናን ‘ለጋስነት’ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ወሳኝ በሆነው (ስትራቴጂያዊ) ቀጠና ላይ ያላትን ቀላል የሚመስል ተጽህኖ (soft power) ለማጠናከር የሚረዳም ነው።

የቻይና ኢኮኖሚ እየተፈተነ ባለበት እና ቻይና ግንኙነቷን ዳግም እያጤነች ባለችብት በዚህ ሰዓት ቢቢሲ የቻይናን የሳተላይት ቲቪ ፕሮጀክት በኬንያ አራት መንደሮች ተገኝቶ ተመልክቷል።

ከኬንያ መዲና ናይሮቢ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ3 ሰዓታት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በሚገኘው ኦልታሲቲ፤ ኒኮላስ ናጉኩ ከጓደኞቹ እና ቤተሰቦቹ ጋር ቲቪ ለመመልከት ተሰባስበዋል። የሚመለከቱት ደግሞ በፓሪስ ኦሊምፒክ ኬንያውያን የሚጠበቁበት የአትሌቲክስ ውድድርን ነው።

“ስታር ታይምስን ከማግኘታችን በፊት በርከት ላሉ ዓመታት ኦሊምፒክን የምናይበት ዕድል አልነበረንም። አሁን ኦሊምፒክን ማየት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል” ይላል።

‘ስታር ታይምስ’ በአፍሪካ ሥራውን የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2008 ሲሆን አሁን ከሰሃራ በታች በአፍሪካ ትልቁ የግል ዲጂታል ቲቪ አቅራቢ ኩባንያ ነው። ኩባንያው 16 ሚሊየን ደንበኞች አሉት።

ተንታኞች ‘ስታር ታይምስ’ ያቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ በአፍሪካ እግሩን ለማስገባት እንደረዳው ይገልጻሉ።

በኬንያ ለዚህ የሳተላይት ቲቪ በወር ከ329 ሽልንግ (2.50 ዶላር) እስከ 1 ሺህ 799 ሽልንግ (14 ዶላር) ይከፈላል።

ይህ ክፍያ ከሌላኛው በአፍሪካ ትልቅ ተወዳዳሪ ከሆነው ዲኤስ ቲቪ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነው። ዲኤስ ቲቪ ከ700 እስከ 10 ሺህ 500 ሽልንግ ያስከፍላል።

‘ስታር ታይምስ’ በከፊል ከተጠቃሚዎች ክፍያ ቢያገኝም ዋናውን ትርፍ የሚሰበሰበው ለዚህ ፕሮጀክት ከተመደበው የቻይና የደቡብ ለደቡብ ድጋፍ ፈንድ ነው።

ስታር ታይምስ ‘የዲሽ ሰሃን’ ላይ የኬንያ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር እና ቀዩ “የቻይና እርዳታ” አርማዎች ሰፍረውበታል።

ዲሹን የሚገጥሙ የ‘ስታር ታይምስ’ ወኪሎች ‘ይህ ከቻይና መንግስት የተበረከተ ስጦታ ነው’ እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።

ስታር ታይምስን በተመለከተ ተደጋጋሚ ጽሁፎችን ያዘጋጁት ዶክትር አንጌላ ሌዊስ ይህ ፕሮጀክት ዋናኛ አላማው በአፍሪካ የቻይናን መልካም ገጽታ ለመገንባት እንደሆነ አጥብቀው ይከራከራሉ።

ይህ ፕሮጀክት ባለባቸው አከባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሁሉም ነገር በነጻ ይቀርብላቸዋል። ይህም ‘የዲሽ ስሃኑን’፣ የመስመር ዝርጋታውን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ይጨምራል።

ቲቪ ‘ብርቅ’ በሆነባቸው አልፎ አልፎ በሌሎች አከባቢዎች ከአገልግሎት ውጪ እየመጡ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ቲቪ በሚታይባቸው የአፍሪካ መንደሮች ‘ስታር ታይምስ’ ታሪክ ቀያሪ ተግባር ፈጽሟል ይላሉ - ዶክትር ሌዊስ።

በርካቶች ከሳተላይት ዲሽ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁ እንደመሆናቸው የተቀረውን ዓለም የሚመለከቱበትን መነጽር የቀየረ ነው ሲሉም ይክላሉ።

በምዕራብ ኬንያ ባለቸው ኤኖሚ መንደር እንደ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት ባሉ የህዝብ መገለገያዎች ውስጥ ‘ስታር ታይምስ’ ክፍያ አይጠይቅም።

በጤና ተቋማት ታካሚዎች ቲቪ እየተመለከቱ ጊዜ ሲያሳልፉ በትምህርት ቤቶች ደግሞ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ በካርቱን ፊልም ይዝናናሉ።

የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ሩት ቺላንጋት “ትምህርት ከጨረስን በኋላ በጋራ ሆነን ሁላችንም ካርቱን እናያለን። ለኛ በጣም የሚያዝናና እና ግንኙነታችንን ለማጠናከር ይረዳል” ትላለች።

ሆኖም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ኬንያውን ‘ስታር ታይምስ’ የሰጣቸው ነጻ የመመልከቻ ጊዜ ሳይጠብቁት እንደተጠናቀቀ ይናገራሉ።

‘ስታር ታይምስ’ የሚጠይቀው ክፍያ ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ቢሆንም ክፍያው በርካቶች ላይ ጫና ፈጥሯል።

በዚህም ሳቢያ አንዳንዶች ከዚህ አግልግሎት እየራቁ ነው። ይህ ደግሞ ቻይና በአፍሪካ መገንባት የምትፈልገው መልካም ስም ላይ ጥላውን አጥልቷል።

በጅማሮው ላይ ከነበረው ተስፋም የራቀ ይመስላል።በኬንያ ቼሞሪ፣ የምትኖረው ሮዝ ቼፔክሞይ “ሁላችንም የሳተላይት ዲሽ ስናገኝ በጣም ደስተኞች ነበርን። ነጻ የነበረው ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ የግድ መክፍል ነበረብን። ክፍያው ደግሞ ለኛ ውድ ነው ስለዚህ መጠቀም አቆምን” ብላለች።

‘ስታር ታይምስ’ ያለ ክፍያ የሚያሳየው የኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ብቻ እንደሆነ ክፍያ ያቆሙ ደንበኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ምልከታ ካደረገባቸው የኬንያ አራት አከባቢዎች አብዛኞቹ ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ የቀረበላቸውን የ‘ስታር ታይምስ’ አገልግሎት ልክ ክፍያ መጠየቅ ሲጀምር አግልግሎቱን እንዳቆሙ ተናግረዋል።

የአኒሞ አስተዳዳሪ በአካባቢው የሳተላይት ቲቪ ከቀረበላቸው 25 አባወራ ወይም እማወራዎች አብዛኞቹ ከክፍያ በኋላ አገልግሎቱን እንዳቆሙ ይናገራሉ።

ቢቢሲ ‘ስታር ታይምስ’ በተለይም ከነጻ የሙከራ ጊዜ ጋር በተገናኘ አስተያየት እንዲሰጠው ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ቻይና በ‘ስታር ታይምስ’ የቲቪ ጣቢያዎች አማካኝነት ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደር ያደረገችው ጥረት የተደባለቀ ውጤትን አስከትሏል።

በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የሚቀርበው የቲቪ ጣቢያ እንደ ‘ኩንግ ፉ’ እና ‘ሲኖ’ ያሉ ድራማ፣ ፊልምና ተከታታይ ይዘቶችን ያሳያል።

በአውሮፓውያኑ 2023 ብቻ ከ 1 ሺህ በላይ የቻይና ፊልሞች በሀገሬው ቋንቋ ተተርጉመው በ‘ስታር ታይምስ’ በኩል እንደቀረቡ የኩባንያው ኃላፊ ማ ሻውዮንግ ለኬንያ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ኩባንያው በአውሮፓውያኑ 2014 በኬንያ በስዋሂሊ ቋንቋ ይዘቶችን የሚያስተላለፍ ጣቢያ ከፍቷል።

የቻይናን ፊልሞች የሚመለከቱ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግን ቅሬታ አላቸው። ፕሮግራሞች ያለፈባቸው ናቸው፣ የቻይናን መልካም ገጽታ ብቻ ያሳያሉ የሚሉና ሌሎች አስተያየቶች አሏቸው።

ሌሎች ደግሞ የሚወዷቸው ፕሮግራሞች አሉ።

ለምሳሌ ‘ሚስተር ራይት’ የተሰኘው ፕሮግራም ተወዳጅ ነው። ይህ ፕሮግራም ሰዎች ከእነሱ ጋር በፍቅር የሚገጥሙ ሰዎችን ሲፈልጉ የሚያሳይ ‘ሪያሊቲ ሾው’ ነው።

ይህ ፕሮግራም በቻይና ካለ የቲቪ ፕሮግራም በቀጥታ የተቀዳ ነው።

ለአንዳንዶች ‘ሚስተር ራይት’ ክፍያቸውን እንዲቀጥሉ እና ከ‘ስታር ታይምስ’ ጋር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል።

የኦሊስታ ነዋሪዋ የ21 ዓመቷ አርያና ኔሽን ንጎቲክ በአንዳንዶቹ ‘ሚስተር ራይት’ ‘ስታር ታይምስ’ ፕሮግራም ጋር ‘በፍቅር እንደወደቅች’ ትናገራለች።

ለምሳሌ የቻይና ተከታታይ ፊልም በሆነውና ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ አንድ ተከታታ ፊልም እጅግ ይመስጣታል።

“እሱን ፊልም ሳላይ ወደ መኝታየ አልሄድም” ስትል ገልጻለች።

እግርኳስ በርካቶችን የመሰብሰብ አቅም አለው

እግር ኳስ በአፍሪካ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ተመልካቾችን መሳብ የሚችል አቅም ይዟል።

ለአብነት፣ በአውሮፓውያኑ 2023 የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ‘ሪከርድ’ በሆነ ቁጥር ታይቷል። እንደ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መረጃ ከሆነ ይህንን የአፍሪካ ዋንጫ በዓለም ዙሪያ ወደ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ እይታ አግኝቷል።

ይህንን የተረዳው ‘ስታር ታይምስ የእግር ኳስ ጨዋታዎች የማስተላለፍ መብት ለማግኘት ከፍተኛ ወጪን ያወጣል። በዚህም የአፍሪካ ዋንጫ፣ የስፔን ላሊጋ እና የጀርመብ ቡንደስሊጋን የማስተላለፍ መብትን በእጁ አስገብቷል።

ዶክትር ሌዊስ “የእግር ኳስ ቀጥታ ሰርጭት ስታር ታይምስ ስሙን የገነባበት ዋነኛ መሳሪያ ነው” ይላሉ።

ውድድሩ ከፍተኛ ነው። በመልቲ ቾይዝ ስር ያለው ሱፐር ስፐርት የእንግሊዝ ፕሪሜየ ሊግን የማስተላለፍ መብት ለማግኘት በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚከፍል ይገለጻል።

የፈረንሳዩ ኮከብ ኪልያን ምባፔ ወደ በስፔን ላ ሊጋ ኃያል ወደሆነው ሪያል ማድሪድ ሲዘዋወር ‘ስታር ታይምስ’ ዕድሉን ተጠቅሞ በናይሮቢ ከፍተኛ ማስታወቂያ እያስነገረ ይገኛል።

በርካታ የአደባባይ ሰሌዳ ማስታወቂያዎችንም ሰቅሏል። በእነዚህ ማስታወቂያዎች ላይ ‘ስታር ታይምስ’ ሎጎ ከላ ሊጋ ከዋክብት ጋር “የላ ሊጋን የደስታ ስሜት ያጣጥሙ” የሚል ጽሁፍ ይዟል።

ችግሩ ይህ ማስታወቂያ ለሁሉም አይሰራም።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የእግር ኳስ ደጋፊ እሱ የሚደሰተው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እንደሆነ ይገልጻል።

“ብዙ ኬንያውያን ላ ሊጋ አያዩም። የእንግለዝ ፕሪሚየር ሊግ ነው በርካቶችን የሚስበው” ሲሉ በናይሮቢ ዴይ ስታር የኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ልቪ ኦባንዮ ይናገራሉ።

የቻይና ዓለም አቀፍ ጣቢያ ሲጂቲኤን ዝቅተኛ ክፍያ በሚጠየቅብት የቲቪ ጥቅል ውስጥ የተካተተ ሲሆን ቢቢሲ እና ሲኤንን ግን በሌላ ጥቅል ውስጥ ይገኛሉ።

በኬንያ ኬሪቾ የምትኖረው እና ጡረታ የወጣቸው መምህርት ሊያ ሩቶ “አዎ የቻይና ዜና ጣቢያ አለኝ ግን አላየውም። ምን ነበር የሚባለው? ሲ የሆነ ነገር ተ የሆነ ነገር ኤን ምናምን?” እያለች ሀሳቧን በሳቅ ታጅባ አጋርታለች።

በሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክትር ዳኒ ማድሪድ ሞራላር ‘ስታር ታይምስ’ በአፍሪካ ዜና ላይ ‘አቢዮት’ አላስነሳም ይላሉ።

በርካታ ነዋሪዎች የሀገር ውስጥ የዜና ምንጮችን እንደሚመርጡ ይናገራሉ። ‘ስታር ታይምስ’ም ያንን የተረዳ ይመስላል።

በዚህም ምክንያት የአፍሪካን ደምጽ ቀዳሚ ለማድረግ በማለም ከላሉት 5 ሺህ ሰራተኞች 95 በመቶ የሚሆት አፍሪካውያን እንደሆኑ የኩባንያው ቃል ቀባይ ገልጸዋል።

በአፍሪካ የቻይና መገናኛ ብዙሃን አማካሪ የሆነ አንድ ድርጅት ‘ስታር ታይምስ’ ቲክቶክ እና ሁዋዌ በምዕራበውያን የደረሰባቻው በጎ ያልሆነ አመለካከት ለማስወግድ እየጣረ እንደሆነ ይናገራል። ይህም ከምዕራባውያኑ የሚደርስብትን ጫና ለመቀነስ ያለመም ነው።

ዶክትር ለዌስ ከ2015 እስከ 2019 ‘ስታር ታይምስ’ ላይ የተሰሩ ዜናዎችን በመመለከት ጥናት ሰርተዋል። ጥናቱም አብዛኞቹ ዘገባዎች ‘ስታር ታይምስ’ን ከቻይና ወይም ከቻይና አፍሪካ ግንኙነት ተያይዞ እንዲጠቀስ እንደማይፈልግ አሳይቷል።

ተቋሙ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መነሻው ቻይና እንደሆነ አለመግለጽን ይመርጣል።

የግል ኩባንያ የሆነው ‘ስታር ታይምስ’ በዓመታት ውስጥ ከፍኛ የሚባል ስኬት አስመዝግቧል።

ሆኖም ለቤጂንግ ፕሮጀክቱ በተለይም መልካም ስሟን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት በኩል የተሳካለት አይመስልም።

“የቻይና መንግስት የመረጃ ፍሰቱን በማስተካከል መልካም ስም ለመገንባት ጥረት እያደረገች ነው። ነገር ግን በበቂ ሁኔታ አልተደገፈም” የሚሉት ዶክትር ማድሪድ ሞራልስ “ የፈሰሰው ገንዘብ ቻይናን ይህንን ያህል ጠቅሟታል ማለት አይቻልም” ሲሉ አክለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ተጠቃሚዎች በክፍያው እና ይዘቱ ላይ ጥያቁ አላቸው።

በየጣሪያው የተሰቀሉት ‘የዲሽ ሰሃኖች’ እየዛጉ ባለበት በዚህ ሰዓት የቻይና ቃል ተጽህኖ የመፍጠር ፍላጎት (soft-power) አብሮ እየተዳከመ ይመስላል።

‘ከስታር ታይመስ’ ጋር በክፍያ ምክንያት የተቆራረጠችው ቼፖካሚ “አዎ፣ ከቻይና እንደሚመጣ እናውቃለን። ነገር ግን ማንም እየተጠቀመው ስላልሆነ ምንም የሚፈጥረው ልዩነት የለም” ብላለች።