ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአክሱምን ሐውልት ከጣልያን ለማስመለስ የተደረገው ጥረት ሲታወስ
አሁን በሥፍራው የቀረ ምልክት የለም።በአንድ ወቅት አንድ ትልቅ ሐውልት ቆሞበት የነበረው ሥፍራ የእግረኞች መረማመጃ እና የሳይክል መንገድ ሆኗል።
ይህ ሥፍራ ከጥንታዊው የአክሱም ሐውልቶች አንዱ ከ68 ዓመታት በላይ ቆሞበት ነበር።
በጥንታዊቷ ሮም ፒያሳ አደባባይ ለአስርተ ዓመታት ተተክሎ የቆየው ሐውልቱ ሞሶሎኒ በሥልጣን የቆዩበትን 15ኛ ዓመት ለማክበር ነበር በአምባገነኑ መሪ ትዕዛዝ እንደ አውሮፓውያኑ 1937 ከኢትዮጵያ የተወሰደው።
ሐውልቱ የጦር ሽልማት ተደርጎ ከኢትዮጵያ ተነቅሎ ከተወሰደ በኋላም እንዲቆም የተደረገው በወቅቱ የኮሎኒ [የቅኝ ግዛት] ሚኒስቴር ፊት ለፊት ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ የጣልያን 'ቅኝ ግዛት' እንደነበረች ለማሳየት ሆነ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ይነገራል።
ሆኖም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ በ1952 ይህ መሥሪያ ቤት የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሆን ተደርጓል።ሐውልቱ በዚሁ መሥሪያ ቤት ደጅም ከአምስት አስርተ ዓመታት በላይ ቆይቷል።
ሐውልቱ ከሦስት የኢትዮጵያ መንግሥታት ያላሰለሰ ጥረት በኋላ በአገሩ ምድር ላይ ቀና ብሎ ከቆመ ዛሬ ድፍን 16 ዓመት ሞልቶታል።
ሐውልቱን የማስመለስ ጥረት
የአክሱም ሐውልትን ወደነበረበት ለመመለስ አጼ ኃይለሥላሴን ጨምሮ መንግሥታት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አጼ ኃይለሥላሴ ሐውልቱ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት ገና በተወሰደ በዓመቱ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ጣልያን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የዘረፏቸውን ቅርሶች ለመመለስ የገቡትን ስምምነት ተከትሎም የ'ቅርሶቻችን ይመለስልን ጥያቄ' በርትቶ ነበር።
ጣልያን እንደ አውሮፓውያኑ 1947 ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በገባችው በዚህ የሰላም ስምምነት መሠረት የመለሰቻቸው ሌሎች ቅርሶች ቢኖሩም፣የአክሱምን ሐውልት ግን ከስምምነቱም በኋላ ሳትመልስ አቆይታዋለች።
አጼ ኃይለሥላሴ እና የጣልያን ንጉስ ውሉን ቢፈራረሙም የጣልያን ባለሥልጣናት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ነበር የሐውልቱ የባዕድ አገር ቆይታ የተራዘመው ።
ንጉሳዊው ሥርዓት ተወግዶ የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላም ሐውልቱን ለማስመለስ ጥረቶች እንደነበሩ ይነገራል።
ሆኖም በአገር ውስጥ በብዙ ሁኔታዎች የተጠመደው ደርግ ጥረቱን ያን ያህል አልገፋበትም ነበር።
ከወታደራዊው የደርግ መንግሥት መገልበጥ በኋላ በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ጊዜም ይኸው ጥያቄ አልተዘነጋም።
በአገር ውስጥ የሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተደረገው ግን የኢህአዴግ መንግሥት በይፋ ከተመሰረተ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም የዚሁ ሐውልት ጉዳይ ይነሳ ነበር።
በመጨረሻም ጣልያንን ከ1992 እስከ1999 የመሩት ፕሬዚደንት ኦስካር ሉጂ ስካልፋሮ በ1997 ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በነበረበት ወቅት አበክሮ የሐውልቱን መመለስ ሲጠይቅ ከነበረው የወቅቱ መንግሥት ጋር ከስምምነት ሊደርሱ ችለዋል።
የተፈራረሙትን ስምምነት ተከትሎም ለ68 ዓመታት በባዕድ አገር ባይተዋር ሆኖ የቆየው ሐውልቱ እንደ አውሮፓውያኑ 2005 ወደ አገሩ ሊመለስ ችሏል።
ሐውልቱን በማስመለሱ ሒደት ውስጥም ዓለም አቀፍ ተቋማት፣በአገር ውስጥ እና በውጭ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ሚናም ከፍተኛ ነበር።
ከእነዚህ መካከል በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ይጠቀሳል።
የኮሚቴው አስተባባሪ በኢትዮጵያ የተወለዱት ጃንፔየሮ አንጀሊኒ ሐውልቱን የማስመለስ ሒደቱ ብዙ የሃሳብ ፍጭቶች የነበሩበት፣ ዓመታትን የወሰደ እና በርካታ አካላትን ያሳተፈ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ጃምፔሮ በሮም ለ47 ዓመታት ኖረዋል።በወቅቱ በፋኦ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረውን የአክሱምን ሐውልት ሲመለከቱ የተደበላለቀ ስሜት ነበር የሚሰማቸው።
በአንድ በኩል ቅርሱ ኢትዮጵያ የጣልያን ቅኝ ግዛት የመሆኗ ምልክት ተደርጎ መቆጠሩ ያበሳጫቸው ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ ድርጅቱ የሚመጡ ባለሥልጣናት እና መሪዎች ኢትዮጵያን እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል በሚል ይፅናኑ እንደነበር ይናገራሉ።
ሐውልቱን ለማስመለስ እንስቃሴ ሲጀመር ግን የቅርሱ ክብር በአገሩ እንደሆነ በማመን ኮሚቴውን በማስተባበር ጥረቱን ተቀላቅለዋል።
ጃንፔየሮ ሐውልቱን ለማስመለስ ከወቅቱ የአገሪቷ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ቢደረስም ከተተከለበት ቦታ የማንሳት እና የማጓጓዝ ሒደቱም ቀላል እንዳልነበር ያስታውሳሉ።
24 ሜትር ርዝመት እና 160 ቶን ክብደት ያለው ሐውልቱ ከሥፍራው በሚነሳበት ወቅት ይፈራርሳል የሚል ስጋትም አይሎ የሃሳብ ክፍፍል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ ነበር።
በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ባለው የቅርሶች አጠባበቅ እና አያያዝ ሁኔታ ቅርሶች በያሉበት ተጠብቀው ቢቀመጡ ይሻላል በሚል የሚከራከሩ፣በሌላ በኩል ደግሞ በክብር ለትውልድ መተላለፍ አለበት የሚሉ ነበሩ።
ሐውልቱን ለመመለስ ወጪው ብዙ በመሆኑና ለመላክም አስቸጋሪ በመሆኑ የጣልያን መንግሥት በምትኩ ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያሰራ የሚል ሃሳብም ቀርቦ ነበር።
ሆኖም ሐውልቱ የአገር ቅርስ እና ሐብት ነው ለትውልድ በክብር መተላለፍ አለበት የሚለው ሃሳብ አይሎ የነበረው የሃሳብ ፍጭት በዚህ እንደተቋጨ ጃንፔየሮ አውስተዋል።
“በመጨረሻም በባለሙያዎች እንዲጠና ከተደረገ በኋላም ሐውልቱ ሦስት ቦታ ላይ ተቆራርጦ እንዲነሳ እና እንዲጓጓዝ ውሳኔ ላይ ተደረሰ” ይላሉ።
'በእልልታ' የተሸኘው አክሱም
ጃንፔየሮ ሐውልቱ ከሮም አደባባይ ሲነሳ የነበረውን ሁነት የትናንት ያህል ነው የሚያስታውሱት።
የመጀመሪያው የሐውልቱ ክፍል ከሥፍራው ሲነሳ ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ ኅዳር 2003 ነበር።ወቅቱ ደግሞ አመሻሽ 11፡00 ሰዓት አካባቢ።
በሥፍራው በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያን ተገኝተው ነበር።
“ተሽከርካሪው ላይ ሲጫንም በእልልታ እና በጭፈራ ታጅቦ ነበር” ይላሉ።
በምን እና እንዴት ይጓጓዝ የሚለው ግን በወቅቱ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነበር። በዚህም ምክንያት ሐውልቱ ከሦስት ዓመታት በላይ በዚያው እንዲቆይ ተደርጓል።
ጣልያን በ1930ዎቹ ሐውልቱን ከኢትዮጵያ የወሰደችው በምጽዋ ወደብ በኩል በመርከብ ነበር።ከአክሱም እስከ ወደቡ ድረስም አዳዲስ መንገዶችን እና ድልድዮችን በመጠቀም በከባድ ተሽከርካሪ ነበር ያጓጓዘችው።
ከ70 ዓመታት ገደማ በኋላ ግን እነዚህን መንገዶች እና ወደቡን የመጠቀም እድል አልነበረም።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በነበረው ግጭት መንገዶቹ ፈራርሰዋል፤የወደቡ ባለቤትም ኤርትራ ሆናለች።በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነትም ሰላማዊ አልነበረም።
በመሆኑም ሐውልቱን በወጣበት መንገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የማይታሰብ ነበር።
ጃንፔየሮ እንደሚሉት በዚህ ምክንያት ነበር ሐውልቱ ከሥፍራው ተቆራርጦ ከተነሳ በኋላ እዚያው ሮም መጋዘን ውስጥ እንዲቆይ የተደረገው።
በመጨረሻ ግን ሐውልቱን በሩሲያ አንቶኖቭ የጭነት አውሮፕላን ለማጓጓዝ ተወሰነ።
ይህም ግን እንደታሰበው ቀላል አልነበረም።በወቅቱ የሩሲያውን አንቶኖቭ አውሮፕላን የሚያሳርፍ አየር ማረፊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ ይህንን ሥፍራ ለማዘጋጀትም ጊዜ ወስዷል።
ከዚያም በአውሮፓውያኑ 2005 ቀድሞ ወደነበረበት አክሱም ከተማ እንዲመለስ ተደርጓል።
እንደ ዩኔስኮ ከሆነ ይህንን ሐውልት መልሶ የነበረበት ቦታ ለመትከል ከሰባት ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎበታል።
ሐውልቱን ከጣልያን የመላኪያው ወጪ በአገሪቷ መንግሥት ነው የተሸፈነ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከተላከ በኋላ ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት በቶሎ ማቆም አልተቻለም ነበር።
ሐውልቱ ከተመለሰ በኋላ ለማየት በዓመቱ ወደ አክሱም አቅንተው እንደነበር የሚናገሩት ጃንፔየሮ፣ ሐውልቱ ተቆራርጦ እንደተጋደመ ሲመለከቱት “ በክብር የተቀመጠው ሮም ነበር” በሚል ሌላ ቁጭት አድሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከዚያ ግን በዩኔስኮ ድጋፍ እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 4፣2008 ሐውልቱ በቀድሞ ሥፍራው አክሱም ከተማ ተተክሎ ተመርቋል።
ሌሎች የአፍሪካ ቅርሶች እንዲመለሱ የፈጠረው ተነሳሽነት
በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በተካሄዱ ጦርነቶች ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች በርካታ ናቸው።
በትውልደ ኢትዮጵያውያን እና በአገሪቷ መሪዎች ጥረት እና ጥያቄ ወደ አገራቸው የተመለሱ ቢኖሩም፤ አሁንም የት እንዳሉ የማይታወቁ እንዲሁም በተለያዩ አገራት በሚገኙ ሙዚየሞች ባይተዋር ሆነው ተቀምጠው የሚገኙ ቅርሶች አሉ።
የአክሱም ሐውልት እንዲመለስ ሲደረግ ሌሎች ቅርሶችም መመለስ አለባቸው በሚል ስሜት ንቅናቄዎች ነበሩ።
ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ከ1960 የቅኝ ግዛት ማብቂያ በኋላ በጀርመን፣በእንግሊዝ፣ በሆላንድ እና በሌሎች አጋራት የተዘረፉ ቅርሶቻቸውን እየጠየቁ ያስመለሱ አሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አሁንም ድረስ ቅርሶቻቸው እንዲመለስላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ አገራትም አሉ።
በዚህ ላይ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጃንፔየሮ ይናገራሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 ላይ በጣልያን ቬኔሲያ በተደረገ ትልቅ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ የሆኑ ቅርሶች ቀርበው እንደነበር የሚናገሩት ጃንፔየሮ፣ ቅርሶቹ ‘ፕራይቬት ኮሌክሽን’ ተብለው [ እንደ ራሳቸው ሐብት ተደርገው] መቅረባቸው ቁጭት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
“ቅርሶች እንደ ማንኛውም ተራ ዕቃ ለዕይታ ሲቀርቡ ያናድዳል” ይላሉ። የአገር ቅርሶች በክብር ተጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ አለባቸው የሚል ጽኑ አቋምም አላቸው።
ሆኖም በአገር ውስጥ ያሉ ቅርሶች አያያዝም መሻሻል እንዳለበትም ይመክራሉ።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን እና የፋሲል ግንብን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች አደጋ እንደተጋረጠባቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
የአክሱም ሐውልቶችም አሁን ላይ የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከውስጡ በሚመነጨው ውሃ ምክንያት የመውደቅ አደጋ እንደተጋረጠበትና በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም ጉዳት እንደደረሰበት የአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ገብረመድኅን ፍፁምብርሃን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኃላፊው እንዳሉት ለሐውልቱ ይደረጋል የተባለው ጥገናም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከተስተጓጎለ በኋላ እስካሁን የተደረገለት ጥገና የለም።
በኢትዮጵያ የቅርሶች አያያዝ እና አጠባበቅ ደካማ ነው ሲሉ የሚተቹት ጃምፔሮ፤ቅርሶች የአንድ አገር ታሪክን ትልቅነት ማሳያ በመሆናቸው ተገቢው እንክብካቤ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በየአገራቱ ተበታትነው ያሉ ቅርሶችን ለማስመለስ እንዲጥሩም ጠይቀዋል።