በዘንድሮው ክረምት በመሬት መንሸራተት እና በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

በተያዘው የክረምት ወቅት እየጣለ ያለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተቶች እና የጎርፍ አደጋዎች አጋጥመዋል።

አደጋዎቹ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቅለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት በአገሪቷ በሐምሌ እና በነሐሴ ወር እስካሁን በተከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የ281 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በአደጋዎቹ 300 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ለችግር የተጋለጡ ሲሆን 142 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

በአደጋው ከተጠቁ ክልሎች መካከልም የጋምቤላ፣ አፋር፣ አማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ዋነኞቹ ናቸው።

በተለይ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በእነዚህ አደጋዎች የከፋ ጉዳት ደርሶበታል።

ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በክልሉ በጋሞ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ243 በላይ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በአደጋው ተጋላጭ ከሆኑ 17 ቀበሌዎች ቢያንስ 24 ሺህ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የጎፋው አደጋ የበርካቶችን ሕይወት ይቅጠፍ እንጂ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎችም የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም እንዲፈናቀሉ አድርገዋል።

በትግራይ በርካታ አካባቢዎች የክረምት ዝናብን ተከትሎ በተከሰቱ የመሬት መደርመስ አደጋዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በእንደርታ፣ ሰላዋ ወረዳ፣ ዓድዋ-የሐ እና ሌሎች የአካባቢዎች ባጋጠሙ የመሬት መደርመስ አደጋዎች በንበርትና በእንስሳ ሃብት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የክልሉ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በደቡብ ምስራቅ ዞን በምትገኘው ሰላዋ ወረዳ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ብቻ ከ500 መቶ በላይ አባወራዎች ከአደጋዎቹ ሸሽተው ደላ በምትባል ከተማ በትምህርት ቤቶች እና ሌሎች መጠለያዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

በጋምቤላ ፣ በአፋር፣ በአማራ ፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች በጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎች ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው ለመውጣት መገደዳቸውን የኦቻ ሪፖርት ያስረዳል።

በእርሻ ሰብል፣ በእንስሳት እና በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል።

የኦቻ ሪፖርት ከወጣ በኋላ በተከሰቱ መሰል አደጋዎችም የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል።

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ በተለያዩ ወረዳዎች በተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከ23 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ዞኑ ገልጿል።

ከሰሞኑም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በስልጤ ዞን በሁለት ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የዞኑ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ ወሲል አሰፋ ተናግረዋል።

በዚያ አካባቢ አደጋው መከሰት የጀመረው ከግንቦት ወር ጀምሮ እንደሆነና በየዓመቱ መሰል አደጋዎች እንደሚያጋጥሙም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ አርሲ፣ ዶዶላ ወረዳ ባለፈው ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት 19 የቤት እንስሳት እና በ270 ሔክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል መውደሙን የወረዳው አስተዳዳሪ አወልይ ነቢ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ አታለል አቦሃይ ጎፋን ጨምሮ አደጋዎች የተከሰቱባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ ቀድሞ ተለይተው እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አሳምነው ተሾመ፣ በኢትዮጵያ በክረምትና በበልግ ወቅቶች ከፍተኛ በሆነ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ምክንያት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል የአዋሽ ተፋሰስ፣ የስምጥ ሸለቆ፣ የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ፣ ኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ እንደሚጠቀሱ ቀደም ብለው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በአገሪቱ ዘጠኝ የሚሆኑ ክልሎች ለጎርፍ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህ ክልሎች በተለያዩ ወረዳዎች አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ እንደተገመተም በወቅቱ አስጠንቅቀው ነበር።

እነዚህ አደጋዎች ለምን የከፋ ጉዳት አደረሱ?

አደጋዎቹ የተከሰቱባቸው አካባቢዎች ያላቸው መልክዓ ምድር ለአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ አድርጓቸዋል። ተራራማ የመሬት አቀማመጥ ያላቸው ለመሬት መንሸራተት አደጋ ሲጋለጡ፣ ዝቅተኛ ቦታዎች ደግሞ በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል።

ሆኖም አንዳንዶቹ አደጋዎች የከፋ ጉዳት ያስከተሉት “ድሮም የነበረ ነው” በማለት በቸልተኝነት በመታለፋቸው፣ ሌሎች ደግሞ አደጋው ቀድሞ ከተገመተው በላይ በመሆኑ ያጋጠሙ መሆናቸውን አቶ አታላይ ተናግረዋል።

በጎፋ ከዚህ ቀደምም የመሬት መንሸራተት ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት የፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባዩ፣ አካባቢው በአደጋ ተጋላጭነት ተለይቶ ነበር ብለዋል።

ነገር ግን ነዋሪዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ሲነገራቸው ‘የዛሬ ዓመት በሰላም ኖረናል’ በማለት ለመነሳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ተናግረዋል።

“ሕብረተሰቡ የኖረበት አካባቢ ስለሆነ ለመነሳት ፈቃደኛ አለመሆን ታይቷል” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ሆኖም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ቀድሞ የተዘጋጀላቸው ማረፊያ ባለመኖሩ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በፀጥታ ስጋት ምክንያት ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ ባለው የግንዛቤ እጥረት ሳቢያ አደጋዎች ሲደርሱ በሚደረጉ የነፍስ አድን ጥረቶች ሕይወት ሲቀጠፍ ተስተውሏል።

በሌላ በኩልም በመንግሥት መሰራት ያለባቸው ተግባራት ባለመከናወናቸው በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሕይታቸው አደጋ ላይ የሚወድቁ ዜጎች አሉ።

ለአብነትም በርብ ወንዝ መሙላት ምክንያት በአማራ ክልል፣ ደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የሚከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ማንሳት ይቻላል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ችግሩን ያበረታባቸው የተፈጥሮ አደጋው ሳይሆን በአካባቢው ያለው ግድብ ግንባታ አለመጠናቀቁ ነው።

“ግድቡ ለምን እንደማይጠናቀቅ አናውቅም” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በየዓመቱ ግድቡ ሞልቶ በመፍሰሱ ለአደጋ እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት አርሶ አደሮች አደጋው ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ ቢነገራቸውም በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መውጣት እንዳልቻሉም አስረድተዋል።

“ ቀኑ ከፋ፣ ከዚህ ቀደም እንስሳቶቻችንን እንኳ እናስጠጋ ነበር።አሁን የት ሄደን እንጠጋለን” ብለዋል አንድ አርሶ አደር።

ቀደም ብሎ የሚወጡ ትንበያዎችን መሰረት በማድረግ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ለማንሳት የሚሰራ በቂ ሥራ ባለመኖሩም ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል።

በርካቶችን የገደለው የመሬት መንሸራተት

የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ዓለማችን እያጋጠማት ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተደጋጋሙ እና እየከፉ መምጣታቸውን ባለሙያዎች የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህም ቀጣይነት አለው ይላሉ።

በኢትዮጵያም በዘንድሮው ክረምት የበረታው ዝናብ መሬትን አቅም ያሳጣ ይመስላል።ከዚህ ቀደሙ በተለየ እዚህም እዚያም የመሬት መንሸራተቶች አጋጥመዋል።

የመሬት መንሸራተት በተዳፋታማ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት፣ በበረዶ መቅለጥ፣ በመሬት መሸርሸር፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ፣ በከርሰ መሬት ውስጥ ባለ የውሃ መጠን ለውጥ እና በሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያት በአንድ ወይም በእነዚህ ምክንያቶች ጥምረት ሊከሰት እንደሚችል ከአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በውሃ አካላት ውስጥም የመሬት መንሸራተት የሚከሰት ሲሆን ይህም በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በውሃ ሞገድ ሳቢያ ይከሰታል።አንዳንዴም እነዚህ ክስተቶችን አውሎ ነፋስ የቀላቀለበት የሱናሚ ማዕበልን አስከትለው የባሕር ዳርቻ አካባቢዎችን ይጎዳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች በበለጠ የመሬት መንሸራተት በስፋት እንዲሁም በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ሊከሰት ይችላል።

በዚህ ዓመት በኢንዶኔዥያ፣ በኔፓል እና በፓፓዋ ኒው ጊኒ ተመሳሳይ አደጋዎች ተከስተው የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፈዋል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2017 ባለው ወቅት የመሬት መንሸራተት 4.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጉዳት አድርሷል።በእነዚህም ዓመታት ውስጥ ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

ከዚህ አደጋ እንዴት መትረፍ እንችላለን?

በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካቶችን ሕይወት የተቀጠፈው ቀደም ብሎ በተከሰተ ናዳ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት በተደረገው ጥረት ወቅት ነበር።

በናዳው የተቀበሩ አራት ሰዎችን አስክሬን ለማውጣት ከተሰባሰቡ ዘመድ አዝማድና የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ከ200 በላይ የሚሆኑት ድጋሜ በተከሰተ ተመሳሳይ አደጋ ሞተዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ጠለምት ወረዳ በቅርቡ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋም የበርካቶች ሕይወት ያለፈው ቀደም ብሎ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሳሉ ናዳ የተጫናቸውን የሁለት ሰዎች አስክሬን ለማውጣት በማግስቱ ጥረት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አደጋዎች ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ ምንድን ነው?

የአሜሪካው ቀይ መስቀል አደጋው ድንገት ከተሰማዎት ሳይውሉ ሳያድሩ አካባቢውን መልቀቅ እንዲሁም ለጎረቤቶች እና ለባለሥልጣናት ማሳወቅን ይመክራል።

እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ድምጾችን በንቃት እንዲያዳምጡም ይመክራል፤ ለምሳሌ ዛፎች በሚንቀጠቀጡበት ወቅት ቋጥኞች ኳኳታ በሚፈጠርበት ወቅት ችላ አለማለት ያስፈልጋል።

በወንዝ አቅራቢያ ለሚኖሩ ደግሞ “ድንገት የውሃ ፍሰት መጨመር ወይም መቀነስ ካጋጠመ እንዲሁም ውሃው ጥርት ካለ፣ ንጹህነት ወደ ጭቃ ከተለወጠ በደንብ አስተውሉ። እንደነዚህ አይነት ለውጦች አሉ ማለት የጥርጊያዎች እንቅስቃሴ አለ ማለት ስለሆነ በፍጥነት አካባቢውን መልቀቅ ያስፈልጋል።” ይላል።

ድንገተኛ አደጋ ከተከሰተም በናዳ የተያዙ ሰዎችን ለመታደግ ጥረት ከማድረግ በፊት ለባለሙያዎች ማሳወቅ እና ተጨማሪ ጉዳት እንደማያስከትል ማረጋገጥ እንደሚያስፈለግ ባለሙያዎች ይመክራሉ።