ከናይሮቢ - አዲስ አበባ በአውቶብስ የሕዝብ ትራንስፖርት ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Abyssinia Luxury Coach
'አቢሲኒያ ሌግዠሪ ኮች' የተሰኘ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ ተጓዦችን ማመላለስ መጀመሩን አስታወቀ።
ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት እሁድ በይፋ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን 'አቢሲኒያ ሌግዠሪ ኮች' ዳይሬክተር ሚካኤል ጄምስ ማቺዮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአንድ ጉዞ 7 ሺህ 500 የኬንያ ሽልንግ እንደሚያስከፍል የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለደርሶ መልስ ጉዞ ዋጋ 15 ሺህ የኬንያ ሽልንግ (16 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ገደማ) መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሚካኤል ከ'አቢሲኒያ ሌግዠሪ' በፊት 'ሮያል አላይድ' ተሰኘ ከናይሮቢ ሞያሌ እና ሞምባሳ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ድርጅት መኖሩን ጠቁመዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት የተመሠረተው 'ሮያል አላይድ' እስከ ሞያሌ ብቻ ይሠራ እንደነበር የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በአውሮፕላን ቲኬት መወደድ ሳቢያ የአውቶብስ ትራንስፖርት ፍላጎት መኖሩን እና ይህንን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል አገልግሎት አቅራቢ አለመኖሩን "በጊዜው ክፍተት ነበር" ይላል።
ይህን ክፍተት ለመሙላት ነው "ለምን ቀጥታ [ከናይሮቢ- አዲስ አበባ] ጉዞ አንጀምርም ብለን አቢሲኒያን ጀመርን" ሲሉ ያክላሉ።
"ስምንት ባስ ነው ያለን የእኛ ዕቅድ 16 መሆን አለበት የሚል ነው። ከ16ቱ ስድስት ባስ እዚያው ኢትዮጵያ እንዲሆኑ ነው የምንፈልገው [እነሱን] በጂቡቲ በኩል እናስገባለን" ሲሉ ቀጣይ የድርጅቱን ዕቅድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሚካኤል ገለጻ አቢሲኒያ ሌግዠሪ በየቀኑ ወደ በናይሮቢ እና በአዲስ አበባ መካከል የሕዝብ ማመላለስ ሥራዎችን ይሠራል።
ባለፈው ዕሁድ ሥራውን በይፋ ሲጀምር ሰባት ተሳፋሪዎች ከናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ትኬት ቆርጠው ነበር።
"እሁድ የሙከራ ጉዞ ነበር፤ነገር ግን በደንብ ማስታወቂያ ስላልተሠራ ቀጥታ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች አልተገኙም" የሚሉት አቶ ሚካኤል "ባሱ 46 ሰዎች የመያዝ አቅም ቢኖረውም ቀጥታ አዲስ አበባ የሚሄዱት ሰባት ሰዎች ብቻ ነበሩ" ብለዋል።
አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ሞያሌ ድረስ የሚሄዱ እንደነበሩ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ "ሰባቱን ሰዎች በሰላም ባስ ወደ አዲስ አበባ ሸኘናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዘው አውቶብስ ትኬት ተሽጦ ማለቁን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አውቶብሱ 46 ሰዎችን ብቻ እንዲጭን የተደረገበት ምክንያት ወንበሮች መካከል ክፍተት እንዲኖር እና ሰፋፊ ወንበሮችን ለመጠቀም መሆኑን አክለዋል።
አቶ ሚካኤል አውቶብሶቹ አስተናጋጆች፣ ራሳቸውን የቻሉ የሴቶችን እና የወንዶች መጸዳጃ፣ በውስጣቸው የኢንተርኔት እና 'ስክሪንን' ጨምሮ የመዝናኛ አግልግሎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የጉዞ መስመር እና ሰዓትን በተመለከተ አውቶብሱ ከቀኑ 10 ሰዓት ከናይሮቢ ሚነሳ ሲሆን፣ በማግስቱ ጠዋት ሞያሌ ይደርሳል።
ኢሚግሬሽን እስከሚከፈት ተሳፋሪዎች እንደሚያርፉ የጠቆሙት አቶ ሚካኤል ኢሚግሬሽን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ያልቃል ብለዋል።
ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ከሞያሌ፤ በያቤሎ፣ ቡሌ ሆራ፣ ዲላ፣ ሐዋሳ አድርጎ ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ አዲስ አበባ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የፀጥታ ሁኔታውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሚካኤል "ይህ መስመር ከመጀመሩ በፊት በራሴ ከ10 ጊዜ በላይ ተመላልሻለሁ፤ በመንገዱ ላይ የፀጥታ ስጋት በእኔ ጉዞ አጋጥሞኝ አያውቅም። ከዚህ በተጨማሪም የመንገዱን ደኅንነት በተመለከተ ከሞያሌ መረጃ ወስደን ነው የምንሄደው። እንዲሁም በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ በምሽት ጉዞ አናደርግም ቀን ብቻ ነው የሚጓዘው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ድርጅቱ ከተመሠረተ ስድስት ወራት እንዳስቆጠረ የጠቆሙት አቶ ሚካኤል በስምንት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ሥራውን እንደጀመረ እንዲሁም ይህን ቁጥር ወደ 16 የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው አስረድተዋል።
"[ድርጅቱ] መጀመሪያ ኬንያ ነው የተቋቋመው እዚህ ስንጨርስ እዚያ ሄደን ንግድ ፈቃድ ለማውጣት ጠይቀን ነበር ግን ዘገየ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር አቶ ደመቀ አጥፎ ከሦስት ሳምንት በፊት ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ኤምባሲው አስታውቆ ነበር።
አምባሳደር ደመቀ ለኩባንያው አመራሮች ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገለጻ ማድረጋቸውን የጠቆመው ኤምባሲው "የኩባንያው አመራሮች ይህንን ዕድል ተጠቅመው ቅርንጫፉን በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ አበረታተዋል" ብሏል።















