የዩክሬን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን በመዲናዋ በጥይት ተገደሉ

የተገደሉት ባለስልጣን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን በመዲናዋ ኪዬቭ በቀን በጥይት መገደላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የዩክሬን የሃገር ውስጥ ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ ባለስልጣኑ በመኪና ማቆሚያ ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ተጠግቶ በርካታ ጊዜ በጥይት ከተኮሰባቸው በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

ጥቃት አድራሹ ከአካባቢው ሸሽቶ ሲሄድ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ተጋርቷል።

የደህንነት ተቋሙ የተገደለበትን ኃላፊ በስም ባይገልጽም የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ኮሎኔል ኢቫን ቮሮንይች እንደሆኑ ዘግበዋል።

የሃገር ውስጥ ደህንነት (ኤስቢዩ) የተሰኘው ተቋም የአገሪቱን ደህንነት እና ስለላዎችን በዋናነት የሚያካሂድ ነው።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2022 የሩስያን ወረራ ተከትሎ በሩስያ ውስጥ ግድያዎችን በመፈጸም እንዲሁም ጥቃቶችን በማቀነባበር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በዘንድሮው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ የሩስያ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑትን ኢጎር ክሪሎቭ ግድያ ጀርባ ይኸው ተቋም እንዳለበት የዩክሬን የጸጥታ አገልግሎት ምንጮች ቢቢሲን ጨምሮ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር።

በተጨማሪም ከጥቂት ወራት በፊት የሩስያው ጄኔራል ያሮስላቭ ሞስካሊክ በሞስኮ በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጂ የተገደሉ ሲሆን፤ ሩስያ ግድያውን የፈጸመችው ዩክሬን ናት ብላ ነበር።

የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት ለወታደራዊ ባለስልጣናቶቹ ግድያ በይፋ ኃላፊነትን አልወሰደም።

የደህንነቱ አገልግሎት ተቋምም ሆነ የኪዬቭ ፖሊሶች አሁን በጥይት ስለተገደሉት ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን ምክንያቱን አልተናገሩም።

የኪዬቭ ፖሊስ በስፍራው በጥይት የተገደለ አስክሬን በፖሊስ አባላት መገኘቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፖሊስ ጥቃት አድራሹን ለመለየት እና "በቁጥጥር ስር ለማዋል" እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን በመግለጫው አክሏል።

ኤስቢዩ በበኩሉ "የወንጀሉን ሁኔታ ለማጣራት እና አጥፊዎችን ለፍትህ ለማቅረብ ተግባራትን እያከናወነ" መሆኑን ገልጿል።

ሮይተርስ ያረጋገጠው የደህንነት ቪዲዮ ሐሙስ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሶስት ሰዓት ላይ በደቡባዊ ሆሎሲቪስኪ ግዛት ከሚገኝ አንድ ህንጻ አንድ ጂንስ እና ጥቁር ቲሸርት የለበሰ ሰው ሲወጣ ያሳያል።

ግለሰቡ የላስቲክ እና የጨርቅ ከረጢቶችን ይዞ በአቅራቢያው ወደሚገኝ መኪና ሲራመድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ ወደ እሱ ሲሮጥ ያሳያል።

ዩክራይንስካ ፕራቫዳ የተሰኘው የድረ-ገጽ የዜና ወኪል ጥቃት አድራሹ የደህንነት ባለሰልጣኑን አምስት ጊዜ በጥይት መትቶ እንደገደላቸው ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

የባለስልጣኑ ግድያ የተሰማው ሩሲያ የአየር ላይ ጥቃቷን አፋፍማለች በተባለበት ወቅት ነው።

ሩሲያ ማክሰኞ ዕለት በዩክሬን ላይ 728 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና 13 ባለስቲክ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ጥቃት ፈጽማለች።

ዩክሬንን ይህ መጠነ ሰፊ የአየር ላይ ጥቃት እንደሆነ ገልጻለች።

እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ ሩሲያ በዩክሬን መዲና በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 16 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል።