ፑቲን የትራምፕን የሰላም ጥሪ ውድቅ ካደረጉ በኋላ ኪየቭን በድሮን ደበደቡ

ሁለት አዛውንቶች የሩሲያን የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ለማምለጥ ሲሞክሩ

የፎቶው ባለመብት, DSNS

የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ ሌሊቱን በሰው አልባ አውሮፕላን ኪየቭን ስትደበድብ ማደሯን ገለፁ።

ሩሲያ ሌሊቱን በኪየቭ በፈፀመችው ከፍተኛ የድሮን ድብደባ የተነሳ ከፍተኛ ፍንደታዎች መሰማታቸውን እና አካባቢው በጭስ መሸፈኑን ተናግረዋል።

ዩክሬን፣ ሩሲያ 550 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና 11 ሚሳኤሎችን መተኮሷን ተናግራለች።

ጥቃቱ የደረሰው በዶናልድ ትራምፕ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል የስልክ ውይይት ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ከስልክ ውይይቱ በኋላ የዩኤስ ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ የሚያካሄዱትን ጦርነት ለማቆም ዝግጁ አለመሆናቸው "አሳዝኖኛል" ብለዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል እንዳስታወቀው ሩሲያ በአንድ ሌሊት ባካሄደችው የአየር ጥቃት 550 ሰው አልባ አውሮፕላኖች የተጠቀመች ሲሆን 72 ቱ የአየር መከላከያውን ጥሰው አልፈዋል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት እንዲሁ 537 ሰው አልባ አውሮፕላኖች የዩክሬንን የአየር ክልል ጥሰው ለመግባት ሞክረው ነበር ተብሏል።

ኪየቭ ለተከታታይ ስምንት ሰዓታት በሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትደበደብ የአየር ኃይሉ የአደጋ ጊዜ ደወል ለሊቱን ሲጮህ አሳልፏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋና ከተማው ውስጥ "ከክፉዎቹ" ምሽቶች መካከል አንዱ በማለት ጥቃቱን አውግዘዋል።

አክለውም "ሞስኮ ሳይዘገይ በጣም ከባድ በሆነ ማዕቀብ መቀጣት አለባት" ብለዋል።

አንድሪ ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ላይ "በኪየቭ ፍጹም አሰቃቂ እና እንቅልፍ አልባ ሌሊት ነበር። እስካሁን ከነበሩት አስከፊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ነበር" ሲሉ ጽፈዋል።

ፑቲን ከትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ውይይት በኋላ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ፣ ሲቢሃ "[ፑቲን] ሆን ብለው ነው የሚያደርጉት" ሲሉ ጽፈው "ለዩናይትድ ስቴትስ እና ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ላቀረቡ ሁሉ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያሳያል" ብለዋል።

የዩክሬን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል የእሳት አደጋ ሠራተኞች በኪዬቭ ሩሲያ ካደረሰችው መጠነ ሰፊ ጥቃት በኋላ እሳት ለማጥፋት ሲረባረቡ ያሳያል።

እንደ ዩክሬን ባለሥልጣናት መረጃ ከሆነ በኪዬቭ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 23 ሰዎች ቆስለዋል፣ የባቡር መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፣ በመዲናዋ ዙሪያ የሚገኙ ሕንፃዎች እና መኪናዎች ተቃጥለዋል።

ሩሲያ አሁን የፈጸመችው ጥቃት በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው የተኩስ አቁም ድርድር ከቆመ በኋላ አጠናክራ የቀጠለችው ጥቃት አካል ነው።

ሩሲያ እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ወረራ የፈጸመች ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት ጦርነት እየተካሄደ ነው።

ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ጦርነቱን ለማቆም ምንም አይነት መሻሻል እንደሌለ ተናግረዋል።

ትራምፕ "ዛሬ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ባደረግኩት ውይይት በጣም አዝኛለሁ፤ ምክንያቱም እዛ ያሉ አይመስለኝም እና በጣም አዝኛለሁ።"

"ማለቴ ጦርነቱን ለማቆም የሚፈልግ አይመስለኝም፤ እና ያ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው።"

ክሬምሊን "በዩክሬን ያለውን ጦርነት ዋና መንስኤ" ለማስወገድ መሞከሩን እንደሚቀጥል በድጋሚ ተናግሯል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለኪየቭ የምትሰጠውን የተወሰነ የጦር መሳሪያ ማቆሟን አስታውቃለች።

በሳምንቱ መጨረሻ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ካደረሰችው ትልቁ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሌስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች።

ሞስኮ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2014 በግዴታ የወሰደቻትን ክራይሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።