በጌዴኦ ዞን ራጴ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች በደረሰ የመሬት መንሸራተት የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ውስጥ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዞኑ ራጴ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ረቡዕ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ነው ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የመሬት መንሸራተት ያጋጠመው።

የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ጫራቃ እና ሀሮ በተባሉት ቀበሌዎች ውስጥ የደረሰው አደጋ መንስዔው ምሽቱን በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመሬት መንሸራተቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የገለጹት ባለሥልጣኑ ሌሎቹ ሁለቱ ሰዎች ደግሞ የተለያየ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን አስረድተዋል።

አደጋው የተደረሰው ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ በስፍራው ለተከታታይ ሁለት ቀናት የዘለቀ ከባድ ዝናብ ሲጥል ነበር ተብሏል።

በሰው ሕይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በመሬት ናዳው በርካታ ሰዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች መውደማቸውን ያስረዱት አስተዳዳሪው እስከ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በተደረገው ፍለጋ የስምንት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ጨምረው ተናግረዋል።

"የአንድ ቤተሰብ አባል አስከሬን እስካሁን አልተገኘም። በአካባቢው ከፍተኛ የናዳ ጫና ስላላ ሕይወቱ ሳያልፍ እንደማይቀር ይታመናል። ስለዚህም የግለሰቡን አስከሬን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ነው።"

በናዳው የሞቱ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት [ሐሙስ] መፈጸሙንም ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ጨምረው ተናግረዋል።

በሌሊት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት በስድስት ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን እና 165 ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለው በአንድ የመጠለያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርገዋል።

በሁለቱ ቀበሌዎች ውስጥ በደረሰው በዚህ አደጋ ከሞቱት ዘጠኝ ሰዎች በተጨማሪም በርካታ የቤት እንስሳት መሞታቸውን እና ሌሎችም አደጋዎች መከሰታቸውን በመግለጽ ዝርዝሩ ተጣርቶ እንደሚገለጽ አመልክተዋል።

አደጋው በደረሰበት ወቅት በአካባቢው ከጣለው ከባድ ዝናብ በተጨማሪ የቀበሌዎቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተዳፋታማ መሆናቸውን የገለጹት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ ቀደም ሲል ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ "አስጊ ቀበሌዎች በሚል የለየናቸው ናቸው" ብለዋል።

አክለውም በጌዲኦ ዞኑ ውስጥ ካሉት 164 ቀበሌዎች መካከል 64 የሚሆኑት የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት የተደቀነባቸው ሆነው መለየታቸውን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ሕዝብ ተዳፋት በሆኑ አካባቢዎች ለዘመናት መኖሩን የሚናገሩት አስታዳዳሪው ዶ/ር ዝናቡ፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት አደጋ አለማጋጠሙን አብራርተዋል።

የሚደርሱ አደጋዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ወደፊት በዞኑ ውስጥ ለእንዲህ ዓይነት የመሬት መንሸራተቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ለመለየት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

አሁን አደጋው የተከሰተበት አካባቢ በከፍተኛ ተዳፋታማ የሆነ ስፍራ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ከቦታው ለቅቀው እንዲወጡ ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር እየሠሩ ነው።

ባለፈው ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ውስጥ በተከሰተ ከባድ የመሬት መንሸራተት ከ225 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።