ዩናይትድ ኪንግደም የኤርትራው አምባሳደር ከአገሯ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም

የፎቶው ባለመብት, eritreanembassyuk.org.uk

የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በለንደን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ከአገሩ እንዲወጡ ማዘዙን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ኤርትራ እና ዩናይትድ ኪንግደም የአምባሳደሩን መባረርን በተመለከተ በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።

በአሁኑ ወቅት በለንደን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ድረ-ገጽ እንደሚያመለክተው የአምባሳደሩን ቦታ በመሸፈን የኤምባሲው (ሚሲዮን) ከፍተኛ ተጠሪ በመሆን የሚሠሩት ሳሌህ አብዱላህ ናቸው።

የዩኬ መንግሥት አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ላይ ከአገር እንዲወጡ የወሰደው እርምጃ፣ ኤርትራ ቀደም ብሎ ለወሰደችው ተመሳሳይ ውሳኔ ምላሽ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በኤርትራ የዩኬ አምባሳደር የሆነው የተሰየሙት ዲፕሎማት በኤርትራ መንግሥት አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ወደ አሥመራ መጓዝ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ይህንንም በተመለከተ የኤርትራ ባለሥልጣናት የዩኬ ተሿሚ አምባሳደር ወደ ምድብ ቦታቸው ገብተው ሥራቸውን እንደጂምሩ ለምን አስፈላጊውን ነገር እንዳላደረጉ የተሰጠ ምክንያት የለም።

በጉዳዩ ላይ ከኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ መብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ ትግርኛ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

አሁን ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት የኤርትራው አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ላለፉት ስምንት ዓመታት አገራቸውን ወክለው ዩኬ ውስጥ ሲሠሩ ቆይተዋል።

አምባሳደሩ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2015 ነበር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሟች ንግሥት ኤልሳቤጥ አቅርበው ሥራቸውን በይፋ የጀመሩት።

አምባሳደሩ መቀመጫቸውን ለንደን አድርገው ኤርትራን በዩኬ ከመወከላቸው በተጨማሪ፣ ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ደግሞ በአየርላንድ የአገራቸውን አምባሳደርነት ደርበው መሥራት ጀምረው ነበር።

ምንም እንኳን የኤርትራው አምባደሳደር ከለንደን እንዲወጡ ቢታዘዙም ኤምባሲው መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል የታወቀ ሲሆን፣ በአሥመራ የሚገኘው የዩኬ ኤምባሲም ለዜጎቹ የቆንስላ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ነገር ግን በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የሁለቱም አገራት ጥምር ዜግነት ያላቸውን ሰዎችን ለመርዳት አዳጋች ሁኔታ እንዳለ ተነግሯል።

ብሪታንያ ለረጅም ጊዜ በኤርትራ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ እና የዜጎች መብት ረገጣን ከሚተቹ ምዕራባውያን አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ለሁለት ዓመት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ተሳትፎን አጥብቃ ስትቃወም ነበር።

የዩኬ መንግሥት በየጊዜው በሚያወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ በኤርትራ የሚገኙ ዜጎቹ ከጅቡቲ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ድንበሮች ከ25 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ እንዳይሄዱ ያስጠነቅቃል።