ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ከዩክሬን በያዘችው ክልል የምታካሂደውን ሕዝበ ውሳኔ አራዘመች
የዩክሬን ደቡባዊ ከተማ፣ ኬርሶን ሩሲያን እንድትቀላቀል ለማስቻል ታቅዶ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ መራዘሙን በሩሲያ የተቋቋመው አስተዳደር ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በሩሲያ አስተዳዳር የአካባቢው ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ኪሪል ስትርሞውሶቭ “ሕዝበ ውሳኔው የተራዘመው በጸጥታ ምክንያት ነው” ብለዋል።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት ከባድ የሆነ የዩክሬን ድብደባ የኬርሶን ድልድይ በመጎዳቱ አያሳልፍም።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ በኬርሶን እና በሌሎች አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ ለመካሄድ መታቀዱ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ኃይሎቿ ቪይሶኮፒልያ የተባለችውን አነስተኛ ከተማ እንደገና መቆጣጠራቸውን አስታውቃለች። ከተማዋ ከኬርሶን 167 ኪሎ ሜትር ትርቃለች።
ይሁን እንጂ ቢቢሲ ይህንን ከገልለተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም፣ ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ጦር በደቡብ በኩል አጸፋዊ ምላሽ ወስዷል።
ከጦርነቱ አስቀድሞ አራት ሺህ ነዋሪዎች በሚኖሩባት በዚች ከተማ የዩክሬን ወታደሮች የዩክሬንን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
ይህ ምስል በፕሬዚደንት ቮሎዲይሚር ዘሌንስኪ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ክይርይሎ ታይሞሸንኮ የፌስቡክ ገጽ ላይ ነው የተጋራው።
የፎቶው መግለጫም “የኬርሶን ክልል፣ ቪይሶኮፒልያ ከተማ ዛሬ የዩክሬን ሆናለች” የሚል ነበር።
ፕሬዚደንት ዘሌንስኪ በበኩላቸው የዩክሬን ኃይሎች በደቡብ በኩል ሁለት ከተሞችን እንደገና መቆጣጠራቸውን ገልጸው፤ የአካባቢዎቹን ስም ግን አልገለጹም።
ሩሲያ በአብዛኛው በተቆጣጠረቻቸው በኬርሶን እና በደቡባዊ ዛፖሪዢያ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ እያቀደች ነው።
በሩሲያ በተቋቋመው አስተዳደር የኬርሶን ምክትል ኃላፊ ስትርሞውሶቭ፣ ለሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን እንዳሉት ዩክሬን በጦርነቱ የኬርሶን አንቶኖቭስኪይ ድልድይ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በድልድዩ ላይ ተሽከርካሪዎች ማለፍ አይችሉም።
ነዋሪዎችን በዲኒፕሮ ወንዝ ላይ የሚያሻግረው ጀልባም በዩክሬን ጥቃት ሥር እንደሚገኝ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።
ሩሲያ ድልድዩን ወታደሮቿን እና ቁሳቁሶችን ከኬርሶን ለማስገባት እና ለማስወጣት ትጠቀምበት ነበር።
ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎችን ከከተማዋ ለማስወጣት አሜሪካ ሰራሽ የሆኑ ሂምራስ በርካታ ሮኬት አስተኳሾችን አስማርታለች።
ከኬርሶን ባሻገር ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ 2014 በክሪሚያ እንዳደረገችው ሁሉ በሌሎች በቁጥጥር ሥሯ በሚገኙ ግዛቶች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እቅድ እንዳላትም አስታውቃለች።
የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢርይና ቨረሽቹክ፣ በአካባቢው የሚካሄደው ውጊያ በመፋፋሙ ሰላማዊ ሰዎች ኬርሶንን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለውም በታቀደው የሩሲያ ሕዝበ ውሳኔ ላይ የሚሳተፍ ሰው ክስ እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ ወረራ በዩክሬን ያለውን ሕይወት አናግቷል። በመሆኑም በእንዲህ ዓይነት ሕዝበ ውሳኔ ላይ ማን ድምጹን ሊሰጥ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
በ2014 በክሪሚያ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደው በጦሯ ቁጥጥር ሥር የነበረ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና አልተሰጠውም።