ሚካይል ጎርባቾቭ፡ ሩሲያውያን የሚነቅፏቸው ዓለም የሚያወድሳቸው አከራካሪው መሪ

ሚካይል ጎርባቾቭ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ ተጽዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

በእስያ እና በምሥራቅ አውሮፓ ግዙፍ ቦታዎችን ይዛ የነበረችውን እና ለ70 ዓመታት ያህል የዘለቀችውን የሶቪየት ኅብረትን መፍረስ በመሪነት መንበር ላይ ሆነው ተመልክተዋል።

እአአአ በ1985 በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የማሻሻያ መርሃ ግብርን ሲያወጡ ብቸኛው አላማቸው ለውጥ አልባ ነበረውን የአገራቸውን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ እና የፖለቲካ ሂደቶችን ማስተካከል ነበር።

ጥረታቸው በሶቪየት ኅብረት ብቻ ሳይሆን በቀድሞ ወዳጆቿ ውስጥ የኮሙኒስት አገዛዝ እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል።

ሚካይል ሰርጌይቪች ጎርባቾቭ መጋቢት 2 ቀን 1931 (እአአ) በደቡብ ሩሲያ በስታቭሮፖል ተወለዱ።

ከገበሬ እናት እና አባት ነው ተወለዱት። አሳቸውም ታዳጊ እያሉ እህል ከማሳ ላይ ሰብስቦ የሚወቃ ማሽንን (ኮምባይነር) ይዘውሩ ነበር።

በ1955 ከሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሲመረቁ ሁሉም ነገር ተቀየረ። የኮሙኒስት ፓርቲ ንቁ አባል ሆኑ።

ከአዲሷ ሚስታቸው ራይሳ ጋር ወደ ስታቭሮፖል ተመለሱ። በአጭር ጊዜ በአካባቢው የፓርቲ መዋቅር ፈጣን ዕድገት ያስመዘግቡ ጀመር።

ጎርባቾቭ በሶቭየት ኅብረት የመሪነት ሥልጣን ላይ የነበሩት በእድሜ የገፉ ሰዎች እንዲለወጡ ከሚፈልጉ አዲሱ የፓርቲው አራማጆች አንዱ ነበሩ።

እአአ በ1961 የወጣት ኮሚኒስት ሊግ የክልላቸው ፀሐፊ ሆኑ። የፓርቲው ኮንግረስ ተወካይም ለመሆን በቁ።

የግብርና አስተዳዳሪነት ሚናቸው ፈጠራዎችን እንዲያስተዋውቁ ዕድል ሰጣቸው። ይህም በፓርቲው ውስጥ ካለው አቋም ጋር ተዳምሮ በክልሉ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ አደረጋቸው።

አዲስ ኃይል

እአአ በ1978 ወደ ሞስኮ አቀኑ። ያቀኑት የማዕከላዊ ኮሚቴ የግብርና ጽሕፈት ቤት አባል ሆነው ነው። ከሁለት ዓመት በኋላ የፖሊት ቢሮ ሙሉ አባል ሆነው ተሾሙ።

ዩሪ አንድሮፖቭ ዋና ፀሐፊ በነበሩበት ወቅት ጎርባቾቭ በተደጋጋሚ ወደ ውጭ አገራት ተጓዙ። በ1984 ወደ ለንደን አቅንተው በነበረበት ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር ዐይን ውስጥ ለመግባት ቻሉ።

ታቸር ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ከሶቪየት ኅብረት ጋር ወደፊት በሚኖረው ግንኙነት ላይ ተስፋ እንዳላቸው ተናገሩ። “እኔ ጎርባቾቭን እወደዋለሁ። በጋራ መሥራት እንችላለንም” አሉ።

አንድሮፖቭን እአአ በ1984 ሲሞቱ ጎርባቾቭ ይተኳቸዋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ግን አልሆነም። ኮንስታንቲን ቼርኔንኮ ዋና ፀሐፊ ሆኑ።

ታመው ነበሩት ቼርኔንኮም ሕይወታቸው አለፈ። አሁን የጎርባቾቭ ተራ ደረሰ። በዕድሜ ትንሹ የፖሊት ቢሮ አባል የሆኑት ጎርባቾቭ ተተኩ።

በዚህም ከ1917 አብዮት በኋላ የተወለዱ የመጀመሪያው ዋና ፀሐፊ ለመሆን በቁ። ከሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ ኃይል ይታዩ ጀመር።

የጎርባቾቭ ቅንጡ አለባበስ፣ ግልጽ እና ቀጥተኛ መሆናቸው ከቀድሞዎቹ መሪዎች የተለዩ ያደርጋቸው ነበር። ሚስታቸው ራኢሳ ጭምር ከዋና ፀሐፊ ሚስት ይልቅ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤቶችን ትመስል ነበር።

ነፃ ገበያ

የመጀመሪያ ሥራቸው ሊወድቅ ከቋፍ የነበረዉን የሶቪየት ምጣኔ ሀብት እንዲያንሰራራ ማገዝ ነበር።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሳካ ከተፈለገ የኮሚኒስት ፓርቲው ከጫፍ እስከ ጫፍ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ተረድተው ነበር።

ይህ የጎርባቾቭ መፍትሔም ሁለት የሩሲያ ቃላትን ወደ መድረክ አመጣ። አገሪቷ “ፔሬስትሮይካ” ወይም እንደገና ማዋቀር ያስፈልጋታል እና ችግሩን ለመፍታት ዋናው መሣሪያ “ግላስኖስት” ወይም ግልጽነት ያስፈልጋል የሚሉ ናቸው።

እአአ በ1991 ሴንት ፒተርስበርግ ተብሎ በተሰየመው የሌኒንግራድ የኮሚኒስት ኃላፊዎች ጉባኤ ላይ “ኢኮኖሚው ከሌሎች አንጻር ወደ ኋላ ቀርቷል። እናንተ አሳፋሪዎች ናችሁ” ሲሉ ተናገሩ።

የመንግሥት ቁጥጥር የሚመራውን ኢኮኖሚ በነጻ የገበያ ለመተካት አላማ አልነበራቸውም። ይህንንም በ1985 ለፓርቲ ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ላይ በግልፅ አስቀምጠዋል።

“አንዳንዶቻችሁ ገበያው የኢኮኖሚያችሁ መዳኛ አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ። ጓዶች ግን ስለመርከቧ እንጂ ስለሕይወት አድን ጉዳይ አታስቡ። መርከቡ ደግሞ ሶሻሊዝም ነው” አሉ።

የሥርዓቱን መቀዛቀዝ ለመቋቋም ሌላው መሳሪያቸው ዲሞክራሲ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነፃ ምርጫዎች ተካሄዱ።

በጣም ከባድ ፈተና

የጨቋኙ አገዛዝ ለቀቅ ማለት የሶቪየት ኅብረትን በመሠረቱ የተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል መነቃቃትን ፈጥሮ ነበር። ታኅሳስ 1986 በካዛኪስታን የተካሄደው ረብሻ ያለመረጋጋትን በር ከፈተ።

ጎርባቾቭ ቀዝቃዛውን ጦርነት ለማቆም ፈለጉ። ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ጋር የተሳካ ስምምነት ለማድረግ ቻሉ።

በሶቪየት ወታደራዊ ኃይሎች መካከል ያለውን ውል አስቀሩ። ከአዋራጁ እና ከደም አፋሳሹ የአፍጋኒስታን ወረራም አገራቸውን አገለሉ።

በጣም ከባዱ ፈተና የመጣመው ያለፍላጎት በጉልበት ወደ ሶቭየት ኅብረት ከተካተቱት አገራት በኩል ነበር።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠረው ግልጽነት የዲሞክራሲ የነፃነት ጥሪዎችን አቀጣጠለ። ጎርባቾቭ መጀመሪያ ላይ በኃይል ለማፈን ሞከሩ።

የሶቪየት ኅብርት መፈረካከስ በሰሜን ባልቲክ ሪፐብሊኮች ተጀመረ። ላትቪያ፣ ሊቱዌኒያ እና ኢስቶኒያ ከሞስኮ ነፃ ወጡ። ቀስ በቀስም ወደ ሩሲያ የዋርሶ ስምምነት አጋሮች ተዛመተ።

እአአ. ኅዳር 9 ቀን 1989 የምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ በርሊን በነፃነት እንዲሻገሩ ሲፈቀድላቸው ነገሮች ይበልጥ ተቀየሩ።

ታንኮችን መላክ የሶቪየት የረዥም ጊዜ ልምድ ነበር። የጎርባቾቭ ምላሽ ታንኮችን መላክ አልነበረም። ይልቁንም ይህ ጀርመኖች ውስጣዊ ጉዳይ ነው አሉ።

ጎርባቾቭ እአአ በ1990 የኖቤል የሠላም ሽልማት ተሰጣቸው። “በምሥራቅ-ምዕራብ ግንኙነት ውስጥ በተደረጉት ስር ነቀል ለውጦች ውስጥ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና” ነው ሽልማቱን ይገባቸዋል የተባሉት።

ነሐሴ 1991 በሞስኮ የሚገኘው የቀደምቶቹ ኮሚኒስቶች ክፍል ግን በቃን አለ። በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደ። ጎርባቾቭ በጥቁር ባሕር ላይ ሲዝናኑ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የፓርቲው የሞስኮ የበላይ ቦሪስ የልሲን ነበሩ። ዕድሉን ተጠቀሙበት። መፈንቅለ መንግሥቱን በማስቆም ሰልፈኞቹን አስረው የጎርባቾቭን የፖለቲካ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ገፈፉ።

ከስድስት ወራት በኋላ ጎርባቾቭ ተባረሩ። የኮሚኒስት ፓርቲም ሕገ-ወጥ ተባለ። ሩሲያ አዲስና እርግጠኛ ያልሆነ ጉዞ ጀመረች።

ቀሪ ዓመታት

ሚካይል ጎርባቾቭ በሩሲያ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ቀጠሉ። በውጭ አገር ያለው ስም ሁሌም ከአገር ቤቱ ከፍ ያለ ነበር።

እአአ በ1996 ለሩሲያ ፕሬዝዳንትነት ተወዳደሩ። ያገኙት ድምጽ ግን ከ 5 በመቶ ያነሰ ነው።

እአአ በ1990ዎቹ በዓለም አቀፍ ትልልቅ መድረኮች ላይ ንግግር ያደርጉ ነበር። ከዓለም መሪዎች ጋር የነበራቸው የሞቀ ግንኙነትም ቀጠለ። በብዙ ሩሲያውያን ባልሆኑ ሰዎች ጀግና ተባሉ። ሽልማቶች በየአቅጣጫው ጎረፈላቸው።

እ.ኤ.አ. በ1999 ራኢሳ በደም ካንስር ሲሞቱ ቅስማቸው ተሰበረ። የሚስታቸው ከጎናቸው መቆም ለፖለቲካዊ ማሻሻያዎቹ ሰብአዊ ስሜትን ፈጥሯል ተብሎ ይታሰባል።

ጎርባቾቭ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀንደኛ ተቺ ነበሩ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የሚሄደውን አፋኝ አገዛዝ እየዘወሩ ነው በማለት ፑቲንን ይከሳሉ።

“ፖለቲካው ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አስመሳይ ዲሞክራሲ እየተቀየረ ነው። ሥልጣኑ በሙሉ በአስፈጻሚው አካል እጅ ነው” ብለዋል ጎርባቾቭ።

እአአ በ2014 ክሬሚያን በኃይል ወደ ሩሲያ ግዛት ለመቀላቀል የተደረገውን ሕዝበ ውሳኔ ግን ጎርባቾቭ ትክክል ነው ሲሉ ሞግተዋል።

“ከዚህ ቀደም ክሬሚያ በሶቭየት ሕጎች መሠረት ወደ ዩክሬን ተቀላቅላ ነበር። ይህም ሕዝቡ ሳይጠይቅ የፓርቲ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የተፈጸመ ነው። አሁን ሕዝቡ ራሱ ስህተቱን ለማስተካከል ወስኗል” ሲሉ ጎርባቾቭ ተናግረዋል።

በጎርባቾቭ 90ኛ የልደት በዓል መጋቢት 2021 ተከብሯል። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን “በአገራችን እና በዓለም ታሪክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካደረጉ የዘመናችን ታላላቅ መሪዎች አንዱ ናቸው” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ጎርባቾቭስ ስለራሳቸው አመራር ውጤት ምን ይላሉ? አምባገነናዊ ሥርዓትን እና የቀዝቃዛ ጦርነትን ማስቆም እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መቀነስ ትክክል ነበር ብለዋል።

በመፈንቅለ መንግሥቱ እና በሶቭየት ኅብረት መቀጨት ላይ አሁንም ቅሬታ አለ። ብዙ ሩሲያውያን አሁንም ለሶቪየት መፈረካከስ እሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ሚካይል ጎርባቾቭ ተግባራዊ እና ምክንያታዊ ፖለቲከኛ ነበሩ። በሶቪየት ኅብረት እና በሌሎች ቦታዎች በሚሊዮኖች የማይፈለገውን የኮሚኒስት ሥርዓትን ሳያጠፉ ለውጦችን ማምጣት እንደማይቻል ግን አልተገነዘቡም።