‘የት እንሂድ?’ የጋዛ ነዋሪዎችን መሸሸጊያ አልባ ያደረገው የተጠናከረው የእስራኤል ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA
“ወዴት እንሄዳለን? በጣም ፀጥ ያለ እና የሚያምር አስተማማኝ ቦታ እዚህ ሰፈር አለ?” ሲሉ በሪማል የሚገኙ ነዋሪዎች ይጠይቃሉ።
የፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የፈጸመውን ያልተጠበቀ ጥቃት ለመበቀል የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ሌላ ዙር ጥቃት በሚፈጽሙበት ወቅት “ያሳለፍኳቸው ሰባት ሰዓታት የሕይወቴ ከባዱ ጊዜያት እንደሆኑ አምናለሁ” ሲል የቢቢሲው ባልደረባ ሩሽዲ አቡ አሉፍ ገልጿል።
የእስራኤል ጥቃት በርካታ የመኖሪያ ሕንፃዎችን አውድሟል። የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ ቢሮዎች እና የጋዛ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻም ክፉኛ ተጎድተዋል።
ሰኞ ዕለት አስፈሪ ፍንዳታዎች አካባቢውን ሲንጡ አመሹ። ልጆች ያለቅሳሉ፤ ለደቂቃዎች ማሸለብ የቻለም የለም።
ጋዛ ውስጥ ሪማል የምትታወቀው የቱጃሮች መናኸሪያ በመሆን ነው። በፀጥታዋም ትመረጣለች። የአሁኑ ክስተት ግን ከአእምሮ የሚጠፋ አይደለም።
ማክሰኞ ጎህ ሲቀድ ጥቃቱ ተቀዛቀዘ። በዚህ ወቅት ነው የጉዳቱ መጠን የታወቀው። የሠፈሩ መሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። ወደ አካባቢው የሚያመሩ ጎዳናዎች በብዛት ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
አካባቢውን ለመቃኘት ስሞክር የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ ነው የሚመስለው። ፍርስራሽ፣ መስታወት እና ገመዶች በየቦታው ተበታትነዋል። የማውቃቸውን አንዳንድ ሕጻዎች ከደረሰባቸው ጉዳት አንጻር ልለያቸው አልቻልኩም።
“ምንም የቀረኝ የለም። አምስት ልጆቼ የሚኖሩበት እዚህ ሕንፃ ውስጥ ነበር። ከሕንጻው በታች ያለው ሱቄ ወድሟል” ሲል መሐመድ አቡ አል-ካስ ሴት ልጁን ተሸከሞ ይናገራል።
“ወዴት እንሄዳለን? ቤት አልባ ሆነናል። ከእንግዲህ መጠለያም ሆነ ሥራ የለንም።”
“እስራኤል ሆይ ለመሆኑ ቤቴ እና ሱቄ ወታደራዊ ዒላማ ናቸውን?” ሲሉ የእስራኤል ጦር በሲቪሎች ላይ አላነጣጠርኩም ማለቱን ውድቅ አድርገዋል።
የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሰኞ ዕለት ብቻ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከእነዚህም መካከል ሁለት ሦስተኛው ሲቪሎች ናቸው ብሏል።
ከቀትር በኋላ ደግሞ በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል። የእስራኤል ጦር የሐማስ አዛዥ መኖሪያ ቤት ላይ ማነጣጠሩን ጠቅሷል። ነገር ግን በአቅራቢያው በሚገኘው ገበያ ወይም በጎረቤት የሚገኙ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል።
እየተባባሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ
ከቅዳሜ ወዲህ በጋዛ የሟቾች ቁጥር 900 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋ። ከእዚህ ውስጥ 260 ሕጻናት ናቸው። 4,500 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በርካታ ሰዎች ተጨናንቀው የሚኖሩባት ጋዛ ቀድሞውንም አስከፊ የነበረው ሰብዓዊ ቀውስ ይበልጥ እየተባባሰ ይገኛል።
የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ የእስራኤል መንግሥት በጋዛ ላይ “ሙሉ በሙሉ ከበባ” እንዲደረግ በማዘዙ የጋዛ 2.2 ሚሊዮን ነዋሪዎች የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመብራት እና የውሃ እጥረት እያጋጠማቸው ነው።
የቅዳሜውን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል በኩል ከ1,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ100 እስከ 150 የሚደርሱ ሰዎችም በታጣቂዎቹ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
“በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ መብራት እና ውሃ እየኖርን እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ? ልጄ ዳይፐር የለውም። ግማሽ ጠርሙስ ወተት ብቻ ነው የቀረው” ስትል ዋድ አል-ሙግራቢ የተባለች የበሪማል ነዋሪ የፈረሰ ሕንጻ እየተመለከተች ተናግራለች።
“ለመሆኑ እስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመው ልጄ ነው?” ስትል ትጠይቃለች።
ከቅዳሜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከፈተው የጋዛ ትልቁ ሱፐርማርኬት የጀርባ በር ላይ በርካታ ሰዎች ተሰልፈው ነበር። ጦርነቱ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል ብለው በመፍራትም የሚችሉትን ሁሉ ለመግዛት ተስፋ ያደርጉ ነዋሪዎች ናቸው።
አብዛኛው የጋዛ አትክልት እና ፍራፍሬ በደቡብ የግዛቲቱ ክልል ይመረታል። በተከሰተው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ምክንያት ምርቱን ማጓጓዝ አስቸጋሪ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከግብፅም በኩል እስካሁን የገባ ምግብም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦት የለም። ሐማስ ጋዛን እአአ በ2007 ከተቆጣጠረ በኋላ በደኅንነት ምክንያት ግብፅ ከእስራኤል ጋር በመሆን በግዛቲቱ ላይ ጥብቅ ከበባ ፈጽማለች።
ነዋሪዎች በግብፅ አቅጣጫ የራፋህ ድንበርን በማቋረጥ ከጋዛ ለመሸሽም አልቻሉም። በጋዛ የሚገኘው የፍልስጥኤም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በቀን 400 ሰዎች ብቻ መውጣትም ሆነ መግባት ይችሉ ነበር።
ሰኞ እና ማክሰኞ በፍልስጤም ድንበር አቅጣጫ እስራኤል የአየር ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ነዋሪዎች በድንበር መተላለፊያው በኩል ለመሻገር ከባድ ሆኖባቸዋል።
ቤታቸውን ጥለው ከሸሹ 200 ሺህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች እንዲጠለሉ ተገደዋል። አንዳንዶቹ በፍርሃት፤ ሌሎች ደግሞ መኖሪያቸው በእስራኤል የአየር ድብደባ በመውደሙ የተሰደዱ ናቸው።
አንዳንድ የጋዛ ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤታቸው ምድር ቤት ውስጥ መጠለልን መርጠዋል። ይህ ግን ሕንጻው ቢፈርስባቸው ለመውጣት ሊቸገሩ ይችላሉ የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ሰኞ ምሽት በአንድ ምድር ቤት ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ሕንጻው ፈርሶባቸው ለመውጣት ሲቸገሩ ታይቷል።
የሪማል ነዋሪ የሆነው መሐመድ አል-ሙግራቢ “ባለፉት ጦርነቶች [እስራኤል] ድንበር ላይ ያለው ይህ የከተማው ክፍል ለነዋሪዎች ጥሩ መሸሸጊያ ነበር” ብለዋል።
የሰኞ ምሽት የእስራኤል ጥቃት ግን አሁን መሸሸጊያ የሚሆን ቦታ እንደሌለ አሳይቷል።












