ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ልውውጥ በኋላ ሰላም እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ለአንድ ሰዓት የዘለቀ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ የሁለቱ መሪዎች ንግግር "በጣም መልካም" እንደነበር ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ በበኩላቸው በትራምፕ አስተዳደር "በያዝነው ዓመት ዘላቂ ሰላም ሊመጣ እንደሚችል" ገልፀዋል።
አክለው በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ያለውን ዛፖሪዠዥያ የኃይል ማመንጫ በአሜሪካ እጅ እንዲገባ ስለማድረግ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።
ዜሌንስኪ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ዋይት ኃውስ አቅንተው ከትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር በቀጥታ በተላለፈ ስርጭት ተፋጠው እንደነበር አይዘነጋም።
ኦቫል ኦፊስ በተባለው የአሜሪካ ፕሬዝደንት እንግዶችን በሚቀበሉበት ሥፍራ በመሪዎቹ መካከል የተከሰተው አለመግባባት በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሁሉቱ መሪዎች ከዚህ እሰጥ-አገባ በኋላ በቀጥታ ሲነጋገሩ ይህ የመጀመሪያቸው ቢሆንም የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች በሳዑዲ አራቢያ ተገኝተው የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት አርቅቀዋል።
ትራምፕ እና ዜሌንስኪ የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ቢደግፉትም የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ማክሰኞ ከትራምፕ ጋር ከነበራቸው የስልክ ልውውጥ በኋላ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
ፑቲን የ30 ቀኑን ስምምነት ባይቀበሉትም የዩክሬን ኃይል ማመንጫዎችን ላለመምታት ለትራምፕ ቃል ገብተዋል።
ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር ባደረጉት ንግግር የኃይል ማመንጫዎች እንዳይመቱ የሚያደርግ ከፊል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ አሳውቀዋል።
ነገር ግን ሞስኮው የተኩስ አቁም ስምምነቱን የምታፈርስ ከሆነ ምላሽ እንደሚሰጡ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት አስጠንቅቀዋል።
ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሒደት ጥሩ እየሄደ እንዳለ ፅፈዋል።
ዝርዝር መረጃ ያካተተ መግለጫ ያወጡት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንዳሉት ትራምፕ ለዩክሬን አየር መቋቋሚያ ሥርዓት በተለይ ከአውሮፓ እርዳታ ለማግኘት እንደሚሰሩ ተስማምተዋል ብለዋል።
ፑቲንም ሆኑ ዜሌንስኪ የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም እንደሚስማሙ ቢያስታውቁም ሁለቱም መሪዎች አሁን እየደረሱ ላሉ ጥቃቶች እርስ በርስ ይወቃቀሳሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዜሌንስኪ ወደ አሜሪካ መጥተው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በአደባባይ በተሟገቱበት ወቅት ትራምፕ "በሶስተኛው የዓለም ጦርነት እሣት እየተጫወትክ ነው" ሲሉ የዩክሬኑን መሪ መውቀሳቸው ይታወሳል።
ከዚህ ግርግር በኋላ ነው አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ እርዳታ እና የደኅንነት መረጃ ልውውጥ ያቋረጠችው።
ፑቲን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚሠራው ዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ ማግኘት ስታቆም ነው ይላሉ። የዩክሬን አጋር የሆኑ ምዕራባዊያን ደግሞ ይህን ፈፅሞ አይቀበሉትም።












