የቱርኩ ፕሬዝዳንት ዋነኛ ተቀናቃኝ ፕሬዚደንታዊ እጩ ከመሆናቸው ከቀናት በፊት ታሰሩ

የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (CHP) አባል የሆኑት ኤክሬም ኢማሞግሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢስታንቡሉን ከንቲባ ለፕሬዚደንትነት እጩነት ሊመረጡ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው፣ በሙስና እና የሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (CHP) አባል የሆኑት ኤክሬም ኢማሞግሉ ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጠንካራ የፖለቲካ ተቀናቃኞች መካከል አንዱ ተደርገው ይቆጠራሉ።

አቃቤ ሕግ በሙስና እና የሽብር ቡድንን በመርዳት የከሰሳቸው ሲሆን "ወንጀለኛ ድርጅትን በመምራት ተጠርጣሪ" ሲል ወንጅሏቸዋል።

ፖሊስ ሌሎች ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን እና ነጋዴዎችን ጨምሮ 100 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ የኢስታንቡል አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ውስጥ የአራት ቀናት እገዳ ጥሏል።

ኢማሞግሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "የሕዝብን ፍላጎት ማፈን አይቻልም" ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ለቱርክ ሕዝብ እና "በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲሞክራሲን እና ፍትህን ለሚጠብቁ ሁሉ . . . በቆራጥነት ለመቆም" ቃል ገብተዋል።

ኢማሞግሉ አክለውም "ለመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በማደርገው ትግል በጽናት እቆማለሁ" ብለዋል።

በቱርክ ጎዳናዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና በምድር ለምድር ባቡር ጣቢያዎች ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል።

የፖለቲከኛውን እስር ተከትሎ የተቀሰቀሰው ይህ ተቃውሞ ለዓመታት ያልታየ የሕዝብ ቁጣ ነው ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቱርክ ትልቋ ከተማ በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል ግጭት መፈጠሩን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሮይተርስ የዜና ወኪል ምስሎች እንደሚያሳዩት ፖሊሶች ከኢስታንቡል ዩኒቨርሲቲ ውጭ ለተቃውሞ የወጣውን ሕዝብ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅመዋል።

መንግሥት በኢስታንቡል የአራት ቀናት የእንቅስቃሴ ገደቡ አካል የሆነ ማንኛውንም ሕዝባዊ ስብሰባ ከልክሏል።

የኢማሞግሉን የትዳር አጋርን ጨምሮ የተቃዋሚ መሪዎች ዜጎች "ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ" መጠየቃቸውን ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎች ይጠበቃሉ።

በኢስታንቡል ውስጥ በርካታ መንገዶች ለትራፊክ ዝግ የሆኑ ሲሆን፣ አንዳንድ የባቡር መስመሮችም አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል።

መቀመጫውን በዩኬ ያደረገው የኢንተርኔት ተቆጣጣሪ ኔትብሎክስ ረቡዕ ቱርክ እንደ ኤክስ፣ ዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ድረገጾችን መጠቀም ላይ በእጅጉ ገደብ ማድረጓን አስታውቋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ጋዜጠኞች እና በመዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ያሉ ባለ ሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ ሰፊ የእስር ዘመቻ እየተካሄደ ነው ተብሏል።

የኢስታንቡል ከንቲባ መታሰርን ተከትሎ ቱርክ ወደ አምባገነናዊ አስተዳደር እየተሸጋገረች ነው የሚል ስጋት በማህበራዊ ሚዲያዎች ተንጸባርቋል።

አንዳንዶች በመጪው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች እንዳይሳተፉ የጠየቁ ሲሆን፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ድምጽ መስጠት አይቻልም ሲሉ ተከራክረዋል።

የኢማሞግሉ ፓርቲ እስሩ "በቀጣዩ ፕሬዝዳንታችን ላይ የተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ነው" ሲል አውግዟል።

ነገር ግን የቱርክ የፍትህ ሚኒስትር የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ኤርዶዋንን ከከንቲባው እስር ጋር ያገናኙትን ተችተዋል።

ይልማዝ ቱንክ በቱርክ ውስጥ ማንም ከሕግ በላይ እንደማይሆን በመግለጽ፣ ይህ የፖለቲካ እርምጃ ነው ብሎ ማሰቡ "በጣም አደገኛ እና ስህተት ነው" ብለዋል።

ኤርዶዋን እና ፓርቲያቸው የቱርክ የፍትህ አካላት ነፃ እና ገለልተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ክሱን አስተባብለዋል።

ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ለ22 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት ኢማሞግሉ የኢስታንቡል ከንቲባ ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ ሲያሸንፉ ፓርቲያቸው (CHP) በኢስታንቡል እና በአንካራ የአካባቢ ምርጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፏል።

የኤርዶሃን ፓርቲ ከ21 ዓመታት በፊት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በአካባቢ ምርጫ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ዋነኛ ከተሞች ሽንፈት ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው ነው።

ምርጫው የኢስታንቡል ከንቲባ በመሆን ወደ ስልጣን ለመጡት ኤርዶዋን በግል ሽንፈት ነበር።

ፖሊሶች በቱርክ ትልቋ ከተማ የሚገኘውን የኢማሞግሉን መኖርያ ቤት የከበቡት ማለዳ ነበር።

የኢማሞግሉ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩውን የሚመርጠው የፊታችን እሁድ ሲሆን ግለሰቡ ፓርቲያቸውን ወክለው የሚቀርቡ ብቸኛው ዕጩ ነበሩ ተብሏል።