ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አውሮፓ ለፍልሚያ ዝግጁ መሆን አለባት አሉ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ አውሮፓ ሕዝቦቿን፣ እሴቶቿን እና የአኗኗር ዘይቤዋን ለማስጠበቅ ስትል ለፍልሚያ ዝግጁ መሆን አለባት ሲሉ ለዓለም መሪዎች ተናገሩ።
ቅዳሜ ዕለት በሙኒክ የደኅንነት ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት ስታርመር፤ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ጥልቅ ግንኙነት እና ትብብር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አውሮፓ "በራሷ እግር መቆም" እንዳለባት አሳስበዋል። ዩናይትድ ኪንግደም ከሩሲያ የሚነሳ ስጋትን ለመቀልበስ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ሲባል ከፍተኛ አቅም ያለውን የባሕር ኃይሏን በአርክቲክ እና ከፍተኛ ሰሜን እንደምታሰማራ ገልጸዋል።
ስታርመር በንግግራቸው የጠቀሱት 'ከፍተኛ ሰሜን' (High North) የዓለምን ሰሜናዊ ጫፍ ለመግለጽ የሚውል መጠሪያ ሲሆን ሥፍራውም የአርክቲክ ክበብን እና በአቅራቢያው ያሉ አካባቢዎችን ያካትታል።
በቀጣናው የተጋረጠውን የሩሲያን ስጋት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሌሎችም የኔቶ አጋሮች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።
በዩክሬን እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለመቋጨት ወደፊት ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ ሩሲያ የጦር ኃይሏን መልሳ "በፍጥነት" እንደምታጠናክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል አውሮፓ "ጥቃትን ለመግታት" እንዲሁም ካስፈለገም ለመዋጋት ዝግጁ መሆን እንዳለባት ተናግረዋል።
"ጠንካራውን ኃይላችንን መገንባት አለብን፤ ምክንያቱም የዚህ ዘመን መገበያያ [ወታደራዊ ኃይል] ነው" ሲሉም የአውሮፓ መሪዎችን አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አውሮፓውያን አገራት በኔቶ መመሪያ አንቀጽ 5 መሠረት ጥቃት የሚደርስበትን አጋር አገር ለመከላከል የገቡትን ቃል ያከብሩ እንደሆነ ጠይቀው ነበር። ከኔቶ መሠረታዊ መርሆች አንዱ የሆነው አንቀጽ 5፤ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የኅብረቱ አባላት ላይ የሚከፈት ጥቃት በሁሉም ላይ የተፈጸመ ተደርጎ እንደሚወሰድ ደንግጓል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥርጣሬ አዘል ጥያቄ ለማርገብ የሞከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዩናይትድ ኪንግደም ለአንቀጽ 5 ያላት ቁርጠኝነት "እንደ ምንግዜውም ሁሉ ጠንካራ" እንደሆነ ተናግረዋል። "ጥርጣሬ እንዳይገባችሁ፤ ከተጠራን ዩናይትድ ኪንግደም ዛሬውኑ ልታግዛችሁ ትመጣለች" ብለዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር አስቀድመው ንግግር ያደረጉት አውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርስላ ቮን ደር ሌየን፤ ስታርመርን "ፍንክች የማይል አጋር እና ወዳጅ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም "ከውስጥ ሆነው ኅብረታቸውን ሊያዳክሙ ከሚሞክሩ የውጭ ኃይሎች" ስጋት ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።
በአሜሪካ እርምጃዎች ምክንያት አውሮፓ ያልተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ መግባቷን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቷ፤ አህጉሪቷ ራሷን ለመከላከል ይበልጥ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባት ገልጸዋል። "አውሮፓ ወደፊት መውጣት እና ኃላፊነቷን መወጣት አለባት" ሲሉም አክለዋል።