ማክሮን 'ሩሲያን አታዋርዱ' ማለታቸው ዩክሬንን አስቆጣ

ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢማኑኤል ማክሮን

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩሲያ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት መዋረድ አይገባትም ማለታቸውን የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተቃውመዋል።

ዲሚትሮ ኩሌባ አጋሮቻቸው "ራሷን በማዋረድ ላይ የምትገኘው ሩሲያን ወደ ነበረችበት መመለስ ላይ የበለጠ ማተኮር አለባቸው" ብለዋል።

ማክሮን የተኩስ አቁም እና ድርድር ለማድረግ ፑቲንን በተደጋጋሚ በስልክ አነጋግረዋል።

ፈረንሳይ ከክሬምሊን መሪ ጋር ንግግር ለማድረግ የምታደርገው ጥረት ከአሜሪካ እና ከዩናይትድ ኪንግደም አቋም ጋር ይቃረናል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩሌባ በትዊተር ገጻቸው “የሩሲያን ውርደት ለማስቀረት የሚደረጉ ጥሪዎች የሚፈጥረው ፈረንሳይን እና መሰል ሃገሮችን ማዋረድ ብቻ ነው” ሲሉ አስፍረዋል።

የሩስያ ወረራ ጭካኔ እንደተሞላበት ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘትን አስከትሏል። ኪዬቭ በበኩሏ ሩሲያ ከዩክሬን መሬት ቅንጣት ስንዝር ማግኘት የለባትም ብላለች።

ማክሮን ቀደም ብለው ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የሩሲያው መሪ “ራሱን በራሱ አግልሏል” ብለዋል።

"እኔ እንደማስበውና የነገርኩትም ለህዝቡ፣ ለራሱ መሰረታዊ እና ታሪካዊ ስህተት ሰርቷል" ብለዋል።

"ራስን ማግለል አንድ ነገር ሲሆን ከዚህ መውጣት መቻል አስቸጋሪ መንገድ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ማሪዮ ድራጊም ከማክሮን ሃሳብ ጋር በማስማማት አውሮፓ “ተአማኒ ድርድር” እንዲኖር እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።

የሴቬሮዶኔስክ ከባድ ውጊያ

ምስራቃዊቷ ሴቬሮዶኔስክ የዩክሬን የውጊያ ማዕከል ሆና ቀጥላለች። የዩክሬን ሃይሎች የሩስያ ታንኮችን፣ እግረኛ ወታደሮችን እና ከፍተኛ መሳሪያ ጥቃቶች በመከላከል ላይ ይገኛሉ።

ከተማዋን ከተያዘች የሉሃንስክን ክልል በሩሲያ ኃይሎች እና በአካባቢው ተገንጣይ ኃይሎች ስር ትወድቃለች። በተጨማሪም አብዛኛውን አጎራባቹን የዶኔትስክ ክልልን መቆጣጠር ያስችላቸዋል።

የክልሉ የዩክሬን ገዥ ሰርሂ ሃይዳይ እንዳሉት ወታደሮቹ አንድ አምስተኛ የሚሆነውን ሴቬሮዶኔስክን መልሰው መያዝ ችለዋል ብለዋል።

“በቂ የምዕራብ ሃገራት የረዥም ርቀት የጦር መሳሪያ እስከያዝን ድረስ መሳሪያቸውን ከአካባቢያችን እናስወግዳቸዋለን። ከዛም እመኑኝ የሩስያ እግረኛ ጦር ዝም ብሎ ይሮጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የኪዬቭ ኃይሎች የሩስያ ዒላማዎችን ከርቀት በትክክል የሚመታ ሮኬቶችን ለመስጠት አቅዳለች። ዩናይትድ ኪንግደምም በርካታ ግዙፍ የሮኬት ባትሪዎችን ትልካለች።

ጦርነቱ አብዛኛው ሴቬሮዶኔስክ አወድሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች አሁንም ምድር ቤት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

አስተዳዳሪው ሃይዳይ እንደሚሉት ዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ እንዳታስገባ እና ለሲቪሎች እርዳታ እንዳታደርስ የሩሲያ ሃይሎች ድልድዮችን እያፈረሱ ነው።