"ለሳሙና ገንዘብ ለመቆጠብ ስል ልጆቼን እንዳይጫወቱ እነግራቸዋለሁ"

 ሱዛና ካትቱምባ

የፎቶው ባለመብት, Jack McBrams

በማላዊ የቤት ሠራተኛ የሆነችው ሱዛና ካትቱምባ በየወሩ የምታገኘውን 80,000 የማላዊ ገንዘብ ወይም (46 የአሜሪካ ዶላር) ደመወዟን አብቃቅታ ቤተሰቧን ስለምትደግፍበት መንገድ በየቀኑ ትብሰለሰላለች።

ሳሎን ውስጥ ካለው የውሃ ባልዲ ላይ እርጥብ ጨርቅ እያወጣች ጠረጴዛዎችን እና ወንበሮችን ማጽዳት ስትጀምር ገንዘብ ለመቆጠብ የዘየደችውን መላ እያጤነች ነበር።

የ43 ዓመቷ ወጣት ለቢቢሲ ስትናገር "የሳሙና ወጪ ለመቀነስ ትናንሾቹን ልጆቼን ሲጫወቱ በጣም እንዳይቆሽሹ ነግሬያቸዋለሁ። ነገር ግን በጣም ከባድ ነው ምክንያቱም ልጆች፣ ልጆች ስለሆኑ መጫወት ይፈልጋሉ።"

በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ የምትሰራ የአራት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ካትቱምባ ላለፉት ጥቂት ወራት በገበያ ላይ የሸቀጦች ዋጋ በመጨመሩ በደመወዟ ለመኖር ስትቸገር ቆይታለች።

ከቀድሞ የትዳር አጋሯ ከምትገኘው ትንሽ የገንዘብ ድጋፍ በስተቀር ቤተሰቧን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእሷ ጫንቃ ላይ ያረፈ ነው።

አብዛኛው ገንዘቧ ከዋና ከተማው በስተሰሜን ምዕራብ 130 ኪሜ ርቃ በምትገኘው በትውልድ ከተማቸው በካሱንጉ ለሚኖሩ አራት ልጆቿ ትልካለች።

ሁለቱ ትንንሽ ልጆች አሁንም በትምህርት ላይ ሲሆኑ ሁለቱ ትልልቅ ልጆች ደግሞ ሥራ አጥ ናቸው።

በግንቦት ወር የማላዊ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ከነበረበት 29.2 በመቶ ወደ 27.7 በመቶ ዝቅ ያለ ቢሆንም ይህ ግን በአፍሪካ ከተስተዋሉት ከፍተኛ የዋጋ ግሽብቶች አንዱ ነው።

"የሚገርመው ደሞዝ ባለበት መቆሙ ነው፤ የሸቀጦች ዋጋ ግን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው የመጣው" ስትል ካትቱምባ ተናግራለች።

"ገንዘቡ ገና በእጃችን ከመግባቱ በፊት ያልቃል። በጣም ከባድ ሕይወት እየኖርን ነው።"

ሸማቾች በማላዊ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርቡ የወጣው የኧርነስት ኤንድ ያንግ ሪፖርት ማላዊ ከቡሩንዲ፣ ሴራሊዮን፣ ሱዳን፣ ቬንዙዌላ እና ዚምባብዌ ጋር "ከመጠን ያለፈ የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚ" አላቸው ከሚባሉ ጥቂት የዓለም አገራት አንዷ ነች ብሏል።

ይህ በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ 100 ፐርሰንት ወይም ከዚያ በላይ የሚደርስ ድምር የዋጋ ግሽበት ሲኖር ነው።

የሂሳብ ድርጅቱ እንደገለጸው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) መረጃ መሠረት ማላዊ ከታህሳስ 2024 ጀምሮ የሦስት ዓመት ድምር 116 በመቶ የዋጋ ግሽበት እንዳላት እና ለ 2025 የ 102 በመቶ የዋጋ ግሽበት እና ለ 2026 የ66 በመቶ የሦስት ዓመት የዋጋ ግሽበት ትንበያ አካሄዷል።

ከዓለም ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አገሪቱ ከዓለም ድሃ ከሆኑ አገራት ተርታ ትሰለፋለች።

በደቡባዊ አፍሪካ የምትገኘው ማላዊ 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በቀን ከ2.15 ዶላር ባነሰ ገቢ እንደሚኖር ይገመታል።

አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ችግር ብዙ ዜጎችን እንደ ካትቱምባ ያሉትን ያለ ምንም ቁጠባ እንዲቀሩ አድርጓል።

"በወሩ መጨረሻ የተወሰነ ገንዘብ አጠራቅማለሁ ብዬ ራሴን እዋሻለሁ፤ ምንም የሚተርፈን ነገር የለም" ትላለች።

"በእያንዳንዱ የትምህርት ዘመን 50,000 የማላዊ ገንዘብ [29 ዶላር] እከፍላለሁ። ከዚያ የመማሪያ ደብተር፣ ምግብን፣ ሳሙና መግዛት ያስፈልገኛል፤ ሁሉንም የምገዛው ከዚችው ደመወዜ ላይ ነው። ስኳር [1 ኪሎ] አሁን 4,500 የማላዊ ገንዘብ [3 ዶላር] ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የማላዊን ወቅታዊ የዋጋ ንረት ችግሮች በከፊል ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ያያይዙታል።

ማላዊ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው የበለጠ ብዙ ስለምታስገባ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ትታገል ነበር።

በማላዊ ዩኒቨርሲቲ የማክሮ ኢኮኖሚክስ መምህር እና የማላዊ ኢኮኖሚክስ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር በርታ ባንጋራ ቺካዳዛ "ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ወደ ውጭ እየላክን አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እንደ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ስኳር ያሉ ምርቶችን ወደ ውጭ እንልካለን፤ ነገር ግን ውድ ምርቶችን እንደ ማዳበሪያ፣መድሀኒት እና የቤት እቃዎች ከውጭ እናስገባለን፤ ለዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እንፈልጋለን።"

ሸቀጦችን ለማስመጣት የሚፈልጉ የንግድ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ በተለይም የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ለባንኮች ሲያመለክቱ ባለመኖሩ ምክንያት ጥያቄያቸው ውድቅ ይደረጋል።

ይህም አንዳንዶች የአሜሪካን ዶላር በጥቁር ገበያ እንዲፈልጉ ያስገድዳቸዋል።

ይህ ምንዛሪ ይፋዊ ከሆነው የምንዛሬ ዋጋ ከፍ ያለ ነው። በይፋዊው የምንዛሬ ተመን አንድ የአሜሪካን ዶላር ዋጋ 1,750 የማላዊ ገንዘብ ነው።

ነጋዴዎች ለአንድ የአሜሪካ ዶላር ከ4,000 እስከ 5,000 የማላዊ ገንዘብ በ$1 መክፈል ይችላሉ።

ይህም በበኩሉ ሸማቾች ላይ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ይፈጥራል።

በዋና ከተማው የጽህፈት መሳሪያ ሱቅ ባለቤት የሆነው መሀመድ ሃኒፍ ዋካ ዋጋ ካሻሻለ በኋላ ብዙ ደንበኞችን እንዳጣ ተናግሯል።

"ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።ሠራተኞች መቀነስ ነበረብኝ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

እንደ ቢሮ እቃዎች፣ እስክሪብቶ እና ማስታወሻ ደብተር ያሉ ለሱቁ የሚሆኑ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ቢሆንም፣ በውጭ ምንዛሪ እጦት ሳቢያ አሁን እቃዎችን በአገር ውስጥ ለማግኘት እየሞከረ ነው።

"ባንኮቻችን የውጭ ምንዛሬ የሰጡንን ወቅት አላስታውስም"።

ለውጥ ለማየት የቋመጡ፣ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች በየካቲት ወር ተቃውሞ ለማሰማት ወደ ጎዳና ወጥተው ነበር፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማላዊን ፓርላማ መግቢያ ዘግተዋል።

የሊሎንግዌ ጾካ የእሁድ ገበያ ሊቀመንበር የሆኑት ስቲቭ ማጎምቦ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በእርግጥ ተጎድተናል፣ ከንግድ ሥራዎቻችን ትርፍ ማግኘት አለብን" ብለዋል።

"ነገር ግን ነገሮች እየወደቁ ነው። ማላዊያውያን ሸቀጣችንን መግዛት ተስኗቸዋል"።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከአይኤምኤፍ ጋር የተደረሰው የ175 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ለጊዜው መቆሙ ይፋ መድረጉ ይታወሳል።

የአራት ዓመት ብድር በሕዳር 2023 የፀደቀ ሲሆን እስካሁን 35 ሚሊዮን ዶላር ተሰጥቷል።

"በአይኤምኤፍ ፖሊሲ መሰረት፣ በ18 ወራት ውስጥ የሚደረጉ ግምገማዎች ካልተጠናቀቁ ፕሮግራሙ ወድያውኑ ያበቃል። እና እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ግምገማዎች በተሳካ ሁኔታ አልተጠናቀቁም" ሲሉ የማላዊ የአይኤምኤፍ ሚሽን ኃላፊ ጀስቲን ታይሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል

ሚስተር ታይሰን አክለውም "የፊስካል ዲሲፕሊን" "በከፍተኛ የወጪ ጫና ምክንያት አሁን ባለው አካባቢ ለመጠበቅ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል።

በማላዊ የኑሮ ውድነትን ተከትሎ የተደረገ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

ሆኖም የማላዊ የፋይናንስ ሚኒስትር ሲምፕሌክስ ቺቲዮላ ባንዳ በውሎች ላይ አለመግባባት በመኖሩ ብድሩን ለማገድ የወሰነው መንግሥት ነው ብለዋል።

ባንዳ ለቢቢሲ ወርልድ ቢዝነስ ሪፖረት "ተቀማጭ እንዲኖራችሁ ሲነግሯችሁ ነገር ግን አገሪቱ ነዳጅ ስለሌላት አገሪቱ ካዝናዋ ባዶ ቢሆንም ተቀማጭ ከማከማቸት ይልቅ ነዳጅ መግዛት ትመርጣላችሁ" ብለዋል።

"በፕሮግራሙ ውስጥ ለመቆየት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከል እንዳለብን ተነግሮን ነበር፤ ነገር ግን ይህ በመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።"

የማላዊ ብሔራዊ ምርጫ በመጪው መስከረም ሊካሔድ የታቀደ በመሆኑ መንግሥት የዋጋ ቅነሳ ለማድረግ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ብሏል።

የንግድ ሚኒስትሩ ቪቱምቢኮ ሙምባ የውጭ ምንዛሬ መከፋፈል እንዳለበት አምነዋል።

አክለውም የተመዘገቡ ንግዶች በመጠባበቂያ ባንክ ወይም በፋይናንስ ሚኒስቴር በኩል አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ማመልከት ይችላሉ ብለዋል። ነገር ግን ለዋጋ ንረቱ ነጋዴዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሚኒስትሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የኢኮኖሚ ማወክን የሚመለከት ሕግ እያዘጋጀን ነው፣ ይህንንም ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ረቂቅ ሕግ ይኖራል" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ ለዋጋ ግሽበት በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

የዋጋ ንረት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የኑሮ ውድነቱ ትልቅ የምርጫ ቅስቀሳ ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

የማላዊ ዜጎች የዕለት ተዕለት ትግላቸው በመንግሥት እቅድ እንደሚቀል ተስፋ ያደርጋሉ። እና ሁሉም በኢኮኖሚው ላይ ዘላቂ መረጋጋት የሚያመጣ መፍትሄ ይፈልጋል።

ካትቱምባ "ለእርዳታ መንግሥትን እንጠብቃለን።"

"ፖለቲከኞቹ ውሳኔያቸውን በሚያደርጉበት ጊዜ አነስተኛ ዕድል ያላቸውን ማላዊያውያን እንደሚያስታውሷቸው ተስፋ አደርጋለሁ" ትላለች።