የፀጥታ ችግር ባለበት የኦሮሚያ አካባቢ የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱ ተነገረ

በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የህክምና አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ባለፉት ጥቂት ወራት በተከሰተ የኩፍኝ ወረርሽኝ ምክንያት ሕጻናት እየሞቱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

በአካባቢው ባለው አማጺ ቡድን እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ግጭት ምክንያት መንገዶች በመዘጋታቸው ነዋሪዎች ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቁንዳላ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ቡርቃ ሚስማ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ካለፈው ዓመት ክረምት ጀምሮ በተለይም ሕጻናት በኩፍኝ እየተጠቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ወረዳው በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ የገለጹት ነዋሪው፣የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነዋሪው “ከቀናት በፊት ከአንድ ቤት ሁለት ሰው ቀብረናል። በፀጥታ ችግር ምክንያት የሕክምና ተቋማት ዝግ ናቸው። አሶሳ ደግሞ ከዚህ ይርቃል። ቤጊ መሄድም አስቸጋሪ ነው። የሕክምና ባለሙያዎች ለቀው ወጥተዋል” ብለዋል።

በአካባቢው ወባ እና ኩፍኝ የነዋሪው ዋነኛ የጤና ችግር መሆናቸውንና በአብዛኛው ለሞት እየተዳረጉ ያሉት ህጻናት መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ አብደና የኩፍኝ ወረርሽኝ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መከሰቱን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ወረርሽኙ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባት ለመስጠት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኃላፊው ጨምረውም የፀጥታ ስጋት በነበረበት የቆንዳላ ወረዳ “የሕክምና ባለሙያዎች ለቀው ወጥተው እንደነበርና አሁን ተመልሰው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“በፀጥታ ችግር መንገድ ሲዘጋ የመድኃኒት አቅርቦት መቋረጥ ይፈጠራል። ነገር ግን በሕዝብ ትራንስፖርት ወይም በቀይ መስቀል በኩል መድኃኒት ለማድረስ ጥረት ይደረጋል። ባለሙያዎችም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሥራቸውን ያከናውናሉ” በማለት መንግሥት አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እና የህክምና አቅርቦት እንደሚያደርስ ገልጸዋል።

የኩፍኝ እና የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች መንግሥት በአሸባሪ ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በስፋት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል በተደጋጋሚ ባጋጠሙ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል።

ኩፍኝ በከፍተኛ ሁኔታ ከሰው ወደ ሰው የመተላላፍ አቅም ያለው በሽታ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለአካል ጉዳት እና ለሞት ይዳርጋል።

የተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በምዕራብ ኦሮሚያ ባለው ግጭት ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመፈናቀላቸው ያለው ሁኔታ “ውስብስብ ነው” ብሏል።

ጨምሮም “በችግር ወዳሉ አካባቢዎች መድረስ፣ የፀጥታ ሁኔታ እና የአቅርቦት አቅም ችግር ፈተና” እንደሆነበት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።