ትራማዶል - ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎች ለሱስ የዳረገው እንክብል

ሃናን [ስሟ የተቀየረ] አንድ ሰሞን ትራማዶል የተሰኘውን መድኃኒት መጠቀም ጀምራ እንደነበር ትናገራለች።

እናቷ መቀለ ከተማ የመድኃኒት መሸጫ (ፋርማሲ) አላቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ትራማዶልን የወሰደችው እንደው ሕመሟን ቀለል እንዲያደርግላት በማሰብ እንጂ የጎንዮሽ ስሜቱን በማሰብ አልነበረም።

“መጀመሪያ ሳላውቅ ነበር የዋጥኩት። ከፍተኛ ራስ ምታት አሞኝ ለእሱ ማስታገሻ እንዲሆነኝ ነበር የወሰድኩት” ትላለች።

ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ስሜቷ ይቀያየር ጀመር። ምንጩን የማታውቀው የደስታ ስሜት ይወራት ያዘ።

“ከትንሽ ደቂቃ በኋላ የማላውቀው ዓይነት ደስታ እየተሰማኝ መጣ። ግራ ተጋባሁ። ምን ሆኜ ነው? ቤት ምን እየጠበቀኝ ነው? ደሞዝ ሊገባ ነው? ምንድን ነው? ብቻ ደስታው ከየት የመጣ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም።”

ሃናን፤ ይህ የደስታ ስሜት ከየት እንደመጣ ማሰላሰል ያዘች። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ‘ጉግል’ ወደተሰኘው የመረጃ ቋት አመራች።

ይሄኔ ነው መጣሁ ሳይል የመጣው የደስታ ስሜት የትራማዶል ውጤት እንደሆነ የተረዳችው።

መቀለ መድኃኒቱ በሁለት እንደሚከፈል ትናገራለች፤ የጀርመን ምርትና የአገር ውስጥ በሚል።

“ልክ ይሁን አይሁን ባለውቅም የጀርመን ብለን የምንገዛው የበለጠ ‘የከፍታ ስሜት’ ውስጥ ይከታል ብለን እናምን ነበር።”

“ካለምንም ምክንያት በጣም ደስተኛ ያደርጋል” የምትለው ሃናን ይህን እንክብል ለሁለተኛ ጊዜ መሞከር ፈለገች። የፈለገችውን አደረገች።

“ለሁለተኛ ጊዜ ገዝቼ ሞከርኩት። ከዚያ በኋላ ግን እናቴ ፋርማሲ ስላላት መውሰድ ስፈልግ ከዚያ ነበር የምውሰደው። ቀስ እያለ ከባድ እንደሆነ እየገባኝ መጣ።”

ሃናን፤ መድኃኒቱ ወደ ሱስ ከመቀየሩ በፊት ራሷን ከትራማዶል አራቀች።

“ደስተኛ መሆን ማንም ሰው የሚፈልገው ስሜት ነው። ግን እውነተኛ አይደለም። መድኃኒቱ ከሰውነት ሥርዓት በወጣ በደቂቃ ውስጥ ያው ተመሳሳይ ሰው ነህ። በጣም ሱስ ያስይዛል። ፈጣሪ ይመስገን እኔ እዚያ ደረጃ ላይም አልደረስኩም። የተወሰነ ከወሰድኩ በኋላ ምን እያደረግኩ እንደሆነ ስለገባኝና በቀላሉም እያገኘሁት ስለነበር በጣም አስፈራኝና ተውኩት።”

ትራማዶል ምንድን ነው?

በፈረንጆቹ 2017 እንግሊዛዊቷ ላውራ ፕላመር 300 ፍሬ ትራማዶል ወደ ግብፅ ይዛ ስትገባ በመያዟ በካይሮ መንግሥት የሦስት ዓመት እሥር ተፈረደባት።

የግለሰቧ ከርቸሌ መውረድ በርካታ እንግሊዛውያንን ቢያስደነግጥም ጉዳዩ በግብፅ ያለው የሚሊዮኖች ችግር የሆነው የትራማዶል ሱስ እንዲጋለጥ ምክንያት ሆኗል።

በርካታ ወጣቶች ከሱስ አስያዥ [ኦፒዮድ] መድኃኒቶች ተርታ የሚመደበው ትራማዶል የተሰኘውን እንክብል በተለያየ ምክንያት መውሰድ ይጀምራሉ።

ትራማዶል የተሰኘውን ክኒን የሚውጡ ሰዎች፤ ‘ሁሉም ነገር ማድረግ የምችል ያክል ይሰማኛል፤. . . ሁሉንም ነገር ያስረሳኛል’ ይላሉ።

አንደ ፍሬ ብለው ጀምረው፤ ወደ ሁለት፣ አልፎም ወደ ሦስት እና አራት ፍሬ ያመራሉ። ይሄኔ ነው የሱስን ዓለም እንደተቀላቀሉ የሚገባቸው፤ ለመውጣትም የሚቸግራቸው።

ሃናን፤ እኔ እንኳ ከአንድ ፍሬ በላይ ወስጄ ባለውቅም ሌሎች የማውቃቸው ሰዎች ግን መጠኑን እየጨመሩት ይሄዳሉ ስትል የታዘበችውን ትናገራለች።

ትራማዶል፤ ዋጋው ኪስ የማይጎዳና መካከለኛ ሕመም ለማስታገስ ጥቅም ላይ የሚውል መድኃኒት ቢሆንም፣ ልክ እንደሌሎች የኦፒዮድ ቤተሰቦች ተጠቃሚዎችን ሱስ ላይ የሚጥል ነው።

በኢትዮጵያ ብቸኛው የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሠሩት ዶ/ር ዮናስ ላቀው ትራማዶል ሱስ አምጪ ከሚባሉ የመድኃኒት ዓይነቶች አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።

“እነዚህ መድኃኒቶች የሚያስከትሉት ሱስ ከባድ ነው። ከሌሎች የኦፒዮድ መድኃኒቶች አንፃር ስናየው ትራማዶል ጠንካራ የሚባል አይደለም” የሚሉት ባለሙያው፣ እኒህ እንክብሎች የማነቃቃት ስሜት ስላላቸው አንዳንድ ሰዎች ለዚህ ሲሉ እንደሚወስዷቸው ይናገራሉ።

ለምሳሌ ሞርፊን በፅኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ በማንኛውም ሆስፒታል በቀላሉ የሚገኝ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ፣ ከዚህ አነስ ያለው ‘ፔቲዲን’ የተሰኘው መድኃኒት በአብዛኛው በጤና ባለሙያዎች ዘንድ የሚዘወተር እንደሆነ ይገልጣሉ።

በእነዚህ መድኃኒቶች ተርታ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ትራማዶል ከሌሎቹ ሲነፃፀር የሚያስከትለው ጉዳትና ሱስ የማስያዝ አቅሙ ዝቅተኛ ነው ይላሉ።

“እንደዚያም ሆኖ ግን ሱስ የመሆን ዕድል አለው። ወጣቶች በተለያየ ምክንያት ሲወስዱት ይታያል፤ ‘ፋሽንም’ ሆኗል። ለመነቃቃት በማለት ወጣቶች ሲውስዱት እንሰማለን።”

ኦፒዮድ ምንድን ነው?

ኦፒዮድ፤ ከኮዴይን ጀምሮ ሄሮይን እስከተባለው ሕገወጥ ዕፅ ድረስ ያሉ መድኃኒቶችን የሚያካትት ነው።

እነዚህ በሐኪም የሚታዘዙ ኦፒዮዶች በዋናነት ለህመም ማስታገሻነት ያገለግላሉ።

እነዚህ መድኃኒቶች ሲወሰዱ በአእምሯችን ውስጥ ካሉ የኦፒዮድ ተቀባይ ሴሎች ጋር በመተሳሰር ሕመም እንዲሰማን የሚያደርገውን ስሜት በመዝጋት የደስታን ስሜት ከፍ ያደርጋሉ።

በጣም ጠንካራና በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ ከሚገኙ የኦፒዮድ ዓይነቶች መካከል ሞርፊን፣ ትራማዶል፣ ፌንታኒል፣ ሜታዶይን፣ ዲያሞርፊን፣ አልፌታኒል እንደሚገኙበት ዶክተር ዮናስ ያስረዳሉ።

ኦፒዮዶች ከቀላል እስከ ከባድ ህመም ለማስታገስ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

እንደ አስፕሪን፣ አይቡፕሮፊን [ibuprofen] እና ፓራሲታሞል ያሉ የሕመም ማስታገሻዎች ለተወሰነ ጊዜ ሕመም ብቻ እንዲወሰዱ ይመከራል።

ትራማዶልና ሌሎቹ የኦፒዮድ መድኃኒቶች ስቃይ ወይ ሕመምን ያስታግሳሉ። ነገር ግን የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሱስ ነው።

እነዚህ መድኃኒቶች አንዳንድ ሰዎች ላይ በእንግሊዘኛ ‘ዩፎሪያ’ [Euphoria] የሚባለው ደስታ የሚያጎናፅፍ ስሜት ይፈጠርባቸዋል።

‘ሱሰኛ የሕክምና ባለሙያዎች’

ዶክተር ዮናስ ላቀው ለሕትመት ካበቋቸው መፃሕፍት መካከል አንደኛው የሆነው ‘የአማኑዔል ሆስፒታል ታሪኮች’ 12 አጫጭር ታሪኮችን አዝሏል።

ዶክተሩ በዚህ ሥራቸው አንድ ልብ-ወለዳዊ የሕክምና ባለሙያ በመርፌ የሚወሰድ የሕመም ማስታገሻ ሱሰኛ ሆኖ ሕይወቱ ሲመሰቃቀል ያስነብባሉ።

የሕክምና ባለሙያዎች በብዛት የሚወስዱት የሕመም ማስታገሻ ‘ፔቲዲን’ የተሰኘው እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ፤ ይህ መድኃኒት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የትራማዶል ልዋጭ [Variant] የሆነው ፔቲዲን ጠንካራ እና ሕመም የማስታገስ አቅሙም ከፍ ያለ እንደሆነ ዶክተሩ ይተነትናሉ።

“ይህ መድኃኒት ሲወሰድ አንዳንድ ሰዎች ላይ የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ከፍ ያለ ስለሚሆን ሱስ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። ዋጋው ውድና በጣም ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ ወጣቶች በቀላሉ ሊያገኙት አይችሉም።”

አእምሮ ውስጥ ለውጦች ስለሚከሰቱ ማንኛውም ደስታ የሚያመጣ ነገር ሱስ የመሆን አቅም እንዳለው የሚናገሩት ባለሙያው፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ደስታው ቀርቶ ሰውነታችን ለመንቀሳቀስ የለመደውን ነገር መጠየቅ ይጀምራል።

“ደስታው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይቆማል። ይሄኔ ሰዎች ‘የዊዝድሮዋል’ ምልክቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ ትራማዶል የለመዱ ሰዎች ይሄን መድኃኒት ካልወሰዱ ደስታ ይርቃቸዋል፤ ምቾት የሚነሳ አካላዊ ለውጥ ያሳያሉ። ላብ፣ ብስጭት፣ ጭንቀት ወይም መከፋት ይታይባቸዋል። ሥነ-ልቡናዊ ለውጦች ያመጣሉ።“

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን አንድ በመንግሥት ጤና ጣቢያ የሚሠራ የፋርማሲ ባለሙያ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ትራማዶልና ሌሎች መሰል መድኃኒቶች መጠቀማቸው የአደባባይ ምስጢር ነው ይላል።

የሕክምና ትምህርት ጀምራ እንደነበር የምትናገረው ሃናንም እንዲሁ ዶክተሮች እና ነርሶች ካለባቸው ጫና አንፃር ትራማዶልና ሌሎች የኦፒዮድ መድኃኒቶችን እንደሚወስዱ አውቃለሁ ትላለች።

የመንግሥት ምላሽ

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ትራማዶልን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እንደሚሰጡ የተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት ቁጥጥር ቢሮ ጥናት ያሳያል።

ይህ ትራማዶል የተሰኘው የሕመም ማስታገሻ በብዛት ወደ አፍሪካ የሚገባው ከእስያ አገራት ነው።

ማሊ፣ ቤኒን፣ ግብፅ እና ሞሮኮ ይህ ሱስ የሚያስይዝ መድኃኒት ከእስያ በብዛት የገባባቸው የአፍሪካ አገራት ናቸው።

ምንም እንኳ ለሕመም ማስታገሻ የሚሆኑ የኦፒዮድ መድኃኒቶች አፍሪካ ውስጥ ብዙም ባይገኙም ትራማዶል ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየጎረፈ ይገኛል።

ወጣቱ የፋርማሲ ባለሙያ አሁን አገልግሎት የሚሰጥበት የመንግሥት ጤና ጣቢያ፣ ከተቀጠረ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነውና በዚህ ጊዜ በርካታ ወጣቶች የትራማዶል ሱሰኛ ሆነው እንደተመለከተ ይናገራል።

የፋርማሲ ባለሙያው አክሎ እንደሚናገረው ወጣቶች ይህን መድኃኒቶች ከሌሎች ሱስ አምጪ ዕፆች (ጫት፣ አልኮል. . . ) ጋር አብረው እንደሚጠቀሟቸው አስተውሏል።

መድኃኒት “ብዙም ውድ አይደለም” የሚለው ወጣቱ የፋርማሲ ባለሙያ እሱ በሚያገለግልበት ጤና ጣቢያ 10 ፍሬ የሚይዘው እሽግ 12 ብር ከ50 ሳንቲም ነው የሚሸጠው።

“በቀን ሁለት ጊዜ ነው የሚፈቀደው። አንዷ ፍሬ 50 ሚሊ ግራም ናት። በአንድ ጊዜ 100 ሚሊግራም መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን ከ200 ሚሊግራም በላይ በቀን አይፈቀደም። አንዳንድ ሰዎች እስከ አራት ፍሬ በአንድ ጊዜ ይወስዳሉ። አንዱን እሽግ በአንድ ቀን ሊጨርሱት ይችላሉ።”

ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ መድኃኒት በተለይ በታዳጊዎች ዘንድ ሱስ እየሆነ መምጣቱ አሳስቦኛል ያለው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አዲስ መመሪያ አውጥቷል።

የባለሥልጣኑ የምርት ደኅንነት ዳይሬክተር አስናቀች ዓለሙ መሥሪያ ቤታቸው ጥናት ከሠራ በኋላ ጠበቅ ያለ መመሪያ ማውጣቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትራማዶል ያለአግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳለ ጥናታችን አሳይቷል የሚሉት ዳይሬክተሯ “ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህ ትራማዶል የተሰኘው መድኃኒት ያለማዘዣ ከሚሸጡ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ መመሪያ አውጥቷል” ሲሉ ነግረውናል።

ከዚህ ዝርዝር መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ልዩ [ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ] ቁጥጥር ከሚያስፈልጋቸው መድኃኒቶች ተርታ መካከል እንዲመደብ መደረጉንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፤ ናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ የተባሉ የመድኃኒት ዓይነቶች ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶችን ስምምነት ተቀብላለች የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ መድኃኒቱ ከዚህ በኋላ ወደ አገር ቤት ሲገባም ሆነ አገር ውስጥ ሲመረት ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ።

“ሌሎች መድኃኒቶች በወደብም ጭምር ይገባሉ። ልዩ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መድኃኒቶች ግን በአየር ብቻ ነው የሚገቡት። ከገቡ በኋላ ወደ ጅምላና ችርቻሮ ሱቆች አልያም ወደ ጤና ማዕከል ሰንሰለታቸውን ጠብቀው ስለመሰራጨታቸው የሚያሳይ ሪፖርት ለባለሥልጣኑ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።”

አስናቀች፤ አክለው ትራማዶል ከዚህ በኋላ በልዩ ትዕዛዝ ካልሆነ በቀር ለተጠቃሚ እንዳይሸጥ ሆኗል ይላሉ።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የፋርማሲ ባለሙያም በተመሳሳይ ከመመሪያው በፊት ማንኛውም ሰው በቀላሉ ያገኘው የነበረው መድኃኒት አሁን በልዩ ማዘዣ ካልሆነ እንደማይሸጥ አረጋግጧል።

“እኔ የምሠራበት የመንግሥት ጤና ማዕከል ስለሆነ ድሮም ቢሆን ማዘዣ ማምጣት ግድ ይላል። አሁን በልዩ ማዘዣ ነው የሚታዘዘው።”

የፋርማሲ ባለሙያው አብዛኛዎቹ ታካሚዎች መጀመሪያ መድኃኒቱን የሚጀምሩት በሐኪም ትዕዛዝ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ሱስ ስለሚይዛቸው ራሳቸው ሄደው ከፋርማሲ መግዛት ይጀምራሉ ይላሉ።

“የመድኃኒቱ ቀለም ሰማያዊ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ 'ሰማያዊዋን መድኃኒት ስጠኝ' እያሉ ይመጣሉ።”

ዳይሬክተሯ ጨምረው ጤና ተቋማትና መድኃኒት መሸጫዎች እኒህን መድኃኒቶች በግልፅ እንዳያስቀምጡ አሊያም ተቆልፈው በፋርማሲው ኃላፊ ቁጥጥር እንዲደርግባቸው መመሪያ እንደወጣም ይገልጣሉ።

መድኃኒቱ መሰል ጉዳት እንደሚያመጣ እየታወቀ እንዴት በማንኛውም ፋርማሲ እንዲሸጥ ተፈቀደ? ተብለው የተጠየቁት የምርት ደኅንነት ዳይሬክተሯ “ዓለም አቀፉ ናርኮቲክ ቦርድ ቁጥጥር ውስጥ አላካተተውም ነበር። እኛም ለዚህ ነው መድኃኒቱ ያለ ሐኪም ማዘዣ ከሚሸጡ ዝርዝር እንዲገባ አድርገነው የነበረው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገር ግን አሁን በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳለ ባለሥልጣኑ በመረዳቱ እርምጃ እንዲወስድ እንዳደረገው ያስረዳሉ።

አስናቀች፤ በተጨማሪም ‘ፔቲዲን’ የተሰኘው በመርፌ የሚወሰድ እና በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ የሚዘወተረው መድኃኒት ተመሳሳይ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

“በትራማዶል ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በዚህም መድኃኒት ላይ እየተደረገ ነው። የጤና ባለሙያዎች ይህን መድኃኒት ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት ሰምተናል። እንዴት ቁጥጥር ኖሮ እንዲህ ዓይነት ትግበራ ይኖራል የሚል ጥያቄ ስላለ ወደፊት በይበልጥ ምርመራ እናደርግበታለን።”

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህን አዲሱን መመሪያ ተላልፈው የተገኙ ሰዎች እርምጃ እንደሚወስዳበቸው ያትታል።

“ለምሳሌ አንድ አስመጪ ባልተፈቀደ መልኩ ምርቱን ሲያዘዋውር ከተገኘ የአስተዳደር እርምጃ ይወሰድበታል፤ አልፎም በወንጀል ይጠየቃል” ይላሉ ዳይሬክተሯ።

የመድኃኒት ሱስ ሕክምና አለው?

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ትምህርት ቤት የክሊንካል ሳይኮሎጂ ባለሙያ እና በትምህርት ቤቱ የሱስ ማገገሚያ ማዕከል የሚሰሩት ዶ/ር አቤል ወልደሚካኤል፣ ወጣቶች በአብዛኛው በትራማዶል ሱስ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።

አክለውም በተለይ ሴት ልጆች በወር አበባ ወቀት ለሕመም ማስታገሻነት በብዛት ስለሚወስዱ ለችግሩ እየተጋለጡ ነው ብለዋል።

ስሟ እንዳይገለፅ የጠየቅችን በሃያዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ያለባትን ‘ከፍተኛ ማይግሪን’ እና የጨጓራ ሕመም ለማስታገስ ከፓራሲታሞል ጀምሮ የተለያዩ መድኃኒቶችን እንደሞከረች ትናገራለች።

ነገር ግን እኒህ ማስታገሻዎች ይበልጥ የጨጓራ ሕመሟን እንዳባሱት ታስረዳለች።

“ይህንን ለአንድ ሐኪም ጓደኛዬ ሳጫውተው 'ትራማዶል/ፓራሲታሞል [Tramadol/Paracetamol] የተሰኘው መድኃኒት ጨጓራ ስለማይነካ እሱን ብትወስጂ ይሻላል' ሲል መከረኝ።”

ትራማዶል/ፓራሲታሞል የተሰኘው ድብልቅ መድኃኒት ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የሕመም ስቃይን ለማስታገስ የሚሰጥ መድኃኒት ነው።

ነገር ግን ይህን መድኃኒት መውሰድ ከጀመረች ወዲህ የሆነ የተለየ ስሜት ይሰማት እንደጀመረ ምንጫችን ትናገራለች።

“ከሆነ ጊዜ በኋላ ህመም ከማስታገሱ ባለፈ መድኃኒቱ ደስ የሚል፣ ቀለል ያለ አይነት ስሜት ይፈጥልኝ ጀመር፤ ለየት ያለ ነገር አለው” ስትል የተሰማትን የምትገልጠው ወጣቷ ይህ የደስታ ስሜት የመድኃኒቱ ተፅዕኖ እንደሆነ አልገባኝም ነበር ትላለች።

ወጣቷ ከአራት ወራት በኋላ ትራማዶል የተሰኘውን መድኃኒት መውሰድ እንዳቆመች ትናገራለች።

እነዚህ ታሪኮች አንድ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዱናል። ሱስ ሊሆኑ የሚችሉ መድኃኒቶችን ለታካሚዎች መስጠት ለምን? የሚል።

የኢትዮጵያ የስቃይ ሕክምና መመሪያ፤ የስቃይ ሕክምና ቀላል ከሆኑት የሕመም ማስታገሻዎች [ፓራሲታሞል፥ አስፕሪን፣ ኤቦፕሮፊን] እንዲጀመር ይመክራል።

“ትንሽ አስቸጋሪ የሆነው በየት በኩል እንሳሳት የሚለው ነው” የሚሉት ዶክተር ዮናስ ስቃይን መለካት ልክ የደም ግፊትን እንደመለካት አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

“ለምሳሌ አንድ ሰው፤ መርፌ ሲወጋ ስቃይ አጋጠመኝ ሊል ይችላል። ሌላው ደግሞ በጥይት ተመትቶ ምንም ላይመስለው ይችላል። ትንሽ ቁስል ያለው ሰው ስቃይ ውስጥ ነኝ ቢል እኔ ውድቅ ላደርገው አልችልም፤ ሥነ-ምግባራዊም አይደለም። ስለዚህ እነዚህ መድኃኒቶች መታዘዛቸው አይቀርም።”

ዶክተር ዮናስ በእነዚህ መድኃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ሁለት ስህተት አስተውያለሁ ይላሉ። አንደኛው መድኃኒቱን ከልክ በላይ ማዘዝ ነው። ሁለተኛው ደግሞ መድኃኒቱ ይታገድ የሚለው አስተያት ነው።

ዶክተሩ መድኃኒቱ መታገድ አለበት በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። “ይህ ስቃይ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሕክምና መከልከል ነው።”

ዶ/ር አቤል በሕክምናና ሙያዊ እገዛ ከሱስ መውጣት እንደሚቻል ይናገራሉ።

በትራማዶልም ሆነ በሌሎች መድኃኒቶች ሱስ ለተጠመዱ ሰዎች የሚሰጠው ሕክምና ‘አዲክሽን ሳይካያትሪ’ ይባላል።

ሕክምናው ዘውዲቱ ሆስፒታል፣ አማኑኤል ሆስፒታል እና ጳውሎስ ሆስፒታል እንደሚሰጥ ዶክተር ዮናስ ገልጸዋል።

ወጣት ዮናታን ሊዮን በተለያዩ ሱሶች ለሃያ ሁለት ዓመታት ሲሰቃይ ከቆየ በኋላ በሕክምና ታግዞ ማገገም መቻሉን ይናገራል።

ከዚያ በኋላም ‘ጉድ ላክ ሪሃብልቴሽን ኤንድ ትሬንግ ሴተንር’ የተሰኘ ማዕከል ከፍቶ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህ ማዕከል ከሱስ ካገገሙ 237 ሰዎች መካከልም ትራማዶልን ጨምሮ ከሕመም ማስታገሻ ሱሶች የተፈወሱ እንዳሉ ወጣት ዮናታን ይናገራል።

በተለይ በቀን እስከ ሃምሳ የትራማዶል ክኒን ሲወስድ የነበረ እና በዚህም ምክንያት የልብ ሕመምተኛ ሆኖ የነበረ ሰው በማዕከሉ ከሱሱ መውጣት እንደቻለም ይገልጻል።

ከሁሉም ሱሶች መዳን እንደሚቻል ራሴ ምስክር ነኝ የሚለው ዮናታን፣ በማዕከሉ በሁሉም የሱስ ዓይነቶች የተጎዱትን ሰዎች ለመርዳት እየሰራ እንደሆነ ይናገራል።

ዶክተር ዮናስ መድኃኒቱ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል ቁጥጥሩን ከማጥበቅ ባለፈ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ ያምናሉ።

“ሰዎች ድንገት ሲከለከሉ በሆነ መንገድ ያንን ለማግኘት ነው የሚንቀሳቀሱት፤ ሕገ-ወጡን መንገድ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም። ስለዚህ ጎን ለጎን ማስተማር፣ የሱስ ሕክምና ተደራሽ ማድረግ እና አስቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት መልካም ውጤት ይኖረዋል።”