“ከስኳር ሕመምተኞች አንድ አራተኛው ስለበሽታው ምንም መረጃ አያገኙም” ጥናት

ከስኳር ታማሚዎች አንድ አራተኛው ምንም ዓይነት እርዳታ እንደማያገኙ አንድ ጥናት አረጋገጠ።

የዓለም የስኳር ሕመም ፌዴሬሽን እንዳለው ከታማሚዎች 26 ከመቶ የሚሆኑት ስለበሽታው ምንም ዓይነት መረጃ አያገኙም።

በዚህ የተነሳ ሕይወታቸው ትልቅ ፈተና ውስጥ ይወድቃል።

በቂ መረጃ እና ትምህርት ስለማያገኙ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስትሮክ፣ የኩላሊት ሕመም፣ መታወር፣ የእግር እብጠት እና የአእምሮ ጤና መቃወስ ይገጥማቸዋል።

ይህ ጥናት እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው በበይነ መረብ አማካኝነት 3 ሺህ 208 የሚሆኑ የስኳር ታማሚዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን መጠይቅ ካደረገላቸው በኋላ ነው።

ተጠያቂዎቹ ከብራዚል፣ ሕንድ እና ናይጄሪያ ናቸው።

ይህ የጥናት ውጤት ለሌላው አስደናቂ ቢመስልም በችግሩ ላለፉት ግን ምንም ነው።

“ስኳር እንዳለብኝ ተነገረኝ እንጂ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አልተነገረኝም”

በሰባት ዓመቴ ‘ዓይነት-1’ የስኳር በሽታ እንዳለብኝ የተነገረኝ ኮስታሪካ እያለሁ ነበር። ያደኩት ስለበሽታው ምንም መረጃ ሳይኖረኝ ነው።

ልጅነቴ በብዙ ጭንቅ የተሞላ ነበር።

ለአጥንት ሕመም የተሰጠኝ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት አድርሶብህ ነው ለስኳር የተዳረከው ተባልኩ።

በልጅነቴ የስኳር መጠን (ጉሉኮስ) መለኪያ አልነበረኝም።

ድንገተኛ እና ከባድ ድንጋጤ [ፓኒክ አታክ] በየቀኑ ያጋጥመኝ ነበር።

ኢንሱሊን መውሰድ አለመውሰዴን እስክዘነጋ ድረስ እሰቃይ ነበር። ምናልባት ሳልወስድ የወሰድኩ መስሎኝ ነው እያልኩ ኢንሱሊን ሁለት ጊዜ ወስጄ አውቃለሁ።

25 ዓመት ሲሆነኝ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሄድኩ። ያን ጊዜ ነው ስለ በሽታዬ በደንብ ማወቅ የቻልኩት። ዛሬ ግን ከዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና አገልግሎት በቂ መረጃ በማግኘቴና ክትትል በማድረጌ በተሻለ የስኳር ሕመሜን መቆጣጠር ችያለሁ።

እንደኔው ብዙ መረጃ ሳያገኝ የሚሰቃይ ሰው ይኖር ይሆን ወይ? ብዬ ስጠይቅ አና ሉሺያን አገኘሁ። አና ከሜክሲኮ ናት።

እሷ እንደነገረችኝ ከሆነ የስኳር ሕመምተኛ እንደሆነች ባወቀች ጊዜ የእርሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቧ ሕይወትም ነው አብሮ የተቃወሰው።

አና ሉሺያ የዓይነት 1 የስኳር በሽታ ታማሚ ናት።

ይህ የሆነው ገና 8 ዓመት ሳይሞላት ነበር። ይህን ያወቀችው ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ከተወሰደች በኋላ ነበር።

“ገና ልጅ ነበርኩ፤ ጣፋጭ ነገር አትበይም አሉኝ፤ ይህን ተመገቢ፣ ያን አትመገቢ ሲሉኝ ጊዜ ተስፋ ቆረጥኩ” ትላለች።

እናቷ ክሌመንቲና ስለልጃቸው አና ሲናገሩ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ፈታኝ እንደነበሩ ያሰታውሳሉ።

“ሐኪሞቹ መርፌ አወጋግ እንድለማመድ እና እሷን እንድወጋት ነገሩኝ። ቀስ በቀስ አብረን ተማርን” ይላሉ ክሌመንቲና።

ነገር ግን አናና እናቷ ስለ ስኳር ሕመም መረጃ ባላገኙባቸው የመጀመርያ ጊዜያት ብዙ ምስቅልቅል እንዳጋጠማቸው አይዘነጉትም።

“ትምህርት ቤት ራሱ የተለየ እንክብካቤ ሊኖር ይገባል፤ ስኳር ሕመምተኛ ተማሪዎችን ሲያገኙ ከዚህ በኋላ ሕይወትሽን በዚህ ሁኔታ መምራት ይኖርብሻል ማለት አለባቸው።’’

ስኳር ሕመም ምንድነው?

ስኳር የማይድኑት በሽታ ነው።

አንድ ታማሚ ስኳር አለው የሚባለው ሰውነቱ የስኳር መጠንን ማመጣጠን ወይም መቆጣጠር ሲያቅተው ነው።

ይህም የሚሆነው ኢንሱሊን በሚባለው ሆርሞን የተነሳ ነው።

በአጠቃላይ ሁለት ዓይነት የስኳር ሕመም አለ። ዓይነት-1 እና ዓይነት-2 የሚባል።

አሁን አና ሉሺያ ዕድሜዋ 17 ደርሷል። አሁን ሁሉን ነገር በራሷ ነው የምትወጣው።

ነገር ግን በስኳር በሽታ መያዝ ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች።

“ትንሽ ሰዓት ነው የምተኛው። ምክንያቱም የስኳር መጠኔን መለካት አለብኝ። መርፌ ራሴን ከወጋሁ በኋላ ደግሞ ትንሽ ሰዓት መቆየት አለብኝ።”

አሁን ዘመናዊ የሚባል የስኳር መጠን መለኪያ [ጉሉኮስ ሴንሰር] አላት። ‘ፍሪስታይል ሊብሬ’ ይባላል። እጇን በመርፌ ሳትወጋ በቀላሉ የጉሉኮስ መጠኗን ማወቅ ያስችላታል።

አሁን አሁን ስታስበው “ምናለ ቀደም ብሎ ይህ መሣሪያ በነበረኝ” ትላለች።

ምንም እንኳ አና ሉሺያ የቤተሰብ ድጋፍ ባይለያትም ከትምህርት ቤት፣ የቤት ሥራ እና ፈተና ጋር ስኳርን ማስታመም ቀላል እንዳልሆነ ደጋግማ ትናገራለች።

ፕሮፌሰር አንድሩ ቦልተን እንደሚሉት የስኳር በሽተኞች ተገቢው መረጃ ካልተሰጣቸው ለጭንቀት እና ድብታ እንዲሁም በኋላ ላይ ነገሩ ከከፋ ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ ነው።

ጥናቱ እንደሚለው ከሆነ ታማሚዎች ብቻም ሳይሆኑ የጤና ድጋፍ ሠራተኞችም በስኳር በሽታ ዙርያ በቂ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው።

ብዙዎቹ ለምሳሌ ስኳር ሕመም ለከፋ ድብታ እንደሚዳርግ መረጃው የላቸውም።

“ብዙ የስኳር ታማሚዎች ከፍተኛ ድብታ ውስጥ ሲገቡ ለራሳቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ ያስጠላቸዋል። የስኳር መጠናቸውን መቆጣጠር ይተዋሉ” ይላሉ ፕሮፌሰር ቦልተን።

ፕሮፌሰሩ የሚመክሩት የስኳር ታማሚዎች ማንኛውንም መረጃ ማግኘት ከፈለጉ ያን መረጃ ከጤና ባለሙያ ብቻ እንዲቀበሉ ነው።

ብዙ ሰዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ ቃርመው ችግር ውስጥ እየገቡ ነው።

ሌላው ችግር ታማሚዎች ሐኪም ለማየት መስጋታቸው ነው።

ጥናቱ እንዳሳየው ከሆነ ስኳር ሕመምተኞች 99 ከመቶ የሚሆኑት በዓመት በድምሩ ከሦስት ሰዓት የበለጠ ሐኪም ዘንድ ቀርበው አያወሩም።

ይህ ደግሞ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል።

ስኳር ከሐኪም ጋር በመመካከር የሚገፋ ደዌ ነው። ለብቻ አይወጡትም።