ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ከዓለም ዋንጫ ውጭ ሆነ

ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ለክለቡ ባየር ሙኒክ ሲጫወት በደረሰበት ጉዳት ምንክያት የጉልበት ቀዶ ህክምና በማከናወኑ ከዓለም ዋንጫ ውጭ ሆነ።

ማክሰኞ ዕለት የሴኔጋል እግር ኳስ ፌደሬሽን ማኔ ከዓለም ዋንጫው “መጀመሪያ ጨዋታችን” ውጭ ይሆናል ብሎ ነበር።

ሐሙስ በተደረገለት ተጨማሪ ምርመራም ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈለገው ተረጋግጧል።

ባየር ሙኒክ ወርደር ብሬመንን ባሸነፈበት ጨዋታ ነበር ሴኔጋላዊው ጉዳት ደርሶበት ከሜዳ የወጣው።

ባየር ሙኒክ ተጫዋቹ ስኬታማ ቀዶ ጥገና ማከናወኑን አስታውቋል።

“ተጫዋቹ በጥቂት ቀናት ማገገም ይጀምራል” ብሏል ክለቡ።

ሴኔጋል በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ጨዋታዋን ሰኞ ዕለት ከኔዘላንናድስ ጋር ትጀምራለች።

በቀጣይም ከአስተናጋጇ ኳታር ቀጥሎ ደግሞ ኤኳዶር ጋር ትገናኛለች።

ለሁለት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ለመሆን የበቃው ማኔ የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነው። ባለፈው የካቲት ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በፍጻሜው ጨዋታ ግብጽን ሲያሸንፉ ወሳኟን የመለያ ምት አስቆጥሮ ነበር።

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በድጋሚ ከግብጽ ጋር ሲገናኙም ማኔ ለቡድኑ ባለውለታ መሆኑን አረጋግጧል።