ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዢ የቻይና-ካናዳ ግንኙነትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ በማቀበል ትሩዶን ወቀሱ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ አቅብለዋል ሲሉ የካናዳ ጠቅላይ ሚንሰትር ጀስቲን ትሩዶን ወቅሱ።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ከካሜራ ፊት ሆነው በአስተርጓሚ አማካይነት የጀስቲን ትሩዶ ተግባር አግባብ አለመሆኑን እና ‘ተዓማኒንት የለህም’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወቅሰዋል።
ዢ ጂንፒንግ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትርን በምን ጉዳይ እንደወቀሱ ግልጽ ባይሆንም ምናልባት ግን ጀስቲን ትሩዶ በካናዳ ምርጫ የቻይናን ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ በውይይት ላይ ከተናገሩት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ሁለቱ መሪዎች ኢንዶኔዢያ ባሊ እየተካሄደ ባለፈው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ላይ ፊት ለፊት ሲገናኙ ከዓመታት በኋላ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ሁለቱ መሪዎች በጋዜጠኞች የካሜራ ዕይታ ውስጥ ሆነው እና ፊት ለፊት ተቀራርበው በአስተርጓሚ አማካይነት ሲነጋገሩ ታይተዋል።
“የተነጋገርነው በሙሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተላልፎ ተሰጥቷል፤ ይህ አግባብ አይደለም” ሲሉ የቻይናው ፕሬዝዳንት ለትሩዶ ተናግረዋል።
ትሩዶ በበኩላቸው ፈገግ ብለው እና ጭንቅላታቸውን ወደላይ እና ወደታች ወዝውዘው፤ “በካናዳ ነጻ እና ግልጽ በሆነ ንግግር እናምናለን፤ ይህን በማድረግም ነው የምንቀጥለው” ሲሉ መልሰዋል።
“የማንግባባቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ገንቢ በሆነ መልኩ መነጋገራችንን በጋራ እንቀጥላለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ።
ሁለቱ መሪዎች በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ተጫባብጠው ተለያይተዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያጋጠመውን ክስተት አቅልለው ለማለፍ ሞክረዋል።
ቃል አቀባዩ ማኦ ኒንግ የፕሬዝዳንቱ ንግግር እንደ ወቀሳ እና አንድን ሰው ተጠያቂ አድርጎ የሚያቀርብ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ይበሉ እንጂ ይህ የሁለቱ አገራት መሪዎች የቃላት ለውውጥ በበርካቶች ዘንድ በቻይና እና ካናዳ መካከል ያለውን ከፍተኛ ውጥረት የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል።
በተለይ እአአ 2018 ላይ የሁዋዌ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜንግ ዋንዙ በካናዳ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ሻክሯል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከፍተኛ ኃላፊ እስር ምላሽ በሚመስል መልኩ ቻይና ሁለት የካናዳ ዜጎችን ሰላዮች ናቸው በሚል አስራ ነበር።
አሁን ላይ ሦስቱም ሰዎች ከእስር ተለቀዋል።
በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በአገራቸው ምርጫ ውስጥ ቻይና ጣልቃ ለመግባት ሙከራ አድርጋለች ብለዋል።
እአአ 2019 ተካሂዶ በነበረው የካናዳ የፌደራል ምርጫ ቢያንስ 11 ዕጩዎች በቻይና ሲደገፉ ነበር ተብሏል።
ቻይና በበኩሉ በሌሎች አገራት ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት በመግለጽ ራሷን ከጉዳዩ አርቃለች።