የማሌዢያን የመንገደኞች አውሮፕላን መትቶ በመጣል ሦስት ሰዎች ጥፋተኛ ተባሉ

የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት የበረራ ቁጥር ኤምኤች17 የመንገደኞች አውሮፕላን መትቶ በመጣል ሦስት ሰዎችን ጥፋተኛ አለ።

ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች እአአ 2014 በሩሲያ በኃይል ከተያዘ ዩክሬን ግዛት ሆነው የመንገደኞች አውሮፕላን መትቶ በመጣል 298 ሰዎችን ገድለዋል።

ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በኃይል ከያዘችው አካባቢ ሩሲያ ሰራሽ በሆነ ሚሳኤል የበረራ ቁጥር ኤምኤች17 አውሮፕላን ተመትቶ ወድቋል ብሏል።

ከዚሁ ድርጊት ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው ከታየው ሰዎች መካከል ሁለት ሩሲያውያን እና አንድ ዩክሬናዊ በሌሉበት ጥፋተኛ ሲባሉ ሦስተኛው ሩሲያዊ ነጻ ተብሏል።

የማሌዢያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 777-200ኢር የበረራ ቁጥር ኤምኤች17 የመንገደኞች አውሮፕላን 298 ሰዎችን ይዞ ከአምስተርዳም ወደ ኳላ ሉምፑር እያመራ ሳለ ነበር ከምድር ወደ አየር በሚወነጨፍ ሚሳኤል ተመትቶ የወደቀው።

ብይኑን የሰጡት ዳኞች ጥፋተኛ የተባሉት ሦስቱ ወንጀለኞች ምንም እንኳ የጦር እንጂ የመንገደኞች አውሮፕላን መትቶ ለመጣል ባያቅዱም አውሮፕላኑ ሆነ ተብሎ ተመትቶ ወድቋል ብለዋል።

ጥፋተኛ ከተባሉት መካከል አንዱ የዶኔክስ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ተብሎ የሚጠራው ጦር መሪ የሆነው ኢጎር ግርኪን ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ በሩሲያ ደኅንነት ውስጥ የቀድሞ ኮሌኔል ነው ይላል።

ግለሰቡ ከሩሲያ ድጋፍ በመጠየቅ አውሮፕላኑን መትቶ የጣለው ሚሳኤል ጥቅም ላይ እንዲውል ወጪ አድርጓል ተብሏል።

ቀሪዎቹ ሰርጌ ዱቢንስኪ እና ሊኦኒስ ክሃራቼንኮ ደግሞ ሚሳኤሉን እና የሚሳኤል ማስወንጨፊያውን በማጓጓዝ እና ሚሳኤሉን በመጠበቅ ጥፋተኛ ተብለዋል።

እአአ 2014 በዩክሬን አየር ክልል በ33 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ እየበረረ በነበረ አውሮፕላን ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት 298 ሰዎች መካከል 80ዎቹ ሕጻናት ሲሆኑ፣ 15ቱ ደግሞ የበረራ ሠራተኞች ናቸው።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ የኔዘርላንድስ ዜጎች ሲሆኑ፣ የማሌዢያ እና የአውስትራሊያ ዜጎችም ከፍተኛ ቁጥር ነበራቸው።

አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው በሩሲያ በሚደገፉ ኃይሎች እና በሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል በመሆኑ ለጥቃቱ ሞስኮ እጅጉን ስትብጠለጠል ነበር።

ሩሲያ በበኩሏ ከመንገደኞች አውሮፕላኑ ተመትቶ መውደቅ ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም ስትል ቆይታለች። ሞስኮ አውሮፕላኑ ተመትቶ ለመውደቁ የተለያዩ መላ ምቶችን እና ሐሰተኛ ማመሳከሪያዎችን ስታቀርብ ነበር ተብሏል።

ክሬምሊን በአንድ ወቅት አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው በዩክሬን ተዋጊ ጄት በመሆኑ ተጠያቂው የዩክሬን ጦር ነው ብላ ነበር።

ክስተቱን የመረመረው ዓለም አቀፍ ቡድን ግን አውሮፕላኑን ሰማይ ላይ ያጋየው ሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል አውሮፕላኑ አጠገብ ደርሶ ከፈነዳ በኋላ ነው ብለዋል።

የስልክ ንግግሮችን፣ የዐይን እማኞችን እና ከሟቾች ሰውነት ውስጥ የተሰበሰቡ ስብርባሪዎችን በመርመር ጥቃቱ የተፈጸመበት የጦር መሳሪያ አይነት እና ስሪት፣ መሳሪው ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ከየት ተነስቶ ወዴት እንደተወሰደ እና ጥቃቱን ያደረሱት ተጠርጣሪዎች መለየት ተችሏል።

ምንም እንኳ ሦስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ቢባሉም በእስር ጊዜ የማሳለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። ሞስኮ የፍርድ ሂደቱን ቀድማ ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ ነጻ ከተባለው ግለሰብ ውጪ ሦስቱ ሰዎች ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ጥፋተኞች ፍርዳቸውን ባይቀበሉ እንኳ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለሟች ቤተሰቦች ግን አንዳች የአእምሮ እረፍ ይሰጣል ተብሏል።

በጥቃቱ የ23 ዓመት ወንድ ልጇን የተነጠቀችው ሲሌን ፍሬድሪክስዝ፤ “ልጆቻችን መቼም መልሰን አናገኝም። . . . እውነቱን ግን ማወቅ እንፈልጋለን። ፍትሕ እንፈልጋለን። ይህ የፍትሕ ትንሹ አካል ነው” ብላለች።

ሲሌን ጨምራም ክስተቱ “ለእኛ ልብ ሰባሪ ነበር” ትላለች። ሲሌን በ2014 ላይ ዓመት በሩሲያ ላይ ጠንካራ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ አሁን ላይ ይህን ግጭት ባላየን ነበር ትላለች።

“ፑቲን በጭራሽ እልተገታም፤ አሁንም የሚያቆመው የለም። እንዲቆም እስካልተደረገ አይቆምም። . . . ዓለም ከተኛበት ነቅቷል ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም እኛ ከስምንት ዓመታት በፊት ነው ያወቅነው” ብላለች።