“ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” አንቶኒ ብሊንከን

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ጥሪ አቀረቡ።

ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመው ስምምነት አንደኛ ዓመትን በማስመልከት ባወጡት መግለጫ ላይ ሁለቱ አገራት “ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች በመቆጠብ የአካባቢውን አገራት ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ይህንን ያሉት ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማስወገድ ስምምነት ጉልህ እርምጃዎች መወሰዳቸው ካመለከቱ በኋላ በተጨማሪ ሊወሰዱ ይገባሉ ካሏቸው ተግባራት መካከል የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ መውጣትን ጠቅሰዋል።

በሁለቱ ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፋ የትግራይ ኃይሎችን ስትወጋ የነበረችው ኤርትራ ሠራዊት አሁን ድረስ በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ያላትን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም እንዲሁ በደፈናው አገራቱ የሁሉንም የአካባቢውን አገራት ሉዓላዊነት በማክበር ከግጭት እንዲቆጠቡ መጠየቃቸው፣ የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ ውስጥ መቆየት እና ከኢትዮጵያ በኩል የባሕር በር ጥያቄ መነሳቱን ለማመልከት ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ንግግር የባሕር በርን በተመለከተ “ኢትዮጵያ ውይይት ያስፈልጋታል ስትል ወራራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት ይደመጣል” በማለት፣ አገራቸው “በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም” ማለታቸው ይታወሳል።

በአፍሪካ ኅብረት፣ በአሜሪካ እና በኢጋድ አማካይነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱን ጨምሮ የተወሰዱ ጉልህ እርምጃዎችን አሜሪካ እንደምትደግፍ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ጨምረውም “ህወሓት ኃይሎቹ ከባድ መሳሪያቸውን ፈትተው ተዋጊዎቻቸውን ማሰናበት በተጀመረበት ጊዜ በትግራይ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፍን ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል” በማለት ለዚህም የኤርትራ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ መውጣት አለባቸው ብለዋል።

ከዚህ ባሻገርም “በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉት ግጭቶች ያሳስቡናል” ያሉት አንቶኒ ብሊንከን፣ ይህም በቀላሉ ሊታወክ የሚችለውን የኢትዮጵያን ሰላም አደጋ ላይ እንደጣለው አመልክተዋል።

እንዲሁም በአገሪቱ በተለያዩ ወገኖች የቀጠለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ጥቃት፣ “የመርዛማ ንግግሮች” መስፋፋ በጦርነቱ ምክንያት የሳሳውን ማኅበራዊ ትስስር የበለጠ እየሸረሸረው ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም አስተማማኝ የሽግግር ፍትሕ፣ ሐቀኛ እና አካታች ብሔራዊ ምክክር በመላዋ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱትን ግጭቶች ለመፍታት ውይይት እንዲደረግ በአስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች በበኩሉ የሰላም ስምምነቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ቢያስቆምም በአገሪቱ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደቀጠሉ ናቸው ብሏል።

ቡድኑ የፕሪቶሪያው ስምምነት የተፈረመበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከፕሪቶሪያው ስምምነት አንድ ዓመት በኋላ ግጭት እና ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሰሜን ኢትዮጵያ እንደቀጠለ ነው ብሏል።

የኤርትራ እና አማራ ኃይሎች በትግራይ ክልል አሁንም የመብት ጥሰቶችን እየፈጸሙ ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዋች፤ በአማራ ክልልም እንዲሁ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በሚደረገው ውጊያ ምክንያት የመብት ጥሰቶች እየተመዘገቡ ነው ብሏል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ፣ መሠረታዊ አግልግሎቶችን ለማስጀመር፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መስጠት እና ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚያስችሉ አሰራሮችን ቢዘረጋም፤ ስምምነቱ ግን በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች የሚመረመሩበት እና አጥፊዎች የሚጠየቁበትን ሁኔታ በዝርዝር አለመያዙ ፍትሕን ከማስፈን አንጻር ትልቅ ከፍተት ፈጥሯል ብሏል።

ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ላይ በተደረሰው ስምምነት የተቋጨው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ ጦርነት ከ600 ሺህ አስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን የሚያመለክቱ አሃዞች ከተለያዩ ወገኖች ሲወጡ ቆይተዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት እና የመሠረተ ልማት ውድመቶች አስከትሎ ነው ጦርነቱ የተቋጨው።